ሥርዓተ ንባብ

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ውድ አንባብያን በባለፉት ትምህርታችን ስምና የስም ዓይነቶች በሚል ርእስ በተከታታይ ማቅረባችን ይታወሳል፤ በዛሬውና በሚቀጥሉት ተካታታይ ትምህርታችን ደግሞ ስለ ንባብ ምንነት፣ ዓይነትና ስልት እንመለከታለን፤መልካም ንባብ!

የንባብ ምንነት ፡- “አንበበ፣አነበበ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን በጽሑፍ የሠፈረን መልእክት ማነብነብ፣መናገር ፣ ሆሄያትን መጥራት፣ መቁጠር፣ወዘተ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድም “ንባብ በቁሙ፤ ነገር፣ ቃል፣ ጩኸት” (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፮፻፲፱) በማለት ይፈቱታል፡፡ አለቃ ቃል፣ ጩኸት በማለት የገለጹት ድምፅን አውጥቶ የሚያነበንቡትና የሚጠሩት መሆኑን ለማመልከት ነው።

በሌላ አገላለጽ፡- ንባብ ማለት ከአንድ የተጻፈ ነገር ላይ መሠረታዊ የሆነውን ሐሳብ መረዳት፣ ነጥሎ ማውጣት፣የጸሓፊውን መልእክት መገንዘብ፣ወዘተ እንደሆነ የቋንቋ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡

ሥርዓተ ንባብ፡- በማንኛውም ቋንቋ የአነባበብ ሥርዓት አለ፡፡ በአነባበብ ሥርዓትም የተነሣ በድምፅም፣ በቃላትም፣ በመዋቅርም ወዘተ ተመሣሣይ ከሆኑ አደረጃጀቶች (መዋቅሮች) የተለያዩ መልእክቶችን እናገኛለን፡፡ የአነባበብ ሥርዓታችንን ባለማስተካከላችን በርካታ የትርጉም ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ ይህ እንደ ማንኛውም ቋንቋ ሲሆን በግእዝ ቋንቋ ደግሞ እጅግ ትኩረት የሚያሻው ነው፡፡ ለምሳሌ ቀደሳ በተነሽና በወዳቂ ሲነበብ የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ነው፡፡ ቀደሳ ወአክበራ እምኲሎን መዋዕል ሲል “ቀደሳ” በአነባበብ ሥርዓቱ ወድቆ ይነበብና ትርጉሙምከዕለታት ሁሉ ለይቶ አከበራት የሚል ይሆናል፡፡ ውእቶን አንስት ቀደሳ ፈጣሪሆን ሲል ደግሞ “ቀደሳ” በአነባበብ ሥርዓቱ ተነሥቶ ይነበብና ትርጉሙም እነዚያ ሴቶች ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ የሚል ይሆናል፡፡

የግእዝ ቋንቋ ሥርዓተ ንባብ፡- የግእዝ ቋንቋ ሥርዓተ ንባብን ስናነሣ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ልብ ሊባሉ ይገባል፡፡ የመጀመሪያው በግእዝ፣ በውርድና በቁም ንባብ የሚነበበው ነው፡፡

ግእዝ ንባብ፡- ይህ ንባብ ፊደል ከመለየት አልፎ ወደ ንባብ ሲሸጋገር የሚያነበው ሲሆን እያንዳንዱን ፊደል እየቆጠረ ዜማ ባለው መልክ የሚያነበው ነው፡፡

ውርድ ንባብ፡- ይህ ንባብ ኃዘንና እንጉርጉሮ በሚመስል ድምፅ የሚነበብ ነው፡፡ ይህ ንባብ ብዙ ጊዜ በዕለተ ስቅለት ከዳዊት መዝሙር የተውጣጡት ምንባባት ይነበቡበታል፡፡

ቁም ንባብ፡- ይህ ምንባብ መደበኛው የንባብ ስልት ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ግእዝ ንባብና ውርድ ንባብን ካጠናቀቀ በኋላ የሚያነበው ነው፡፡ በዚህ ንባብ ፊደላትን በትክክል ለይቶ ለራሱም ሆነ ለሰሚ በተገቢው ሁኔታ የሚያነብበት ነው፡፡

ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ የግእዝ ቋንቋ ንባብን ስናነሣ ከቃላቱ ድምፀት ማለትም መነሣት፣ መጣል፣ ተናቦ ከመነበብ፣ ጠብቆ ከመነበብ፣ ላልቶ ከመነበብ ወዘተ ጋር ተያይዞ የሚታይ ጉዳይ አለ፡፡ ይህን ሥርዓት በተመለከተ ሊቃውንት “የ፹፩ዱ መጻሕፍት ምንባባት ፬ ወገን ናቸው፡፡ እነርሱም፡- ተነሽ፣ ተጣይ፣ ሰያፍ ፣ወዳቂ ናቸው፡፡ ተነሽ በ፭ ፊደላት ይነገራል፤ ተጣይና ሰያፍ በ፩ በሳድስ ይነገራሉ፤ ወዳቂ በ፯ ፊደላት ይነገራል” በማለት ሁሉም የግእዝ ንባብ በእነዚህ ሥርዓተ ንባብ እንደሚካተት ያስረዳሉ፡፡

መምህር ኃይለ ኢየሱስ መንግሥት ደግሞ የልሳነ ግእዝ መማሪያ በሚል መጽሐፋቸው ለአንባቢ ግልጽ ለማድረግ እንዲመች ዐበይት ንባባትና ንኡሳን ንባባት በማለት ከፍለዋቸዋል፡፡

መምህር ዘርዐ ዳዊትም አራቱን ዐበይት ንባባት በዋናነት ከገለጹ በኋላ ንኡሳን የሚባሉትን
“ቀዋሚ ምድባቸው ከዚህ በላይ ከተመለከትናቸው ዐራቱ የንባብ ዐይነቶች ሳይወጣ በዐራቱ ንባባት ሥር ሆነው ልዩ ልዩ የንባብ ጠባይ ያላቸው ንኡሳን የንባብ ዐይነቶች ፍኖተ ንባብ ተብሏል” በማለት ዐበይትና ንኡሳን ተብሎ እንደሚከፈል ገልጸዋል፡፡ (መርኆ ሰዋስው ዘልሳነ ግእዝ ገጽ፴) ነገር ግን ንኡሳን ንባባት ከዐበይት ንባባት የማይወጡ በመሆናቸው ለአረዳድ ግልጽ እንዲሆን ነጣጥለን እንመለከታቸዋለን እንጂ የጎላ ልዩነት እንደማይፈጥር መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

እኛም በዚህ  ርእስ የመምህር ኃይለ ኢየሱስንና የመምህር ዘርዐ ዳዊትን አከፋፈል መሠረት አድርገን ዐበይት ንባባትና ንኡሳን ንባባት ብለን እንከፍላቸዋለን፡፡

ዐበይት ንባባት የሚባሉት አራት ሲሆኑ እነሱም ተነሽ፣ ተጣይ፣ ወዳቂና ሰያፍ ናቸው፡፡ ንኡሳን ንባባት ደግሞ ተናባቢ፣ኢተናባቢ፣ጠብቀው የሚነበቡ፣ላልተው የሚነበቡ፣በጥቅል የሚነበቡ፣ በተናጠል የሚነበቡ ወዘተ ናቸው፡፡

ዐበይት ንባባት፡- በዋናነት የግእዝ ቋንቋ ንባብ የሚከናወንባቸው ሲሆኑ የድምፅ ባሕርያቸውን፣ንባባቱ የሚጨርሱበትን ቀለማት ከምሳሌ ጋር ለማየት እንሞክራለን፡፡

ማስታወሻ፡- በዚህ ዐውድ ቀለማት ማለት ከግእዝ እስከ ሳብእ ንባባቱ የሚጨርሱበትን ሆሄያት ወይም ፊደላት ነው፡፡

ተነሽ፡– ይህ ንባብ ድምፅን በማንሣትና በማውጣት የሚነገር ሲሆን በአምስት ፊደላት ይነገራል፡፡ ፊደላቱም ግእዝ፣ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ሳብዕ ናቸው፡፡

ምሳሌ፡-

ተነሽ በግእዝ ሲነገር፡- “እግዚአብሔር ቆመ ውስተ ማኅበረ አማልክት፤እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ”  (መዝ.፹፩፥፩) እንዲል፡፡

ሐመ ወሞተ ወተቀብረ ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት፤ ታመመ፣ ሞተ ፣ተቀበረ፣ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ” (ጸሎተ ሃይማኖት) እንዲል፡፡

ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ፤ጾምን እንጹም ባልንጀራችንንም እንውደድ (ቅ/ ያሬድ) እንዲል፡፡

በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ (ዘፍ.፩፥፩) እንዲል፡፡

ተነሽ በካዕብ ሲነገር፡- ሐሙ ወርህቡ ወተመንደቡ፤ ታመሙ፣ተራቡ ተቸገሩ

“ትግሁ ወጸልዩ  ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱት፤ ወደ ፈተናም እንዳትገቡ ትግታችሁ ጸልዩ (ማቴ.፳፮፥፵፩) እንዲል፡፡

“ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ፤ ዕወቁም” (መዝ.፴፫፥፰) እንዲል፡፡

ተነሽ በሣልስ ሲነገር፡- ተንሥኢ ወንዒ ዖፈ ገነት፤ አንቺ የገነት ወፍ ተነሥተሸ ነዪ፡፡

“ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ፤ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሺ (መዝ.፵፬፥፲) እንዲል
፡፡

ግብዒ ነፍስየ ውስተ ዕረፍትኪ እስመ እግዚአብሔር ረዳኢኪ፤ ነፍሴ ሆይ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ እግዚአብሔር ረዳትሽ ነውና”(መዝ.፻፲፬፥፯) እንዲል።

ተነሽ በራብዕ ሲነገር፡- ወበእሑድ ሰንበት በጽባሕ አሌለያ ገይሰ ወሖራ ኀበ መቃብር ወወሰዳ ውእተ አፈዋተ ዘአስተዳለዋ ወካልዓትኒ አንስት ምስሌሆን፤ በእሑድ ሰንበትም በጥዋት ማልደው ገስግሰው ወደ መቃብር ሔዱ፤ ያን ያዘጋጁትን ሽቱ ወሰዱ ሌሎች ሴቶችም  አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ.፳፬፥፩) እንዲል፡፡

ተነሽ በሳብዕ ሲነገር፡- “እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ፤ አቤቱ ፍርድህን ለንጉሥ ስጠው (መዝ.፸፩፥፩) እንዲል፡፡

-ሑር እድዎ ለዮርዳኖስ፤ሂድ ዮርዳኖስን ተሻገር።

 “ወነሥእዎ፣ወአውጽእዎ፣ አፍኣ እምዐጸደ ወይን ወቀተልዎ፤ ይዘው ከወይኑ
ቦታም ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት(ማቴ.፳፩፥፴፱) እንዲል፡፡

-መራሕያን የቅርብ ብዙ ሴቶችና የሩቅ ብዙ ሴቶች (አንትን እና ውእቶን) በቀር  (አነ፣ንሕነ፣ አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ) ሁሉም ተነሽ ናቸው፡፡

-ተነሽ ከሰባቱ ፊደላት ውስጥ በሁለቱ በፍጹም አይነገርም፡፡ እነሱም ኃምስና ሳድስ ናቸው።

መልመጃ፡- ውድ አንባብያን የሚከተለውን ምንባብ ካነበባችሁ በኋላ በጥያቄው መሠረት መልሱ፡፡

ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ እምኀበ እግዚአብሔር ኀበ አሐቲ ሀገር ዘገሊላ እንተ ስማ ናዝሬት እንተ ተፍኅረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ ዘእምቤተ ዳዊት ወስማ ለይእቲ ድንግል ማርያም። ቦአ መልአክ ኀቤሃ ወይቤላ ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልእተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ ቡርክት አንቲ እምአንስት ወርእያ ደንገጸት እምቃሉ ወኀለየት ወትቤ እፎኑ ከመዝኑ እንጋ አምኃ ይትአምኁ። ወይቤላ መልአክ ኢትፍርሂ ማርያም እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምይዮ ስሞ ኢየሱስ። ውእቱ ዐቢይ ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል። ወይሁቦ እግዚአብሔር አምላክ መንበረ ዳዊት አቡሁ። ወይነግሥ ለቤተ ያዕቆብ ለዓለም ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ። ትቤሎ ማርያም ለመልአክ እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ እፎ ይከውነኒ። አውሥአ መልአክ ወይቤላ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኀይለ ልዑል ይጼልለኪ። ዘኒ ይትወለድ እምኔኪ ቅዱስ ውእቱ ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል። ወናሁ ኤልሳቤጥኒ እንተ እምአዝማድኪ ይእቲኒ ፀንሰት ወረከበት ወልደ በልኅቃቲሃ ወበርስዓቲሃ። ወናሁ ሳድስ ዝንቱ ወርኅ ለእንተ ይብልዋ መካን እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር። ትቤሎ ማርያም ለመልአክ ነየ አመቱ ለእግዚአ ኵሉ
ነየ አመቱ ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ።

በግእዝ የሚነገር ተነሽ……..

በካዕብ የሚነገር ተነሽ……..

በሣልስ የሚነገር ተነሽ……..

በራብዕ የሚነገር ተነሽ……..

በሳብእ የሚነገር ተነሽ……..

ውድ አንባብያን የመልመጃውን መልስና ሌሎችን የንባብ ዓይነቶች በሚቀጥሉት
ትምህርታችን  እናቀርባለን።