ማኅበራዊ ሕይወታችን!

ክፍል ሁለት

በቃሉ እሱባለው

ታኅሣሥ  ፳፫፤ ፳፻፲፯  .

ተወዳጆች ሆይ! ስሙ እንደ መዓር በሚጣፍጥ፣ መድኃኒትም በሚሆን፣ በቅዱስነቱ ዘለዓለም ያለ ረዓድ በአስጨናቂዎቻችን ፊት ክብር እና ሞገስ አግኝተን፣ ሕያውም ሆነን በምንኖርበት በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዴት ሰነበታችሁ? ፍቁራን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ፣ በባሕርይ አባቱ በአብ፣ በባሕርይ ሕይወቱ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ሳምንቱን አልፈን በቀጣይ ክፍል እነሆ ተገናኘን!

በባለፈው ሳምንት ስለ ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ በእኛ ዘመን ምን እየሆነ፣ ምን እየሠራን እያለፍን እንደሆነ፣ ካለፈው ዘመን ጋር እያመሳሰልን ከራሳችን ጋር እየመዘንን በስሱም ቢሆን ገረፍ አድርገን ለማየት ሞክረናል። ዛሬም ያንኑ ርእሰ አንቀጽ ይዘን ማኅበራዊ ሕይወት በክርስትና አስተምህሮ እና በዘለዓለማዊ የሕይወት ሽግግራችን ያለውን ምልከታ፣ የማኅበራዊ ሕይወት መሳሳት መንሥኤዎችን እና መዳኛ የሚሆነንን ጠቅሰን እናልፋለን።

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን “ብቻ” የሚባል ነጠላ ትርጉም ያለው የሕይወት ፍልስፍና እና የመዳን ጉዞ የለም። ይህን ለመዳን የሚለማመዱትን እድገት እና የጽድቅ መንገድ ፍለጋ ማሳረጊያው እና ምልዓታዊ የሚያደርገው መጠቅለያው አንድነት ነው። ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዓተ አምልኮዋ ሁሉ ከአካል ለይታ የምታቀርበው የአካል ክፍል የለም፤ ከአካል ክፍልም አግዝፋ የምታየው አካልም የለም።

የሁሉም ነገር ማሠሪያ እና መጠቅለያ ገመዱ አንድነት ነው። ለዚህ ትምህርት መነሻው እና አርአያችን እራሱ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ያስተማረን ትምህርት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ካስተማረው ትምህርት አንዱ በስሙ በመሰብሰብ መጸለይ፣ መኖር፣ መሥራት፣ በስሙ በመተባበር አንድ አሳብ አንድ ልብ በመሆንም እንዲኖሩ በጋራ ወደ አንዲት መንግሥት እንዲቀርቡ ያስተማረበት የወንጌል ክፍል ይህ ነው። “ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ.፲፰:፲፱-፳)

የእርሱን መንገድ የተከትሉ ቅዱሳን ሐዋርያቱም ቢሆን በአንድ አሳብ በአንድ ልብ ሆነው በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ሲኖሩ በአንድ አሳብ የሚያፀናን መንፈስ እንደተቀበሉ በመጽሐፍ ተጽፎ እናገኛለን። “በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቈረሱ፥ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፡፡” (ሐዋ.፪:፵፮፣ ፪:፩-፬)

ይህ ትምህርት ከክርስቶስ ኢየሱስ የተቀበልነው በቅዱሳን በኩል ያገኘነው  ነው። ቅድስት ቤተ ክርሲቲያን በወንጌል በቅዳሴ ለምእመኗ የምትሰብከው ከአፏ የማይጠፋ ስብከት ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊም ስለ ማኅበራዊ ሕይወት እና ስለ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ብለው ጽፈዋል። “ቤተ ክርስቲያናችን ራሷ የማኅበራዊ ኑሮ ትምህርት ቤት ናት። ማንኛውም በጎ አድራጎት ሰብአዊ ርኅራኄም የሚጀምርባት የሚፈጸምባት የኅብረትም ሥራ የሚከናወንባት ከፍ ያለችው ድርጅት ቤተ ክርስቲያናችን ናት።” (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፣ ማኅበራዊ ሕይወት በኢትዮጵያ ገጽ ፲፱)

በሕይወት ዘመናችን፣ በበዓላት ቀን፣ በሰንበታትም ዕለት የታመሙትን በመጎብኘት፣ የታሠሩትን በመጠየቅ፣ የተጣሉትን በማስታረቅም፣ ያዘኑትን በማረጋጋት፣ ችግረኞችን በመርዳትም ቢሆን እስከ ዕለት ምጽአት ድረስ ሳናቋርጥ እንድንፈጽም ሕዝቡን በመምራትም በማስተማርም ቤተ ክርስቲያን ከችግረኞች ጋር አብራ ነበረች፤ አለች፤ አብራም ትዘልቃለች። (ማቴ. ፳፭፥፩- ይመልከቱ)

በዘለዓለማዊ እና በሰማያዊ የሕይወት ጉዞአችን እንዲሁም በመዳን ትምህርታችን ውስጥ መዳን የሚፈጸመው በግልም በኅብረትም እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። በዚያ መገፋፋት የለም፤ ብቸኝነት እና እኔነት ብቻ የለም፤ አይሁዳዊም ግሪካዊም የለም፤ ጥቁርም የለም ነጭም የለም፤ ባሪያና ሎሌም የለም፤ አፍሪካዊም ሆነ አውሮፓዊ የለም፤ የቀደመም ሆነ ዘግይቶ የገባ የለም፤ ሁላችንም ስለሁላችን በበጎቹ የታረደውን እንደ የዋህ በግ ሥጋ ከአንድ መሶብ ቆርሰን እንበላለን፤ ያፈሰሰልንን ደም ከአንድ ጽዋ ቀድተን እንጠጣለን እንጂ። “አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።” (፩ኛ ቆሮ ፲፪:፲፫)

ይህን የጽድቅ ሥጋ በልተን የሕይወት መጠጥ ጠጥተን ዘለዓለም ከድካማችን እናርፋለን፤ ከጥማችን እንረካለን። ብዙ ስንሆን በአንድ መሶበ ወርቅ አንድ እንሆናለን፤ ቁጥራችን እልፍ ሲሆን በአንዱ ጌታ በመስቀል ላይ በተከፈለልን ቤዛነት አንድ እንሆናለን። በመስቀሉ ሥር ሁላችንም እንገናኛለን። ሌሎች በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉ የትምህርታችን አካል የሆኑትን ሁሉ በዚህ ጽሑፍ ዘርዝሮ መጥቀስ ውቅያኖስን በእንቁላል ስባሪ ቀድቶ መፈጸም እንደማይችለው ሁሉ አይቻልምና ወደ ተከታዩ ጉዳያችን እንራመድ።

ማኅበራዊ ቀውስ

ዓለም ቀውስ ውስጥ ያልገባችበት ዘመን ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የሚቻልበት ጊዜ የለም። ከቅትለተ አቤል ጀምሮ ምስቅልቅል የማያቋርጥ የሕይወት መልክ ነው። ካብ ለካብ መተያየት፣ የመገፈታተሪያ ጉድጓድ መማስ፣ ከላይ ወደ ታች መጎተቻ ገመድ መፍተል ዘመናትን ያሳለፉ የገፉ ደዌዎቻችን ናቸው። በእኔ እበልጣለሁ እና ለእኔ ይገባኛል በሽታ መለከፍ የጀመርነው ከቃየል ክፉ ተግባር ጀምሮ ነው። እነዚህ እኩይ ግብራት (ክፉ ሥራዎች) ማኅበራዊ ቀውስ እንዲስፋፋ መገፋፋት በደም ሥራችን እንዲከተብ ምክንያት ሆነውናል። ከእነዚህ ክፉ ሐሳቦች ዋነኞቹን እና ቀዳሚዎችን ከእነ መዳኛቸው እንይ።

ራስ ወዳድነት:- በነጻ ያገኘውን እንዲሁ በነጻ ከመስጠት ይልቅ ዋጋው ከፍ ባለ ነገር መሸጥ፣ በምን አገኝበታለሁ እና ላላገኝበት ምን አደከመኝ በሚል የግል ጥቅም መታሰር ነው። የምናደርገውን ዋጋ ጠብቀን ማድረግ፤ በሌሎች ድካም ላይ የራስን ጥቅም አሻግሮ መቃረም፣ የማይገባንን መሰብሰብ፣ እነዚህ ሁሉ በጋራ ሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ልዩነቶቻችንን የሚያሰፉ ናቸው። ቃየል በአቤል ላይ የተነሳሳው የእርሱ ባልሆነ ነገር ላይ የራሱን ጥቅም በማስቀደሙ የወንድሙ የሆነውን ለማግኘት በመመኘት በሽታ ስለተጎዳ ነው። የራስ ጥቅም ፍላጎትን በማስቀደሙ ከጽድቅ ይልቅ መርገምን ወደ ቤቱ ጋበዘው፤ ተቅበዝባዥነትን በእንግድነት በሕይወቱ ጠራው። በዘመኑም ሰው ሁሉ የሚቀጠቅጠው፤ ከእጁም መዳፍ የወንድሙ ደም የሚጮህበት ሆነ።

ጥቅመኝነት በሌሎች ጥላ እንዳናገኝ፤ በበረሃ ብቻዋን እንዳለች ዛፍ በብቸኝነት ፀሐይ የምንቀጠቀጥ እንድንሆን ያደርገናል። በዚህ ጥላ ሥር የሚኖር ሰው ብቻውን ለጦርነት በጠላት ፊት እንደተሰለፈ ወታደር ነው፤ ሁለቱም ቤዛ የሚሆንላቸው የላቸውምና።

ምቀኝነት:- ምቀኝነት እና ጥቅመኝነትን የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች አድርገን ልናያቸው እንችላለን። ምቀኝነትም ሆነ ጥቅመኝነት ከሌሎች ይልቅ ራስን ማስቀደም ናቸው። የማይገባንን ነገር መፈለግ ልንለው እንችላለን። መመቅኘት ባልበላው ልጫረው ዓይነት ነው። ላንበላው ግን ሌሎችም እንዳይጠቀመ መፈለግ ነው። ምቀኝነት ቅዱስ ጳውሎስ የሥጋ ፍሬዎች ብሎ ከሚጠራቸው ውስጥ አንዱ ነው። (ገላ ፭:፳፩) ይህ የሥጋ ፍሬ ፍጻሜው ሞት ነው። በምቀኝነት የሚጓዝ ሰው በሆዱ ውስጥ የሚገድለውን መርዝ ይዞ እንደሚኖር እባብ ነው። ይህንን ሰው ቅዱስ ዮሐንስ ዘቅሊማቆስ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ “በምቀኝነት የሚኖር ሰው የገዛ ራሱን ገዳይ መርዝ ተሸክሞ እንደሚኖር እባብ ነው።” (መንፈሳዊ መሰላል ገጽ ፻፲፯፣ በእንግሊዝኛው ቅጅ:-the ladder of divine ascent)

ምቀኝነት ማኅበራዊ ሕይወትን የሚያፈርስ አፍራሽ፣ የነፍስ መርዝ፣ የጽድቅ ሥራዎች መሰናክል እና በልብ ውስጥ ያለ ትል፤ በመራርነት ውስጥ ደስታ የለሽ ስሜትን የሚያፈራ ተክል፣ በሰይጣን የውድቀት መረብ ውስጥ ያለ የጽድቅ እና የአብሮነት ሕይወት ጠላት ነው።

ሆዳምነት:- በዚህ ሐሳብ ዙሪያ የአንድን ሊቅ ሐሳብ ጠቅሰን እንለፍ።

“እኛ ራሳችንን ስንወቅስ ሆዳችንን በተለየ ሁኔታ ልጠቅሰው ግድ ነው። በእርግጥም  የሚያስደንቀው ማነኛውም ሰው ከመሞቱ በፊት ከሆዳምነት አምልጦ እንዴት ነጻ ሊወጣ ይችላል? ሆዳምነት በሆድ ላይ ግብዝ ነው። ሆዳምነት አሳሳች ነው። በመካከለኛ ደረጃ ይመገባል፤ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ማንኛውንም ነገር ተስገብግቦ መዋጥ ይፈልጋል።” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘቅሊማቆስ፡ መንፈሳዊ መሰላል ገጽ ፻፳፱)

በሆዳምነት የተቃጠለ ሰው ነገ በእኔ ሊደርስ ይችላል ብሎ አያስብም። ማግበስበስን፣ መጎምዠትን እና መስገብገብን በቤቱ ይጠራል። ስለ ሌሎች ግድ የለውም። ለማኅበራዊ ሕይወት መቃወስ ትልቅ በር ይከፍታል። የሊቁን ሐሳብ አንድ በአንድ እየመረመርን ብንመለከተው የምናገኘው ይህንኑ ነው። ሆድን ስለመሙላት ፈንታ እንጂ ስለ ሌሎች ደኅንነት የምናስብብበት፣ የሌሎች ጾም ማደርን የምናስታውስበት በቂ ሰዓት አይኖረንም። የማጣት ጣዕምን እያመላለሱ በመሠቃየት መኖርን መምረጥ እንጅ የሌላውን ጉድለት ለመሙላት በመዳፋችን ውስጥ ያለውን የእኛን ርዳታ እና ሽርፍራፊ ሳንቲም፣  የዳቦ ፍርፋሪ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች እንድንረዳ ዕድል አይሰጠንም።  ሆዳምነት አንዱ የኃጢአተኞች መልክእ፣ የኃጢአት ሁሉ ነቅዕ ነው። ኃጢአትንም የሚወልደው የበኩር ልጁ ሆዳምነት ነው።

ተንኮለኝነት:- የሌላውን መውደቅ አሻግሮ በራስ ሐሳብ ውስጥ ማቀድና በሴራ ውስጥ መረብ ዘርግቶ ሌሎች  እንዲወድቁ መጣር ሌላው የማኅበራዊ ሕይወታችን መቃወስ መንሥኤ ነው። አንዱ ሲነሣ ሌላውን ለመጣል የሚደረግ የድንቁርና ቁማርተኛነት መሆን ነው። አዳምን ያሳተ እባብ በተንኮሉ ነው። ተንኮለኝነት በመልካም ጠባይ ውስጥ ተሰውሮ በደም እና በመንፈስ ውስጥ ዘልቆ የሚገባ አደገኛ መርዝ ነው። ተንኮለኛ ሰው ከሁሉም ክፉ ሰዎች በሚተፋው መርዛማ ነገር እጅግ ይለያል። ምላሱ ያማረ፤ ቃሉ የተዋበ፤ አንደበቱ የሚጣፍጥ በሽንገላ ቃላት የወደቀ የዋህ የሚመስል ሰው ነው።

ያ አዳምን ያሳተ እባብ ከዚህ አይነት ግብር ካለው ሰው ጋር የተስማማ ነው። እባቡ ለአእምሮ ደስ የሚሉ ቃላትን ቢያወራም፣ ለሥጋ ሐሴትን የሚሞሉ ምኞቶችን ይዞ ነበረ። በአመጣው ተንኮልም አለመተማመንን፣ መለያየትን ሰበከ፤ አዲስ እና እንግዳ ጠባይ አስተዋወቀ፤ ኃጢአትም የባሕርይ ሆና ዘልቃ ወደ ሰው ባሕርይ እንድትገባ መንገድ ጠራጊ ሆነ። በእርግጥ ባመጣው የተንኮል ሥራ ቀድሞ የጠፋው እራሱ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን በሰዎች መካከል፣ በሰው እና በሰማያውያን መካከል፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል፣ በሰውና በፍጥረታት መካከል የነበረችን አንድነት አፍርሷል። መርገም በሰው እና በራሱ ላይ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። (ዘፍ ፫:፩- መጨረሻው ይመልከቱ።)  በተንኮል የወደቀ ሰውም ስለሌላው መውደቅ እንጅ ስለራሱ ቀድሞ መረገም አያስተውልም። በኋላ ላይ ግን ለራሱም ሞትን ይጋብዛል፣ ለማኅበሩም መለያየትን ይዘራል። ይህ ነው የተንኮለኝነት ፍሬ። በሁሉም ዘንድ ሞትን እና መለያየትን ማምጣት።

ሌሎች ማኅበራዊ ሕይወታችንን ከሚያፈርሱ ምክንያቶች መካከል ዘረኝነት በዋናነት የሚጠቀስ ነው።

ታዲያ ምን እናድርግ ? እንዴት እንውጣ?

ማኅበራዊ ሕይወት በግለሰባዊም ሆነ በኅብረት (አንድነታዊ) ላይ ያለንን ትስስር በመጨመር የሚመጣ መስተጋብር ነው። በዚህ መስተጋብር ኦርቶዶክሳውያን ያለ ዘውገኝነት (ወገንተኝነት)፣ ያለ ሃይማኖታዊ ልዩነት ከሁሉ ጋር በሰላም እና በፍቅር በመኖር ሌሎችን በፍቅራችን መዓዛ በመሳብ ወደ ክርስቶስ ፍቅር እንድንደርስ መሽቀዳደም ይገባናል። በልባችን የሚፈሰው የፍቅር እና የሰውነት መዓዛ ሌሎች እንዲማረኩ እንዲያደርጋቸው የምንችለውን  ቅድስና እንድንለብስ፤ በመንፈሳዊ ባሕር መስመጥ እና ጽድቅን ወዳጅ ማድረግ ያስፈልገናል። ያም በዚህ በማኅበራችን በሚገኘው አንድነት ነው። (በማኅበር ሳሉ የሚያጽናናውን መንፈስ ቅዱሳን ሐዋርያት እንደተቀበሉ።  (ሐዋ.፪:፩- እስከ መጨረሻው)

ይህን ለማድረግ ደግሞ ልዩነትን ካመጡት በመሸሽ የሚገኝ ነው። በትሕትና እና በቅንነት ስለ አንድነት እና ስለ ጽድቅ የወገናችንን እንባ መጥረግ፣ ለሌላው መብት እኛ ዘብ መቆም፣ በፍቅር ወንበር ተቀምጦ ርትዕ (የቀናች) የሆነችን ፍርድ በመፍረድ የባከነ ልዩነታችንን ነፍስ ልንዘራበት እንችላለን። በየቤታችን ወደቀው ወንድማችን ለራሳችን የምንሰጠውን ክብር በመስጠት፣ ማዶ ጋራ ተሻግሮ ባለው ሰው ኀዘን አብሮ ማዘን የፈረሰውን ይጠግነዋል።

ያ አሻግረን ያየነው እሳት አይደል፤ ሰደድ ሆኖ የእኛን ቤትስ ያለከልካይ የሚያቃጥለው በዝምታ ያለፍነው ጩኸት አይደል በተኛንበት መጥቶ የሰላም እንቅልፋችንን የሚነሳን፣ ያ የረሳነው እና የተውነው ድሮ የፈሰሰው እንባ አይደል ዛሬ የደም ጎርፍ ሆኖ በቤታችን በራፍ ሲያልፍ ያየነው። ትናንት ሲቆፈር ያየነው ጉድጓድ አይደል የልጃችን መቃብር የሆነው። አዎ! ሕልም እናልም የነበረው እኮ ልጃችንን፣ እናታችንን፣ አባታችንን፣ ወንድማችንን፣ እኅታችንን እኮ ልንቀብር አልነበረም። የጦር መሣሪያ ድምጽ ልንሰማ ሳይሆን የልጆቻችንን የእድገት እና ዜማ ልናደምጥ ነበር።

እስኪ ጥያቄ እንጠይቅ፤ አሁን ባለው ነገር ለምን ራሳችንን ከዚያ ነጻ እናወጣለን? ለምን እንደ ጲላጦስ እጃችንን እንታጠባለን? ለምን ርቀን እንቆማለን? እንዴ ለትልቁ ወንዝ ከቤታችን የሚወጣው የውኃ ፍሳሽ ገባሪ እና መጋቢ መሆኑን እንዴት እንዘነጋዋለን? እንዴት ያዋጣነው አንዳንድ ኃጢአት እና ክፋት እንዳለ ማስታወስ የአእምሮ ወቀሳ አመጣብን? ትንሽ የሰጠን የመሰለን ግን ብዙ የዘግንናቸው የችግሮቻችን ሰበቦች የሉም እንዴ? ታዲያ ይህ ሁሉ ከወዴት መጣ? ሃይማኖተኛ በምንባል በእኛ ቤት እንዴት ይህ ይሆናል? ምን ያህሎቻችን ልጆቻችንን በሥርዓት በውስጥ እና በአፍአ ተቆጣጥረን መልካሙን ዘር እናቀብላቸዋለን? ከልጆቻችን በጀርባ የሚታየው የእኛ ማንነት አይደለም እንዴ? ያንን ከኅብረቱ የመነጠል ዕቅድ ማን ወጠነው?

ስለሆነው ነገር ቁሙና እናልቅስ እንጂ፤  የተከፈለልንን ውድ ዋጋ አንዘንጋው። እያደርን ወደ ኋላ አንመለስ። በመስቀል ርቃኑን የቆመውን ጌታ እኮ ያገኘነው አንድ አድርጎን፣ የተጣላነውን አስታርቆን፣ የተለያየነውን አንድ አድርጎን፣ የተበታተንነውን እኮ ሰብስቦን እንጅ እንደተለያየን አይደለም። ያንን የሕይወታችንን ወደብ አሻግረን እንመልከት። ከጥልቁ ባሕር እንውጣና ከከንዓን ምድር ከሚፈሰውን ሰማያዊ ምግብ እና መጠጥ ለመብላት እና ለመጠጣት እንሽቀዳደም እንጅ። ወደ ባሕረ ኤርትራ እንግባ እና ከጠላቶቻችን ጋር ተናንቀን ወደ ጥልቁ የገባውን ሁሉ በውኃው ይወሰድ ዘንድ የጠላታችንን ሠራዊት ከሥር ትተን ብቻችንን እንውጣ።

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “የሙሴ ሕይወት” በሚል ርእስ በጻፈው ድርሰት ውስጥ እስራኤላውያን ወደ ኤርትራ ባሕር ሲገቡ እና ሲወጡ ያጋጠማቸውንና እኛ ምን መማር እንዳለብን ለመጠቆም በጻፈበት አንቀጽ ሥር እንዲህ የሚል ሐተታ አቅርቦልን እናገኘዋለን። የግብፃውያንን ሠራዊት፣ ፈረሶቻቸው፣ ሠረገሎቻቸው፣ ነጅዎቻቸው፣ ጦረኞቻቸው፣ ወንጫፊዎቻቸው፣ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ወታደሮቻቸው፣ በጠላት ወገን የነበሩ ሁሉ የሰው ልጅ ባሪያ የሆነባቸው ልዩ ልዩ የነፍስ ተጻራሪዎች ምሳሌ መሆናቸውን የማያውቅ አለን? ያልተገራ ኅሊናው ወደ ደስታ፣ ኀዘን እና ምኞት የሚነዳው እና ስሜታዊነቱም የሚገፋው ሰው ከተጠቀሰው ሠራዊት የተለየ አይሆንም። …. በማለት ይናገርና …. ከውኃው የሚወጡት ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ሲናገር፤ ከባሕሩ የሚወጡት የግብጻውያንን ሠራዊት በባሕሩ ጥለው የሚወጡት፣ በባሕሩም ውስጥ እነዚያን ሠራዊቶች የገደሉት ብቻ ናቸው በማለት ይገልጸዋል። በግብጻውያን ሠራዊቶች የመሰላቸው የሥጋ ፍላጎቶቻችንን፣ ልጓም አልባነትን፣ ንዴትን፣ ተንኮልን፣ ቅናትን፣ ሥርዓት አልበኝነትን፣ አውሬአዊ ጠባይን፣ ቁጣን፣ ስግብግብነትን፣ ማጭበርበርን ነው። (መንፈሳዊ ሕይወት ምንድን ነው?: በማኅበረ ቅዱሳን ገጽ ፷፮-፷፯)

የቅዱስ ጎርጎርዮስን ሐተታ እንዳለ ይዘነው ወደዚህ ስንራመድ የምናገኘው አንድ መሠረታዊ ሐሳብ አለ። ያ ደግሞ መንፈሳዊ የጽድቅ ሕይወት ነው። የጽድቅ ሕይወት የሚፈጸመው ደግሞ አንድ በምታደርግ የክርስቶስ መገኛ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ነውና በዚያች መንፈሳዊት ሐመር ከቅዱሳን ጋር አንድነት በመፍጠር የግብጻውያንን ሠራዊቶች በባሕሩ ውስጥ ገድለን በመውጣት በጋራ ልንቆም ያስፈልጋል። እነዚያ የጠላት ሠራዊቶችም ከኅብረቱ የሚለዩን እና ክርስቲያናዊ ማኅበራዊ አንድነታችንን የሚያፈርሱ ናቸው። እኒህም ሆዳምነት፣ እኔነት፣ ቅናት፣ ቅንዝረኝነት(አመንዝራነት)፣ ምቀኝነት ናቸው።

ተወዳጆች ሆይ! ከዚያች ከባሕረ ኤርትራ የጠላቶቻችንን ሠራዊቶች ድል አድርጎ በመውጣት የፈረሰውን እና ሊበጠስ ያለውን የሕይወታችንን ማሰሪያ አንድነታችንን እንታደገው። በዚያ በሚያቀልጥ በረሃ እና በግዞት ሀገር መኖራችንን ጥለን እንውጣ እና በሚያስደንቀው የአባቶቻችን የርስት ሀገር ወደ ከነዓን ምድር እንውረድ። በመንግሥቱ ዳግመኛም በተገለጠ ጊዜ ደስ እንድንሰኝ፣ ርስታችንንም እንዲያወርሰን በጋራ እንቁም።

ተወዳጆች ሆይ! ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ዳግመኛም በሕይወት ብንቆይ በሌላ ርእስ እንገናኛለን። የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ነውና ሁላችንም የተሻለች ነገን በመመኘት፣ዛሬን በትጋት ውስጥ ባለች ጥረት እየኖርን እስከዚያ እንቆይ።

ይቆየን!

                        ስብሐት ለእግዚአብሔር!