ሥላሴ በአብርሃም ቤት
ሐምሌ ፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት የገባበትና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት በመኾኑ በቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው፤
አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ኹሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አስቦ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ ወደ አብርሃም ቤት የሚሔዱ እንግዶችን አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱም ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው አድርጎ እየተናገረ እንግዳ ወደ ቤቱ እንዳይመጣ አደረገ፡፡ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ /ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ/፡፡
በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች ተመስሎ ከአብርሃም ቤት ገብቷል፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ አድባር ዛፍ ለአብርሃም ተገልጦለታል፡፡
አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና “አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ?” ብሎ ተማጸነ፡፡ እዚህ ላይ “ሦስት ሰዎች፣… ሊቀበላቸው፣… ወደ እነርሱ፣…” የሚሉት ሐረጋት ሦስትነቱን፤ “በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ?” የሚለው ዐረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ያመለክታል፡፡
በመቀጠልም አብርሃም “ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና” ሲላቸው እነርሱም “እንዳልህ አድርግ” ብለውታል፡፡
በዚህ ኃይለ ቃልም የእግዚአብሔርን ሦስትነት እንረዳለን፡፡ የዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን “ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ” ሲላቸው ደክሞናልና አዝለህ አስገባን ብለውታል፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ከቤቱ ገብተዋል፡፡
አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና “ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ” አላት፡፡ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ ሦስት መሥፈሪያ የሦስትነት፤ ዳቦው አንድ መኾኑ የአንድነት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሔዶ ወይፈን አምጥቶ አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡
ወይፈኑም ተነሥቶ “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ” ብሎ እግዚአብሔርን አመስገኗል፡፡ ነገር ግን ሥላሴ በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ተመግበዋል ተባለ እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ የሚስማማቸው ኾኖ አይደለም፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ሥላሴ ምግብ በሉ ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ እዚህ ላይ እግዚአብሔር “ሣራ ወዴት ናት?” ሲል መጠየቁ ያለችበት ጠፍቶበት ሳይኾን የሚነግራት ታላቅ የምሥራች እንዳለ ለማጠየቅ ነው፡፡ ይኸውም “አዳም ወዴት ነህ?” ከሚለው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው /ዘፍ.፫፥፱/፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አባታችን አዳምን “ወዴት ነህ?” ሲል የጠየቀው ያለበትን ዐላውቅ ብሎ ሳይኾን ቃል በቃል ሊያነጋግረውና “ከልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለውን ቃል ኪዳን ሊገባለት ነበር፡፡ እንደ አዳም ኹሉ ለሣራም ለጊዜው ይስሐቅን እንደምትወልድ፤ ለፍጻሜው ግን እግዚአብሔር ከአብርሃም ወገን ከምትኾን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ለብሶ እንደሚገለጥና ዓለምን እንደሚያድን ለመንገር አብርሃምን “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” ሲል ጠይቆታል፡፡
እግዚአብሔርም “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” ብሎ ለአብርሃም ነገረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና “ሲያረጁ አምባር ይዋጁ” እንዲሉ “እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን?” ብላ በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡
እግዚአብሔርም አብርሃምን “ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” አለው፡፡ ይህንን ኃይለ ቃልም እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት “ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?” ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ተናግሮታል /ሉቃ.፩፥፴፯/፡፡
ሣራም ስለፈራች “አልሳቅሁም” አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ እንደምትወልድ (ይስሐቅን) አብሥሯቸዋል፡፡ ይህም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋ ለብሼ በመጣሁ ጊዜ ሣራ ወንጌል ምእመናንን ታስገኛለች ማለትም ሐዲስ ኪዳን ተመሥርታ ክርስቲያኖችን ታፈራለች ሲለው ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደ ተረጐሙልን የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ ቀትር በኾነ ጊዜ ማለትም በስድስት ሰዓት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደ ገቡ ኹሉ፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዓመት ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዓመት እግዚአብሔር አብ ለአጽንዖ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመልበስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አድረዋል፡፡ “በስድስተኛው ወር ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እመቤታችን ተላከ፤” እንዳለ ቅዱስ ወንጌል /ሉቃ.፩፥፳፮/፡፡
“ስድስተኛው ወር” የሚለው ሐረግ በአንድ በኩል ጌታችን የተፀነሰበት ወርኃ መጋቢት ስድስተኛው ወር መኾኑንና (ከጥቅምት ጀምሮ በመቍጠር)፤ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት በተፀነሰ በስድስተኛው ወር ጌታችን መፀነሱን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዘመን ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዘመን ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን መላኩን ያመለክታል /ትርጓሜ ወንጌል/፡፡
በአብርሃም ቤት (በድንኳኑ) ውስጥ ወይፈኑ “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ” ብሎ እንዳመሰገነ ኹሉ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን በተወለደ ጊዜም ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጅ በአንድነት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይኹን፤ ሰላምም በምድር፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ” እያሉ እግዚአብሔርን አመስግነዋል /ሉቃ.፪፥፲፬/፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም የይስሐቅን መወለድና በሥጋ ማርያም መገለጡን ከነገረው በኋላ ተመልሶ ሔዷል፡፡ “ሔዷል” ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ኹሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡
/ምንጭ፡- የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ፣ ምዕ. ፲፰፥፩-፲፱/፡፡
ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ተገኝቶ የይስሐቅን መወለድና የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ከመናገሩ በተጨማሪ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ኹሉ በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱና ይህንን ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል የገባለት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በኀጢአታቸው የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው፤ አብርሃምም በአማላጅነት በፊቱ የቆመው በዛሬው ዕለት ነው፡፡
ከዚህ ታሪክ እግዚአብሔር እንደ አብርሃም ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ልማዳቸው አድርገው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤቱ ወደ ሰው ቤት ሲገባም የተዘጋ ማሕፀን እንደሚከፍትና ቤቱን በበረከት እንደሚሞላ፤ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገልጽ እንረዳለን፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ገብቶ ያደረገው ኹሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየታየ አምላክነቱን ለዘመናት እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከታሪኩ እንማራለን፡፡
ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት መገለጥም በአንድ ወቅት ብቻ የተፈጸመና “ነበር” እየተባለ የሚነገር ታሪክ ሳይኾን፣ ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ትምህርት ነው፡፡ ይህንንም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ለዘመናት በሚያደርገው ድንቅ ሥራና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡
ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመራቅ በተጨማሪ ቤት ላጡና ለተቸገሩ መራራትን፣ ደግነትን፣ ቀና አስተሳሰብን ገንዘብ ካደረግን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያድራል፡፡ አድሮም ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡ በአጠቃላይ የምንሻውን መልካም ነገር ኹሉ ይፈጽምልናል፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡