‹‹ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› (ሮሜ. ፲፪፥፲፰)
በለሜሳ ጉተታ
ማኅበራዊ ሕይወት የአንድነት፣ የመቻቻል እና የመደጋገፍ ኑሮ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን አስተምሮ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ መተሳሰብ፣ መረዳዳትና መተጋገዝ እንዳለብን ያስረዳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዳሉት ‹‹ማኅበራዊ ሕይወታችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ የመተጋገዝ፣ ምንጭ ስለሆነ የእርስ በርስ ግጭትን በማራቅ ሰላማዊ፣ የለመለመ አካባቢ፣ የለማ ሀገር እንዲኖረን ትልቅ እና መሠረታዊ አስተዋጽኦ አለው››፡፡ ይህም ኃላፊነትና አደራን መወጣት ነው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን ሀገርን፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ታሪክን፣ ትውፊትን፣ ሥርዓትን ለእኛ ያስረከቡን የክርስትና ፍቅር፣ ውለታና አደራ ስላለባቸው ባለ ራእይና ሩቅ አሳቢ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡ ክርስቲያኖች ይህን አደራ ተቀብለው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን በመጠበቅ በኅብረት ለመኖር ክርስቲያናዊ ምግባሮችን የመፈጸም ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ዘረኝነት፣ ለዝሙት መገዛት፣ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍቅርን አለመፈለግ፣ ትዳርና ቤተሰብን መበተን፣ ክርስቲያናዊ ግዴታን አለመፈጸም እና ከክርስትና ሕይወት መራቅ የመንፈሰዊ ሰው ምግባር አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ. ፲፪፥፲፰ ላይ ‹‹ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› በማለት መክሯል፤ ክርስትና ፍቅር ነውና፡፡ ያለምንም አድልዎ ሰውን ሁሉ ሳንንቅ በማክበር፣ በሰው ላይም ችግርን ሳንፈጥርና ተንኮልን ሳንሠራ መኖር አለብን፤ ይህ ደግሞ ክርስቲያናዊ መሠረት ነው፡፡
ማኅበራዊ ጉዞ በእምነትና በእውነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ለበረከት ይሆናል፡፡ ሥራችንን በትጋት፣ በቅንነት፣ በታማኝነት እንዲሁም በታዛዥነት ልንፈጽም ይገባል፡፡ ትዳራችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሲጸና፣ መልካም ቤተሰብ ስንመሠርት፣ የታመሙትንና የተቸገሩትን ስንጠይቅና ስናስተዛዘን፣ የተራቡትን ስናበላና ስናጠጣ፣ ተዝካር ስናወጣ፣ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ በአንድነት ውይይት ስናደርግ፣ ቅዱሳንን፣ ጻድቃንና ሰማዕታትን ስንዘክር እንዲሁም የቡሄ (ደብረ ታቦር) እና የደመራ (የመስቀል) በዓላትን በአንድነት ስናከብር፤ ማኀበራዊ ሕይወታችን ጠንካራ ይሆናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የማኀበራዊ ሕይወት ጠቀሜታን ሲገልጽ ‹‹ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ፡፡›› ብሏል (ሮሜ. ፲፪፥፲፭)
በሐዲስ ኪዳን በሐዋርያት ስብከት ያመኑ ምእመናን በአንድ ልቡናና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ይኖሩ ነበር፡፡ ያላቸውንም ሀብት የሚያስቀምጡት በጋራ እንጂ በግል አልነበረም፡፡ ንብረታቸውን በሙሉ እየሸጡ ገንዘባቸውን ሰብስበው በሐዋርያት እግር ስር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ‹‹ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ ‹ይህ የእኔ ገንዘብ ነው› የሚል አልነበረም››፡፡ (ሐዋ.፬፥፴፪)
ማኅበራዊ ሕይወት የጽድቅ፣ የቅድስና፣ የበረከት ሥራን የምንሠራበት እና ለዘለዓለም ሕይወትና ክብር የሚያበቃንን ሥራ የምንፈጽምበት ነው፡፡ ለስንፍናችን ሰበብ ማቅረብ የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከትን ያሳጣል፤ ሰላም የሰፈነበት ሕይወት እንድንኖር አያደርግም፡፡ ሁሉ ጊዜ ሕይወትን በሀሳብ፣ በጭንቀት፤ በጉድለት ለመምራት ይዳርጋልና ወደ ልቦናችን መመለስ አለብን፡፡ ፩ኛ ጢሞቴዎስ ፮፥፳ ላይም ‹‹የተሰጠህን አደራ ጠብቅ›› ማለቱ ማንነትን ያለመርሳት ኃላፊነት እና አደራን መወጣት እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች መድረስ እንዳለብን ስለሚያሳይ ልንማርበትና በሕይወትም ልንኖርበት ይገባል፡፡
ተምረው ማገልገል ያቃተቸው፣ የጠፉ፣ በዓለም ጉያ ሥር የተሸሸጉ፣ ከቤተ ክርስቲያን እና ከንስሓ ሕይወት የሸሹ ሰዎች የክርስትና ክብር ስላልገባቸው ነው፡፡ የክርስትና ክብር የገባው ለሥጋ ምቾት ቦታ አይሰጥም፡፡ ነፍሱን ያስበልጣል፤ ከሁሉም ነገር ይልቅ ለክርስትና ሕይወቱ ቅድሚያ ይሰጣል፤ ራሱን አሳልፎም ለአምላኩ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ዛሬ ብዙዎች በዓለም ጠፍዋል፤ ማንነታቸውን ረስተዋል፤ በዚህም ለዲያብሎስ ለሥጋ ፈቃድና አምሮት ተገዝተዋል፡፡ እንኳን በእኛ በአሕዛብ ዘንድ የማይሠሩ በዓይን ለማየትና በጆሮ ለመስማት አሰቃቂ የሆነ ሰይጣናዊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፤ ስለዚህም ወደ ልቡናችን መመለስ ይኖርብናል፡፡
ዛሬ ሰዎች በኅብረትም ሆነ በግል የረከሰ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፤ ጫት የሚቅሙ፣ ሲጋራ የሚያጤሱ፣ አብዛኛው በዝሙት የተጠቁ እና የሚተዳደሩ፣ ትዳራቸውን በየፍርድ ቤቱ የሚፈቱ፣ ለተለያዩ ሱሶች የተገዙና በመጠጥ ብዛት የሚሰክሩ፣ በስመ ክርስቲያን የሆኑ ነገር ግን በሕይወት የሌሉ ብዙ ናቸውና፡፡ ችግሩንም ለመፍታት ሁላችንም በጋራ ልንሠራ ይገባል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ቃለ እግዚአብሔርን የሰማን፣ የተማርን፣ ለሌላውም መትረፍ የነበረብን ክርስቲያኖች ነበርን፡፡ ነገር ግን ለሥጋ በማድላት የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር፣ ኃላፊነትን፣ የእግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያንን ውለታ በመርሳት አደራችንን መወጣት ያቃተን አለን፡፡ ይህ ከማኅበራዊ ሕይወት ውጪ ነውና ያለብንን አደራ እና ኃላፊነት በማሰብ ልንወጣ ይገባል፡፡