ምኵራብ

መምህር አብርሃም በዕውቀቱ
መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ኢየሩሳሌም በሚገኘው መቅደስ አይሁድ ስግደትና መሥዋዕታቸውን የሚያቀርቡት እንደሆነ ቢያምኑም በየተበተኑበት ቦታ ምኵራብ (ሰቀላ መሰል አዳራሽ፣ የአይሁድ የጸሎት ቤት) እየሠሩ ትምህርተ ኦሪትን በመማር ሃይማኖታቸውን ያፀኑ ነበር። (ዮሐ.፬፥፳) በብሉይ ኪዳን ዘመን የእነርሱ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው ናቡከደነጾር የአይሁዳውያንን ቤተ መቅደሱን አፍርሶ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን ካፈለሰ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎትና ለማኅበረተኛነት ልዩ ቤት ሊሠሩ እንደጀመሩ ይገልጻል፡፡

አይሁድ በምኲራቦቻቸው የሕግንና የነቢያትን መጻሕፍት (የብራና ጥቅሎች) በአንድ ሣጥን ውስጥ ያስቀምጣሉ፡፡ በመሆኑ የጸሎት ሥፍራዎቻቸውን ለትምህርትና ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በሕገ ኦሪት የአይሁዳውያን ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ሕግ ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ተግባራት ከሚሄዱበትም ይልቅ በዓመት አንዴ የሚቀርበውን መሥዋዕትና መብዓ ለመስጠት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሕግ ሊፈጽም ወደ ቤተ መቅደስ ይሔድ ነበር፡፡ ‹‹ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንዳስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ›› እንዲል (ሉቃ.፪፥፵፪) ‹‹ዕለት ዕለትም በቤተ መቅደስ (ምኵራብ) ያስተምር ነበር፡፡›› (ሉቃ.፲፱፥፵፯)

በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት ‹‹ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ፤ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ›› እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኵራብ ማስተማሩን እያነሣ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኵራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ስለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ስለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ነው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፲፪)

ጌታችን በምኵራብ እየተገኘ ሲያስተምር ትምህርቱን ሕግን አውቆ እንደሚያሳውቅ ሠራዔ ሕግ ስለሆነ በሙሉ ሥልጣንና ኃይል ያስተምር ነበር፡፡ ‹‹ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕትአነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለየሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው)፤ ወደ ምኵራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤ እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ። የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

ቅዱስ ዳዊትም አስቀድሞ በተናረው ትንቢት መሠረት ጌታ ለቤተመቅደሱ ቀንቶ አጽድቶት ነበር፡፡ ‹‹እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፤ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡›› (መዝ.፷፰፥፱)