ማእከለ ክረምት
ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ
ዘመነ ክረምት የሚጋመስበት ወቅት ማዕከለ ክረምት ይባላል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት ንኡስ ክፍል ይገኛሉ፤ እነርሱም ዕጒለ ቋዓት እና ደሰያት / ዐይነ ኩሉ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህም ወቅት ከነሐሴ ፲፩ – ፳፯ ቀን ድረስ ያለውን ፲፯ ዕለታት ያካትታል፡፡ ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ወቅትም ነው፡፡
ዕጒለ ቋዓት- የሚለው ቃል ቁራን ያመለክታል፤ ቁራ ከእንቁላሉ ተቀፍቅፎ ሲወጣ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወጣል፡፡ እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሹታል፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እያደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ (ኢዮ. ፴፰፥፵፩) «ለቁራ መብል የሚሰጠው ማን ነው?›› ብሎ እንደገለጸው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አባቱና እናቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ ቁራ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር በክንፍ ከሚበሩ አዕዋፍ ነው፡፡ ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅራኄ ለተመላው ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተክርስቲያን ዕጒለ ቋዓት በማለት ታስታውሳለች፡፡
ደሰያት – የሚለው ቃል በውኃ የተከበቡ ቦታዎችን ያመለክታል፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጣቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት፤ አራዊትና አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን በዚህ ያመሰግኑታል፡፡ ደሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፤ አንዲት ደሴት በውስጧ ብዙ ፍጥረታትን ትይዛለች፡፡ ከደሴት የተጠጉ ድኅነትን እንደሚያገኙ ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያን የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡
በዚህ ዕጒለ ቋዓትና ደሰያት ወቅት ክፍለ ክረምቱ እየተገባደደ፣ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዝ ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችና አሞራዎች ድምጻቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡
‹‹ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፣ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት›› እንዳለው፤ ዝናብ ይቀንሳል፣ ምድሪቱም መቀዝቀዝና መጠንከር የምትጀምርበት ወቅት ነው፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ወቅት እግዚአብሔር አምላክ ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ምሕረቱም ለዘላለም የሆነውን የሰማይን አምላክ መሆኑንና ፍጥረታትም ሁሉ እርሱን ተስፋ የሚያደርጉ መሆናቸውን የሚገልጡ መዝሙራት፣ ትምህርት፣ ስብከት ይሰጣል፣ ይነበባል፡፡ (መዝ.፻፵፬፥፲፮-፲፯)
በተጨማሪ በዚህ በማእከለ ክረምት ‹‹ዕረፍተ አበው›› ከነሐሴ ፳፯ እስከ ነሐሴ ፳፱ ድረስ ባለው ጊዜ ይታሰባል፡፡ ከ፳፪ቱ አርዕስተ አበው አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ የቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ የአብርሃም ታዛዥነት እና የይስሐቅ ቤዛነት ይታሰባል፡፡ የተቀበሉትም ቃልኪዳን ‹‹ወተዘከረ ሣህሉ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም መመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያረኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እምሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍሰ ርኅብተ›› በማለት ይዘመራል፡፡