ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)
ታኅሣሥ ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
ሙት ላነሣውና ብዙ ተአምራትን ላደረገው ቅዱስ ጴጥሮስ አሁን ግን ይህን ዅሉ ጥበቃ የሚያደርግለት መልአኩ ነው፡፡ ይህ መልአክ የቅዱስ ጴጥሮስ ጠባቂ መልአክ እንደ ኾነ ብዙ ሊቃውንት በትርጓሜአቸው አስተምረዋል፡፡ በዚሁ ታሪክ ላይም፡- ‹‹ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መኾኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም፦ ‹አብደሻል› አሏት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ኾነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ ‹መልአኩ ነው› አሉ፤›› ተብሎ ተጠቅሷል /ቍ.፲፫-፲፭/፡፡ ከቤት ውስጥ የነበሩትም ‹‹ጴጥሮስ አይኾንም፤ መልአኩ ነው›› ያሏት ‹‹እርሱን ሊመስልሽ የሚችለው ጠባቂ መልአኩ ነው›› ማለታቸው ነበር፡፡ ይህም የኾነው በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ የጠባቂ መላእክት ጥበቃና መገለጥ በሰፊው ይታወቅ ስለ ነበረ ነው፡፡ በመጽሐፈ ጦቢት ላይም ቅዱስ ሩፋኤል ሰው መስሎ ለጦብያና ለቤተሰበው እንደዚሁም ለራጉኤልና ለቤተሰቡ ቀድሞ ጸሎታቸውን በማሳረግ፣ በኋላም ከፈተናቸው በማዳንና ሕይወታቸውን በመባረክ ተገልጦ አይተነዋል፡፡
እነዚህ ሁለት ታሪኮች የሚያስረዱን ጠባቂ መላእክት በድኅነታችን ውስጥ ትልቅ ስፋራ የሚሰጣቸውና በእርግጥም እነርሱ የሌሉበት ድኅነት የሌለ መኾኑን ነው፤ ልዩነቱ በአንዳንዶቹ ታሪኮች ላይ መገለጣቸው፣ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ተገልጠው ለሰው አለመታየታቸው ብቻ ነው፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፤›› በማለት የተናገረው ስለ ጠባቂ መላእክቶቻችን ነው /ማቴ.፲፰፥፲/፡፡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአችንና ፈተናችን ላይ ወደ እግዚአብሔር እያመለከቱ የሚጠብቁን፣ የሚያድኑን፣ የሚያስፈርዱልን ወይም የሚያስፈርዱብንም እነርሱ (ቅዱሳን መላእክት) ናቸውና፡፡ እንደናቡከደነፆር ያለውን አስፈርደውበት አውሬ አድርገው ሣር ያስግጡታል፡፡ እርሱ ራሱም ‹‹አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤›› ብሎ አሁንም እውነቱን አረጋግጧል /ዳን.፬፥፲፫/፡፡ እንደ ሄሮድስ ያለውን ደግሞ ‹‹ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፪፥፳፫/፣ በእግዚአብሔር አስፈርደው ይቀሥፉታል፡፡
እንደ ዳንኤል፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ጻድቁ ዮሴፍ፣ ሠለስቱ ደቂቅ ያሉትን ደግሞ በጠባቂነታቸው ያድኗቸዋል፡፡ ‹‹… እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፣ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፡፡ እውነት እንደ ጋሻ ይከብሃል። ከሌሊት ግርማ፣ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፣ በጨለማ ከሚሔድ ክፉ ነገር፣ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺሕ በቀኝህም ዐሥር ሺሕ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርቡም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፤ የኀጥአንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፤ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ዅሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል … ›› ተብሎ ተጽፏልና /መዝ.፺፥፩-፲፪/፡፡
ሠለስቱ ደቂቅንም ጠባቂ መላእክቶቻቸው የሚያድኗቸው ቢኾንም ‹‹ለናቡከደነፆር የታየው አንድ መልአክ ኾኖ ሳለ ሦስቱ መላእክት እንዳዳኗቸው ተደርጎ ለምን ይገለጻል?›› የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡ እንዲህ ያሉትን ምሥጢራት መረዳት የምንችለው በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉትን ተመሳሳይ ታሪኮችና ይህ የሚኾንበትን ምክንያት ስናውቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የጌታችንን ትንሣኤ አራቱም ወንጌላውያን መዝግበውልናል፤ አራቱም የመዘገቡበት መንገድ ተቃርኖ ባይኖረውም ልዩነት ግን አለው፡፡ ዐበይት ልዩነቶቹም ሦስት ነገሮች ላይ ይስተዋላሉ፤ ይኸውም የተገለጹት መላእክት፣ ወደ መቃብሩ የመጡት ሴቶች ማንነት እና ሴቶቹ የመጡበት ሰዓት በአዘጋገብ ይለያያል፡፡ ለርእሰ ጉዳያችን ቅርበት ባለው ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገን ጥቂት ምሳሌዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን፤
ቅዱስ ማቴዎስ፡- ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ኾነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ኾኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ ‹እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፡፡› የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሒዱና ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፡፡ በዚያም ታዩታላችሁ፤› ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው፤›› ሲል የገለጸውን /ማቴ.፳፰፥፪-፯/፣ ቅዱስ ማርቆስ፡- ‹‹ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ …›› በማለት መዝግቦታል /ማር.፲፮፥፭/፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ ፤›› ብሎ ጽፎታል /ሉቃ.፳፬፥፬/፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም ስለ ትንሣኤው ብዙ ነገር ካተተ በኋላ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች፤›› ሲል መዝግቦልናል /ዮሐ.፳፥፲፩-፲፪/፡፡ እነዚህን አገላለጾች ስናያቸው የአዘጋገብ ልዩነት ቢታይባቸውም ተቃርኖና የእውነታ ልዩነት ግን የላቸውም፡፡ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ስለ አንድ መልአክ ሴቶችን ማነጋገር ቢገልጹም ሌላ መልአክ እንዳልነበረ ግን አላመለከቱም፡፡ ወንጌላውያኑ ስለ አንድ መልአክ መታየት ይመዝግቡልን እንጂ የተናገሩት ግን ስለ ተለያዩ መላእክት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ከመቃብሩ ወጭ ድንጋዩን አንከባሎ ስለ ተቀመጠው መልአክ ዘግቦ ከመቃብሩ ውስጥ በቀኝ በኩል (በራስጌ ወይም በግርጌ) ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስላለው መልአክ መዝግቦ ከውጭ በኩል ስላለው ወይም የመቃብሩ ድንጋይ ላይ ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ሁለቱም ግን ‹‹ሌላ መልአክ አልነበረም›› በሚያሰኝ መንገድም አልገለጹልንም፡፡
ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ሁለቱም መላእክት መኖራቸውንና በግርጌና በራስጌ መኾናቸውን ገልጸውልናል፡፡ ስለዚህ ዅሉም ትክክል ናቸው ማለት ነው፡፡ የተለያዩና የማይቃረኑ የተባለውም ስለዚህ ነው፡፡ የተለያዩትስ ለምንድን ነው ስንል ደግሞ አንድ መሠረታዊ መልእክት እናገኛለን፤ ይኸውም ስለ መላእክቱ የተለያየ ዓይነት መገለጥ የገለጹት ለተለያዩ ሰዎች በትንንሽ የጊዜ ልዩነት የታየውን መገለጥና ለአንዳንዶችም በተቀራራቢ፣ ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የተገለጠውን ስለ መዘገቡ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ ለመግደላዊት ማርያም የተደረገውን የአንድ ጊዜ መገለጥ ብቻ ሲነግረን፣ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ለሌሎች ሴቶች የተደረገውን (ምክንያቱም ተመላልሰው ያዩም አንድ ጊዜም ያዩ አሉ፤ እንደዚሁም ብዙ ታሪኮች በውስጡ አሉና) እያሉ ከነሰዓቱ ስለ መዘገቡ እንጂ አንዱን ነጠላ ድርጊት ለያይተውና አሳሰተው መዝግበውት አይደለም፡፡ በዚህ መሠረት በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ክፍል ላይ እንዳየነው ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ተሰጥቷቸውና በጊዜው የነበረውን እውነተኛውን ትውፊት ከሐዋርያትና ከነበሩት ቅዱሳን ተምረው ከተረጐሙት መምህራን ሳይረዳ ልክ እንደነዚያ ርኩሳን እንደ ተባሉት እንስሳት ሳያመሰኳ ወይም እውነታውን ሳይቆነጥጥ ወይም እንደ ዓሣዎቹ ሐዋርያት የእምነት መከላከያ ቅርፊት (ጋሻ) እና ምሥጢራትን የሚረዳበት ክንፈ ጸጋ ሳይኖረው በአመክንዮ (ሎጂክ) ብቻ እረዳለሁም፣ አስረዳለሁም ቢል ይሳሳታል፡፡
ስለዚህ የሠለስቱ ደቂቅ ድኅነትን በተመለከተ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል፤ በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል፤ በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ደግሞ ሩፋኤል አዳናቸው ተብሎ መገለጹ ከላይ በወንጌል እንዳየነው ትውፊቱን ለያይቶ መዘገብ እንጂ ተቃራኒ ነገር አይደለም፡፡ በዚሁ መሠረት ሦስቱን ሕፃናት አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልንም ያዳኗቸው ጠባቂ መላእክቶቻቸው፤ እነዚህም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ልክ ሥላሴ ለአብርሃም በተገለጹለት መንገድ ሦስት ኾነው ከሦስቱ በስተጀርባ ቆመው መታየት ነበረባቸው ካላልን በስተቀር ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በተላለፈው ትውፊት ሦስቱ መላእክት የሦስቱ ሕፃናት ጠባቂ መላእክት ነበሩ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ሦስት ኾነው ይቅርና አንድም ሰው ቢኾን ሦስትና ከዚያ በላይ መላእክት ሊገኙ ይችላሉ፡፡
ዮናታን ወልደ ሳዖል ‹‹በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና፤›› እንዳለው /፩ኛሳሙ.፲፬፥፮/፣ በአንድም በብዙም መንገድ ማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድና ምሥጢር እንጂ የመላእክቱ የማነስና የመብዛት ጉዳይ የሚከራክር አይደለም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር እንኳን በመላእክት ዘንድ ቃል ኪዳን ተቀብለው በሚያማልዱ፣ በሚያድኑ ሰማዕታትና ቅዱሳንም ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸ መኾኑን ከተለያዩ ገድላት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ዓሣ አስጋሪ ሰው ‹‹መርምሕናም እርዳኝ?›› እያለ ቅዱስ መርምሕናምን ሲማጸን ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ መርምሕናም በአንድነት መጥተው ዓሣ አስጋሪውን እንደ ረዱት ‹‹ወበጊዜሃ መጽኡ ኅቡረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅዱስ መርምሕናም ተጽዒኖሙ ዲበ አፍራሲሆሙ ….›› ተብሎ በተአምረ ጊዮርጊስ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በዋናነት ሊገለጽ የሚችለው በገድለ መርምሕናም እንደ ኾነ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በቅዱሳን ዘንድ አንዱ ብቻ ነው እንጂ ሌሎቹ የሉም የሚያስብል ታሪክም ድርጊትም የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ልዩነት ያለ የሚመስለን መገለጦችን የምንረዳበት ሒደት አነስተኛ ሲኾን ብቻ ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍየዚህ ጽሑፍ ማጠቃለያም፡- ‹‹ይህ ከኾነ ታዲያ በሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ገብርኤል ጐልቶ ለምን ይወጣል? ዕለቱ (ታኅሣሥ ፲፱ ቀን) በዓል ኾኖ የሚከበረው ለቅዱስ ገብርኤል፤ በሥዕልም ላይ ‹አራተኛው ሰው› ተብሎ በናቡከደነፆር የተገለጸው የቅዱስ ገብርኤል ሥዕል የሚሣለው ለምንድን ነው?›› ለሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ይኾናል፡፡
ይህ የኾነበት ምክንያት ዝም ብሎ ወይም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥጋዌውን አስቀድሞ የገለጸው መላእክትንም በሰው አምሳል እንዲገለጹ በማድረግም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ለሙሴ መጀመሪያ የተገለጠለት በዚሁ መንገድ ነበረ፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾኽ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ፣ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዘፀ.፫፥፪/፡፡ ይህም ነገረ ተዋሕዶን ወይም ምሥጢረ ሥጋዌን የሚያስረዳ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመላእክት አምሳል ሲገልጥ ደግሞ ቅድሚያውን ስፍራ የሚይዘው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ምክንያቱም ገብርኤል ማለት ‹‹ቃለ እግዚአብሔር›› እንደዚሁም ‹‹ሰውና አምላክ›› ማለት ስለ ኾነ ነው፡፡ እመቤታችንን ሊያበሥር የተላከውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹አራተኛ ሰው አያለሁ›› እስኪል ድረስ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር ሥጋዌውን (ሰው መኾኑን) ገልጦ ያሳየው ከሦስቱ ሊቃነ መላእክት መካከል ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር በስሙም በተልእኮውም ቅዱስ ገብርኤል የተሸከመው በመኾኑ ነው፡፡
ስለዚህም ሦስቱም ሊቃነ መላእክት በጠባቂ መላእክትነታቸውና ረቂቃን ኃይላት በመኾናቸው በአዳኝነት ቢጠቀሱም እግዚአብሔር ሊገልጠው ለፈለገው ታላቅ ምሥጢር ተስማሚ የኾነውን መልአክ (ራሱ ገብርኤል መኾኑ ትርጕምና መልእክት ያለው ነውና) የነገሥታትን ልጅ በሚመስል ጐልማሳ አምሳል የንጉሠ ሰማይ ወምድር የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ምሳሌ ኾኖ እንዲገለጽለት አድርጓል፡፡ በዓሉ ለገብርኤል የተሰጠውና ሥዕሉ የእርሱ የኾነበት ምክንያትም ይኸው ምሥጢር ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር መሠረት አድርጋ በዓሉ በቅዱስ ገብርኤል ስም በታላቅ ሥርዓት እንዲከበር፣ በሥዕሉም ቅዱስ ገብርኤል ጐልቶ እንዲታይ በማድረግ ነገረ ሥጋዌውንም፣ የሕፃናቱን ተጋድሎም፣ የመላእክቱን ጠባቂነትም ስትገልጽበትና ስታስረዳበት ትኖራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምልዓት መረዳት ያለውም በእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት ትውፊትና ሥርዓተ አምልኮ ጸንታ በምትኖረው በዚህች ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ አማላጅነት፣ የሊቃነ መላእክቱ ጥበቃና የቅዱሳን ዅሉ ምልጃ አይለየን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡