ምኵራብ
ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
የካቲት ፳፬፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዐቢይን ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምኵራብ ብላ ትጠራዋለች። ዓመት እስከ ዓመት ያለውን ይትበሃል በያዘው ድጓ ዐቢይ ጾም በገባ በሦስተኛው ሳምንት መጀመሪያው ቀን ቅድስት በሆነች በሰንበት በሚዘመረው በጾመ ድጓው ክፍል “ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ” ሲል እናገኘዋለን። “መሀረ ቃለ ሃይማኖት እንዘ ይብል፤ እንዲህ እያለ የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው፤ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤ ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤” ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል” እያለ አስተማራቸው። እነርሱም የቃሉን ግርማና የአነጋገሩን ጣዕም አደነቁ ይላል። (ዮሐ.፪፥፲፮)
በዕለቱ ወንጌል ደግሞ “በመቅደስም በሬዎችና በጎችን ርግቦችን የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ። የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፤ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ። ርግብ ሻጮችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው” ይላል። (ዮሐ.፪፥፲፪)
ቅዱስ ያሬድ “ይህን የወንጌል ክፍል ይዞ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖትንም ቃል አስተማራቸው” ይላል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብቶ በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ በጅራፍ እየገረፈ እንደ አወጣቸው ነው የሚናገር። ምን ነው ተለያዩ ቢሉ አልተለያዩም። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በዚህ የወንጌል ክፍል ባስተማረው ትምህርት ላይ እንዲህ ይላል። “አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ መቅደሱን ገበያ አድርገውት ባገኛቸው ጊዜ ከወትሮው በተለየ በታላቅ ቁጣ ገሠፃቸው፤ ገሥፃጿቸውም አልበቃውም፤ በጅራፍ አበጅቶ እየገረፈ አወጣቸው እንጂ፤ ነገር ግን ከዚህ በፊት አንተ ሳምራዊ ጋኔን አለብህ ሲሉት ምንም አልተናገራቸውም ነበር ለምን? ሊል ይችላል። በእርግጥም እውነት ነው። እነርሱም ቢሆን ያን ሁሉ ሲናገራቸው ከወትሮው በተለየ ዝም አሉ እንጂ ክፉ ኃይለ ቃል አልተናገሩም። አይሁድ ለራሳቸው ጥቅም ሲሆን ይናገሩታል፤ ክርስቶስ ግን ለእነርሱ ጥቅም ሲሆን ይናገራቸዋል። ለዚህም ማሳያው “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት” ባላቸው ጊዜ ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክት ታሳየናለህ አሉት” ይላል። (ዮሐ ፪፥፲፰)
እውነት ነው! ክርስቶስ ምንም እንኳን በተግሣፅና በጅራፍ ቢያስወጣቸውም ከፍቅሩ የተነሣ ነውና የሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሲያስተምር አንዳንዴ ጠንከር ያሉ ተግሣፆችን አንዳንዴም ስድብ የሚመስሉ ኃይለ ቃላትን ሲናገር እናገኘዋለን። በዚህ ሁሉ ግን ፍጹም የሆነ ፍቅር አለበት። ሁሉንም ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል አድርጎታልና። ሰው በፈተና ውስጥ ሲያልፍ ለተሻለ ክብር ይደርሳል። በውድቀት ምክንያት ስንገሠፅ ከፍ ወዳለ ክብር እንድንደርስ ያደርጋል።
ክርስቲያኖች ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን የብሔር፣ የቋንቋ፣ የዘር፣ የሥልጣን፣ መነገጃ ለማድረግ የሚጥሩ አሉና እንደ ቅዱስ ዳዊት ““የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና ነፍሴን በጾም አስመረርኋት” እንበል፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን እንጹም፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን እንቅና። (መዝ ፷፱፥፲) በስሙ ክርስቲያን ተብለን የተጠራን ሁላችን መንፈሳዊ ቅናት ይኑረን። ቅዱስ ያሬድ “መዓዛሆሙ ለቅዱሳን፣ አንቀጸ መድኃኒት፤ የቅዱሳን መዓዛ የመዳኃኒት በር እያለ የሚጠራትን ቤተ ክርስቲያን ሻጮችና ለዋጮች የወንበዴዎች ዋሻ እንዳያደርጓት ዘወትር ወደ በሯ እንገሥግሥ፤ (ጾመ ድጓ) በመዓዛዋ እንርካ በመድኃኒትነቷ እንፈወስ። ጌታችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ውበት የሚሸፍኑትን በጅራፍ እየገረፈ አስወጣቸው።
ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው “ሀገረ ክርስቶስ አዳም ወሠናይት ከመ ፀሐይ ብርህት ወከመ መርዓት ሥርጉት ይበውኡ ውስቴታ ደቂቀ እግዚአብሔር ያዕርፉ ላዕሌሃ፤ እንደ ፀሐይ የምታበራ፣ እንደሙሽራ የተሸለመች፣ የእግዚአብሔር ልጆች በውስጧ ገብተው የሚያርፉባት፣ እጅግ ያማረች የክርስቶስ ሀገር እያለ ስለሚናገርላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውበት ትንሽ ሐሳብ እናንሳ።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውብ ነች። ውበት ልዩ ልዩ ነው። ሥላሴ ይህን ዓለም ውብ አድርገው ፈጥረውታልና። የሰው ልጅ በተፈጥሮ ውበት ይማረካል። ከሁሉም ደግሞ ውብ የሁነው የቅድስት ቤተክርስቲያን ውበት፡ ውበት ራሱ የሚለካበት ነው። ሰላማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ በማይናወጽ ዓለት ላይ የመሠረታት በከበረ ደሙ ያተማት ናት። የክርስቶስን መዓዛ የምናሸትባት ክርስቶስን ራሱን የምናይባት ቅድስት ልዩ የሆነች መንግሥት ናት። የሰው ልጅ በዓለም ሳለ ለዓይኑ መልካምን ነገር ማየት ለጆሮው መልካምን ነገር መስማት ጊዜያዊ ቢሆንም ሰላም እንዲሰማው ያደርገዋል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን እውነተኛውን ምንጩ የማይነጥፈውን ዘለዓለማዊውን ሰላም ትሰጣለች። በዓለም ምናምንቴ ምክንያት ያጣናውን ሰላም ዕለት ዕለት ትለግሠናለች። የእውነተኛ ዕረፍት ምንጭ ናት። ዓለምን የሚማርክ ኃያል የሆነ ውበት አላት። ሰሎሞን በመኃልየ መኃልይ “ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች ዓላማ ይዛ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት የምታስፈራ ማን ናት” ይላታል። (መኃ.፮፥፲) ጨረቃ ብርሃኗን ከፀሐይ የምታገኝ ቢሆንም ግርማና ውበት ተሰጧታልና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጨረቃ ተመሰለች። (ኢዮ.፴፩፥፳፮) ክርስቶስ ይህን ውበት የሚያደበዝዙትን እጅግ ይቃወማል።
ጌታችን ከወትሮው በተለየ ቤተ መቅደሱን ገበያ አድርገውት ባገኛቸው ጊዜ የተቆጣ ለዚህ ነው። ሊወግሩት ደንጋይ ሲያነሱ ያላሳየውን መቆጣት ምራቃቸውን ሲተፉበት ያላሳየውን ቅጣት በከበረ ደሙ ለሚያትማት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ለሚወልዳቸው ልጆቹ መጠጊያ ለምትሆን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅናት ተናገራቸው፤ በጅራፍም እየገረፈ አወጣቸው። ለክብሯ አይመጥናትምና። ገበያ አንድ ቀን ማትረፍ አንድ ቀን መክሰር አለበት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ዘወትር ማትረፍ ነው። ብንኖርም ብንሞትም ትርፍ ነው። ገበያ አንድ ቀን ርካታ አንድ ቀን ርኃብ ያለበት ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ለዘለዓለም የማያስርብ ለዘለዓለም የማያስጠማ መብል መጠጥ ያለባት ናት። ገበያ ሽንገላ አለበት፤ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ሁል ጊዜ ጽድቅ አለ። ገበያ ሥስት አለ፤ ራስ ወዳድነት፣ ፍቅረ ንዋይ አለበት። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን ፍጹም የሆነ ሕግ ፍቅር፣ ጠላትን መውድድ ያለባት ናት። በሰዓቱ ክርስቶስ “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ” ብሎ የገሠፃቸውና ወደ ምኩራብ በገባ ጊዜ በዚያው ስፍራ ያገኛቸውን አይሁድን ለቤተ መቅደሱ ተቆርቋሪ የሚመስሉትን ከእነርሱ በላይ ለእግዚአብሔር ቅርብ እንደሌለ አድርገው የሚያስቡትን ነበር እንጂ በዚያ ስፍራ ያልተገኙትን አልነበረም።
ስለዚህ ዛሬም ክርስቶስ ይህን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ውበት በገበያ የሚሸፍኑትን በጅራፍ እየገረፈ ያስወጣቸዋል። እጅግም ይቀናልና። ይህን የውበት ሁሉ መለኪያ የሆነውን ውበት ተማርከንበት ሳናደበዝዘው ዕለት ዕለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ውበት እየገለጥን ለመኖር ያብቃን። እንዲሁም ክርስቶስ በክርስቲያኖች አካል በደሙ በገዛው ቤተ መቅደስ ይቀናል። በአርአያውና በአምሳሉ በፈጠረው ክቡር በሆነው በሰው ልጅ ያለ ዋጋ እንደተገኘ እቃ በዓለም ገበያ በረከሰ ዋጋ ሲቸረቸር ክርስቶስ እጅግ ይቀናል።
ቅዱስ ዳዊት “ለወንድሞች እንደ ሌላ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው፤ የቤትህ ቅናት በልቶኛልና የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና” እንዳለ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሁሉ ሲል ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሁኖአል። (መዝ.፷፱፥፰) ክብር ይግባውና ሩቅ ብእሲ ተብሏል። ጋኔን አለብህ ተብሎ ተሰድቧል፤ ምራቅ ተተፍቶበታል፤ ማነው የመታህ እስኪ እወቀው እየተባለ ተዘብቶበታል። ቅዱስ ዳዊትም አስቀድሞ ይህን ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሁሉ ድኅነት ሲል የሚቀበለውን መከራና መዘባበት በመመልከት ለሥዕለ ፀሐይ ስገድ መሥዋዕተ እሪያ ብላ ብለው በተገዳደሩት ጊዜ “የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና” አለ። (መዝ.፷፱፥፱) ስለዚህም ክርስቶስ ይህን ያክል ለሚቀናለት ቤተመቅደሱ እንደ እሳት በሚያቃጥል ቅናት እየተቃጠለ ይህን የሃይማኖት ቃል አስተማረ።
ምንጭ፦ ጾመ ድጓ ዘምኩራብ ዘሰንበት፣ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል” አንድምታ ትርጓሜ፣ መዝሙረ ዳዊት አንድምታ