ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል ሁለት

በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ

ታኅሣሥ ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንድንበላቸውና እንዳንበላቸው የታዘዝናቸው እንስሳት ከላይ በተገለጸው መንገድ እኛን የሚወክሉ መኾንና አለመኾናቸውን የሚያረጋግጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ወይም የሐዋርያዊው ትምህርት ትውፊት አለ ወይ? ከተባለ አዎን፤ በእርግጥ አለ፡፡ ሰፊውና ዋነኛው ምስክርም ቅዱስ ጴጥሮስ ያየው ራእይ ነው፡፡

በሐዋርያት ሥራ ‹‹… ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፡፡ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ዅሉ አራዊት፣ በምድርም የሚንቀሳቀሱ የሰማይ ወፎችም ነበሩበት፡፡ጴጥሮስ ሆይ፣ ተነሣና አርደህ ብላ!› የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ጴጥሮስ ግን ‹ጌታ ሆይ አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና› አለ፡፡  ደግሞም ሁለተኛ ‹እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው› የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ይህም ሦስት ጊዜ ኾነ፡፡ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፥፲-፲፮/፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ራእይ ደጋግሞ ካየ በኋላ ራእዩ በቀጥታ ምግብ ሳይኾን ምሥጢራዊ መልእክት እንዳለው ተረድቶ ‹‹ትርጕሙ ምን ይኾን?›› እያለ ሲያስብ ነበር፡፡

በኋላም መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን ገለጸለት፤ ‹‹… ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ መንፈስ እነሆ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፡፡ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሒድ አለው፤›› እንዲል /ቍ. ፲፱-፳/፡፡ ከታዘዘው ቦታ ከደረሰ በኋላም ‹‹አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ‹ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው› እንዳልል አሳየኝ፤›› በማለት ምስክርነቱን አስቀደመ /ቍ. ፳፯/፡፡ በዚህ ራእይ ያያቸው የማይበሉ እንስሳትም ምሳሌነታቸው ከእምነት ውጪ ላሉ ሰዎች እንደ ኾነ አረጋገጠ፡፡

ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ጊዜ ‹‹… መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከዅሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጧት፡፡ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ፤ ክፉውን ግን ወደ ውጪ ጣሉት፤›› በማለት /ማቴ.፲፫፥፵፯-፵፰/፣ መረብ የተባለችው ቤተ ክርሰቲያን ዅሉንም እንደምታጠምድ (ወደ እርሷ እንደምታቀርብ)፤ የዓሣዎቹ ሐዋርያትን ትምህርታቸውን ንቀው ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው የሚወድቁት ደግሞ መናፍቃንና ኀጥአንን እንደሚወክሉ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡

ለመሥዋዕት የሚቀርቡት እንስሳትም የሰማዕታትና የቅዱሳን ምሳሌዎች መኾናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?›› በሚለው መዝሙሩ መምለክያነ እግዚአብሔር እስራኤልን በጎች ብሎ ጠርቷቸዋል /መዝ.፸፬፥፩/፡፡  ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፤ ወደ አሕዛብም በተንኸን፤›› ዳግመኛም ‹‹ስለ አንተ ዅልጊዜም ተገድለናል፡፡ እንደሚታረዱም በጎች ኾነናል›› በማለት ሰማዕትነታቸውና ተጋድሏቸው እንደ መሥዋዕት በጎች እንደሚያስቈጥራቸው ተናግሯል /መዝ.፵፬፥፲፩-፳፪/፡፡  ይህ ቃል በእርግጥ ስለ ሰማዕታት የተነገረ መኾኑንም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ስለ አንተ ቀኑን ዅሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን፤›› በማለት አረጋግጦልናል /ሮሜ.፰፥፴፮/፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰበትን መከራና ሰማዕትነቱን ሲገልጽ ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፤ የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል፤›› በማለት ሕይወቱን በመሥዋዕት መስሎ መናገሩም /፪ኛጢሞ.፬፥፮/፣ ጥንቱንም እነዚህ የመሥዋዕት እንስሳት የቅዱሳን፣ የንጹሐን ምእመናን፤ ርኩሳን የተባሉት ደግሞ የማያምኑትና የመናፍቃን ምሳሌዎች መኾናቸውን አመላካች ነው፡፡ ጌታችንም በነቢዩ በሕዝቅኤል ላይ አድሮ ‹‹‹እናንተም በጎቼ፣ የማሰማርያዬ በጎች ሰዎች ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ› ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤›› በማለት በተናገረው ቃል /ሕዝ.፴፬፥፴፩/ እስራኤልን ‹‹በጎቼ›› ብሏቸዋል፡፡ ነቢያትም ዅሉ ይህን ቃል ደጋግመው ተናግረውታል፡፡ ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው ቃሉን አጽድቆታል፡፡ በመጨረሻው ዕለትም ‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፡፡ ‹እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ› የሚል ተጽፎአልና፤›› /ማቴ.፳፮፥፴፩/ ያላቸው ቅዱሳኑ፣ ንጹሐኑ የመሥዋዕቱ እንስሳት የሚያመሰኩትና ቆንጥጦ ለመርገጥ የሚያስችል ስንጥቅ ሰኮና ያላቸው እነርሱ በመኾናቸው ነው፡፡

ስለዚህ በዘመነ ኦሪት ከሁለቱም ወገን የሚመደቡ እንስሳትን የሚያርዱና የሚበሉ ሰዎች የነበሩ ቢኾንም እግዚአብሔርና የእርሱ የኾኑት የሚቀበሉት ግን ከንጹሐን ወገን የኾኑትን እንስሳት ብቻ ነበር፡፡ ይህም ምሳሌ ስለ ኾነ ዛሬም ከሁለቱም ወገን የሚመደብ አለ፤ እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር የኾኑት የሚቀበሉትም በንጹሐን እንስሳት ከተመሰሉት ከሐዋርያት፣ ከሰማዕታት፣ ከቅዱሳን ሊቃውንትና ከእውነተኞች መምህራን የሚገኘውን ትምህርት ብቻ ነው፡፡ ቀደም ብለን እንደ ገለጽነው እነዚህ ቅዱሳን በበግና በመሳሰሉት የተመሰሉት ሰኮናቸው የተሰነጠቀ እንስሳት በትክክል መሬትን ጨብጦ ወይም ቆንጥጦ መርገጥ እንደሚችሉት እንደዚሁ ሃይማኖታቸውን በሥራ ገልጠው ከእነርሱ የሚጠበቀውን መሥዋዕትነት ወይም ሰማዕትነት በገቢር ገልጸው የሚኖሩ በመኾናቸው ነው፡፡ በባሕር ውስጥ በሚኖረው ቅርፊትና ክንፍ ባለው ዓሣ የተመሰሉትም በዚህ እንደ ባሕር በሚነዋወጥ ዓለም ውስጥ እየኖሩ ወደ ከፍተኛው ጸጋና ክብር ብቻ ሳይኾን ወደ ላይኛው መለኮታዊ ምሥጢር ብቅ የሚሉበት ክንፈ ጸጋ፣ የዚህን ዓለም አለማመን፣ ክሕደትና ኑፋቄ ድል የሚነሡበት በቅርፊት የተመሰለ የእምነት ጋሻና ጦር ስላላቸው ነው፡፡

እኛንም ‹‹በዅሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤›› ሲሉ አስተምረውናልና /ኤፌ.፮፥፲፮/፣ የእምነት ጋሻችንን እናነሣለን፡፡ ደግሞም  ‹‹የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤›› /፪ኛቆሮ.፲፥፬/ ተብሎ እንደ ተጻፈው መሣሪያችንም ሥጋዊ የጦር ትጥቅ ሳይኾን የዲያብሎስን የተንኮልና የክሕደት ምሽጎች ለመስበር የበረታው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ከተባሉት፤ ያለ መከላከያ ኾነው ራሳቸውን አስማርከው እኛንም ወደ እነርሱ ጥርጥርና ክሕደት ሊስቡ ወደሚሮጡት፤ ዳግመኛም የእግዚአብሔርን ቃል ምሥጢራት ወደማያመላልሱትና ሰኮና በተባለ ክሳደ ልቡናቸው መሬት ገቢርን ወደማይጨብጡት እንዳንጠጋ ‹‹እነርሱ ዅልጊዜም በነፍስ ርኩሳን ናቸው፤›› ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ ‹‹ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣቸው ማን ነው?›› ለሚለውን ጥያቄ ምላሽ የምንሰጠውም ‹‹ያመሰኳሉ›› የተባሉ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቃሉን እያመላለሱ መርምረው፣ ምሥጢሩን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተረድተው እንደ ጻፉልን በማመንና በዚሁ (በእነርሱ) መንፈስ ይኾናል ማለት ነው፡፡

በእርግጥ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው?

መጀመሪያውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣቸው ‹‹ገብርኤል ነው›› አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም፡- ‹ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን?› ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፡- ‹ንጉሥ ሆይ እውነት ነው› ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፡- ‹እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ፤›› /ዳን.፫፥፳፬-፳፭/፡፡ በዚህ አገላለጽ መሠረት አራተኛውን ሰው ያየው ንጉሡ ናቡከደነፆር ሲኾን የጨመረበት ቃል ቢኖር ‹‹አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል›› የሚለው ነው፡፡

ለመኾኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየው? ሌሎቹ ለምን አላዩትም? የጥያቄው ቍልፍ ምሥጢር ያለው ከዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት የጣላቸው ሕዝቡን ለራሱ ምስል በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ አስቦ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አማክት አድርጎ የሚቈጥር ከኾነ የሚያየውን አራተኛውን  ሰው ‹‹የእኛን ልጅ ይመስላል›› ወይም ‹‹እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹የአማልክትን ልጅ ይመስላል›› ያለበት ምሥጢር ምንድን ነው? ንጉሡ ይህን ያለበት ምክንያት እነርሱ ሳያዩት ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር አራተኛ ሰው ወደ እሳቱ ገብቶ ሳይኾን ነገሩ የወልደ እግዚአብሔርን በሥጋ መገለጥ የሚያመላክት ምሥጢር ሳለለው ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን ከተገለጹት ታላላቅ ሦስት የእግዚአብሔር መገለጦች ውስጥ ሦስተኛው ይህ የሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ነው፡፡ አንደኛው መገለጥ በመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር እግዚአብሔር ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል የተገለጠው መገለጥ ሲኾን /ዘፍ.፲፰/፣ ሁለተኛውም እግዚአብሔር ለአባታችን ለያዕቆብ በጐልማሳ አምሳል ተገልጾ ሲታገለው ያደረበት ታሪክና ያዕቆብም መጀመሪያ ‹‹ካልባረከኝ አልለቅህም›› ብሎ ከተባረከ በኋላ ‹‹‹እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፤ ሰውነቴም ድና ቀረች› ሲል የዚያን ቦታ ስም ‹ጵንኤል› ብሎ ጠራው፤›› ያሰኘው መገለጥ ነው /ዘፍ.፴፪፥፳፭-፴፪/፡፡ ሦስተኛው መገለጥ ደግሞ አላዊው የባቢሎን ንጉሥ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እቶነ እሳት በጣለበት ወቅት ያደረገው መገለጥ ነው፡፡

ሦስቱም መገለጦች የሚያመሳስሏቸው ሁለት ጠባይዓት አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው በሦስቱም መንገድ እግዚአብሔር በሰው መልክና አምሳል መገለጡ ሲኾን ሁለተኛውና ዋነኛው ቃለ እግዚአብሔር በሥጋዌ (ሰው በመኾን) ተገልጦ ለሰው ፍጹም ድኅነት የሚሰጥ መኾኑን አስቀድሞ በምሳሌ መግለጥ ነው፡፡ መሠረታዊ መልእክቱ ደግሞ አምላክ ሰው ከኾነ በኋላ የሚያድነው የተስፋውን ዘር እስራኤልን ብቻ ሳይኾን አሕዛብንም ጭምር መኾኑን ለማሳየትና አሕዛብም የሥጋዌው ነገር ቀድሞ የተገለጠው ለእስራኤል ብቻ ስለ ኾነ እኛ ልናምንበት አይገባም እንዳይሉ ለዚህ ደንዳናና ጨካኝ ናቡከደነፆርም ጭምር ተገለጠለት፡፡

የነነዌ ሰዎች ታሪክም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኾኖ የተቀመጠውና እግዚአብሔር ለአሕዛብም ድኅነት ይፈጽም እንደ ነበር የተመዘገበው እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይኾን የዅሉም አምላክ መኾኑን ራሱ ብሉይ ኪዳንም ምስክር እንዲኾን ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ታሪኮችና ምሳሌዎችም በብዛት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በሠለስቱ ደቂቅ ድኅነት ውስጥ የታየው መገለጠጥ ዋነኛው ምሥጢርና መልእክትም የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና አዳኝነት፤ እንደዚሁም እንደ ሠለስቱ ደቂቅ እሳትና ስለት፣ ሰይፍና ጐራዴ፤ እስራትና ግርፋት የሚቀበሉ ሰማዕታትን ዅሉ የሚያድናቸው እርሱ መኾኑን መግለጽ ነው፡፡ ታዲያ ዋነኛው መልእክቱና ምሥጢሩ ይህ ከኾነ ገብርኤልም ኾነ ሌሎቹ መላእክት ለምን ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት አወጡ (አዳኑ) ይባላሉ? በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት መሠረት ለሰዎች ከጊዜያዊና ምድራዊ አደጋና ሰዎች ከሚያመጡባቸው መከራ ድኅነት ሲደረግላቸው ድኅነታቸውን የሚፈጽሙላቸው ቅዱሳን መላእክት ማለትም ጠባቂ መላእክቶቻቸው ናቸው፡፡

ይህም ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በግልጽ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምሥጢር ቢገለጽም የእግዚአብሔር መላእክት ከሚጠብቋቸው ሰዎች ተለይተው አያውቁም፡፡ ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ያዕቆብን ያስገደለው ሄሮድስ ቅዱስ ጴጥሮስንም ለመግደል ባሰረው ጊዜ በዚያ ወቅት እንዲሞት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ መልአኩ እንዲያድነው አድርጓል፡፡ ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ቀረበ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፡፡ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና ‹ፈጥነህ ተነሣ› አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም፡- ‹ታጠቅና ጫማህን አግባ› አለው፤ እንዲሁም አደረገ። ‹ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ› አለው። ወጥቶም ተከተለው፡፡ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ኾነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፡፡ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ‹ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ዅሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ› አለ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ሐዋ.፲፪፥፯፲፩/፡፡

ይቆየን