ማኅቶት!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፭፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በበደል ምክንያት የገባውን ከጥልቅ፣
በኃጢአት ጎስቁሎ የራቀውን ከጽድቅ፡፡
ዳግም ሊመልሰው ከከበረው ሥፍራ፣
ጽልመት ርቆለት ሕይወቱ እንዲበራ፡፡
ከሰማያት ወርዶ ከልዑል መንበሩ፣
ቃላት የማይገልጹት ስቦት የአዳም ፍቅሩ፡፡

ሕመሙን ታሞለት ሞቶ ለእርሱ ብሎ፣
ነጻነትን ሰጠው ከዲያብሎስ ጉያ አወጣው ነጥሎ፡፡
ሞት መውጊያው ተሰብሮ፣ በሕይወት ተበሥሮ፣
የሞት ሞት ዐዋጅን በምሕረቱ ሸሮ፡፡

ለጨለመው ሕይወት ሆኖለት ማኅቶት፣
በብርሃኑ ጸዳል ሰውሮት ከጽልመት ፡፡
የክህነትን ሥልጣን፣ ሥጋውና ደሙን ፣ የንስሐን መንገድ፣
በፍቅሩ ለግሶ መዳንን ለሚወድ፡፡

  • ያናገረው ትንቢት የሰጠው ምሳሌ፣ በአማን ተፈጽሞ፣
    በይባቤ መልአክ በዕልልታው ደግሞ፣
    እያለ ከፍ ከፍ ረቆ ያይደለ! እያዩት በርቀት፣
    ዐረገ ወደ ላይ ወደ ክቡር መንበሩ ሰማየ ሰማያት፡፡
  • ተሰማ መለከት ዝማሬ ዕልልታ ፣
    የዳዊት ትንቢቱ ፍጻሜ አግኝታ፡፡
    ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ ነግሮ፣
    ቃሉም እስኪፈጸም ሰጥቷቸው ቀጠሮ፡፡

ዐረገ በክብሩ ዐረገ ወደ ሰማይ፣
የነገሥታት ንጉሥ ክርስቶስ ኤልሻዳይ፡፡
የመስቀሉን ፍቅር በልባችን ስሎ፣
የመከራን ቀንበር ከእኛ ላይ አቅሎ፡፡
ከኢየሩሳሌም ጸንተን ከተገኘን፣
ቃል ኪዳን ገብቶልን ጸጋውን ሊሰጠን፡፡

ዐረገ በክብሩ ዐረገ ወደ ሰማይ፣
የነገሥታት ንጉሥ ክርስቶስ ኤልሻዳይ፡፡
የእኛ መኖሪያችን እንዳይደለ ምድር፣
በዕርገቱ ሰብኮልን የመንግሥቱን ምሥጢር፡፡

ዳግም ከልዕልና ዳግም ከክብር ሕይወት፣
እንደምንገባ ከኢየሩሳሌም ከዘለዓለም ርስት፡፡
የሚፈጸም ተስፋን ውስጣችን አስርጾ፣
በአማናዊ ቃሉ ልባችን ታድሶ፡፡

ዐረገ በክብሩ ዐረገ ወደ ሰማይ፣
የነገሥታት ንጉሥ ክርስቶስ ኤልሻዳይ፡፡
ከጸጋው ግምጃ ቤት ከቤቴል ከጸናን፣
መንግሥቱን ለመውረስ ተደርጎልን መዳን፡፡
ለመኖር እንትጋ አምነን እና ታምነን፣
ሁሌ እያዘከርን ውለታና ፍቅሩን!!!