“ማኅበረ ቅዱሳን የመዋቅር ለውጡ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚያስፈልጋት ያምናል፡፡”

 አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ

 

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያን ያሉትን ብልሹ አሠራሮች ለማስተካከል፤ የሰው ኃይል ምጣኔ፤ የንብረት አጠቃቀምና አያያዝ፤ በሌሎችም ዘርፎች እየታዩ ያሉትን ችግሮች ይፈታል ተብሎ የታሰበ ጥናት በማስጠናት ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ በማቅረብ እንዲተችና ገንቢ አስተያየቶች እየተሰጡት ይገኛሉ፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ተቃውሞ ሲገጥመው ተስተውሏል፡፡ ይህም ጥናቱን ያጠናው ማኅበረ ቅዱሳን ነው በማለት በአገልጋዮችና ምእመናን ላይ ብዥታን ሲፈጥር ተመልክተናል፡፡ ይህንን ጥናት ማኅበረ ቅዱሳን አጥንቶታል? ቢያጠናስ ችግሩ ምንድነው? ለሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡን የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ የሆኑትን አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝን አነጋግረናል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያስጠናውን የመዋቅር ጥናት ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ይመለከተዋል?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ጥናቱን በዝርዝር አያውቀውም፡፡ ነገር ግን ዘመኑን የዋጀ አሠራር ሀገረ ስብከቱ እንደሚያስፈልገው እናምናለን፡፡ የሀገረ ስብከቱን አገልግሎት ጠንካራ እና የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮች ሁልጊዜም እየተተገበሩ መሄድ አለባቸው፡፡ ከዚህ አንጻር ማኅበረ ቅዱሳን የዚህ ጥናት ዝርዝር መረጃ ባይኖረውም ይደግፈዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችንም ያስፈልጋታል ብሎ ያምናል፡፡

አንዳንዶች የመዋቅር ጥናቱን ያጠናው ማኅበረ ቅዱሳን ነው ይላሉ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- ይህን ጥናት በተመለከተ ማኅበሩ እንዲያዘጋጅ ከሀገረ ስብከቱ የተጻፈለት ደብዳቤ አልደረሰውም፡፡ አልተጠየቀም፡፡ ከዚህ በፊት አንዳንድ ጥናቶች ሲያስፈልጉ ማኅበሩ በደብዳቤ ይጋበዛል፡፡ አዘጋጅቶ ያስረክባልም፡፡ይህንን የመዋቅር ለውጥ ግን እንዲያጠና አልተጋበዘም፡፡

ማኅበሩ ተጋብዞ ባያጠናም ከአጥኚዎቹ መካከል የማኅበሩ አባላት የሉም?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ዓላማ የተማረውን ወጣት ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀርብ ማድረግ፤ ለቤተ ክርስቲያን ጥሩ አመለካከት እንዲኖረው ማድረግ፤ ለማገልገል ክህሎት እንዲኖረው ማስቻል ስለሆነ በመንግሥትም ሆነ በግል ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችንእያስተማረ ያስመርቃል፡፡ ከዚህ አንጻር በግቢ ጉባኤያት ተምረው፤ በማኅበሩ አባልነት ተመዝግበው በተለያዩ የቤተ ክርሰቲያን መዋቅር የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ከያሉበት አጥቢያ ተጠርተው ይህንን የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ ካዘጋጁትና ከሠሩት መካከል አብዛኛዎቹ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ጥናቱን ለመሥራት ሲጋበዙ ከማኅበረ ቅዱሳን ደብዳቤ ተጽፎላቸው ወይም ማኅበሩ ወክሏቸው አይደለም፡፡

ማኅበሩ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ ተጋብዞ የማጥናት መብት የለውም?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አካል በመሆኑ መብት አለው፡፡ ይህ ሁሉ ባለሙያ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን መጥቶ አባል ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ለማገልገልና አባቶቻችንን ለማገዝ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያንን ክፍተት እሞላለሁ፤ አግዛለሁ ብሎ የተመሠረተ በመሆኑ ካለው የተማረ የሰው ኃይል አንጻር ሙያዊ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ መሥራትም አለበት፡፡ ከዚህ በፊትም በተለይ በምህንድስናው ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመስራት ከፍተኛ የሆነ ወጭን ቤተክርስቲያኗ አንዳታወጣ አድርጓል፡፡ አባለቱም የማኅበረ ቅዱሳን አባል ስለሆኑ አያገባቸውም፤ አይመለከታቸውም ሊባል አይችልም፡፡ አባላት የቤተ ክርስቲያን ልጆች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም አባላቱ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተመዝግበው ማገልገል እንዲሁም ማኅበሩ በሚያዛቸው ሁሉ መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እያገለገሉም ነው፡፡

እየተነሱ ያሉት ተቃውሞዎች ጥናቱ ላይ ነው ወይስ ማኅበሩ ላይ ነው?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- ጥናቱን አስመልክቶ ለተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ገለጻ በማድረግ ውይይት ተካሒዶበታል፡፡ በዚህም ወቅት በጥናቱ ላይ የቀረቡ ትችቶች አሉ፡፡ ገንቢ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ተገቢ እና ጤናማ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥናቱ ይቅር ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት መነሳታቸውን ሰምተናል፡፡ ተቃውሟቸው ይሄ ችግር አለበት፤ ያ ደግሞ ቢስተካከል ጥሩ ነው በሚል አይደለም፡፡ ሰነዱ ላይ ያቀረቡት ክፍተት የለም፡፡ ተቃውሟቸው ጥናቱ ላይ ሳይሆን አዘጋጀው ብለው በሚያስቡት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ነው፡፡ እነዚህ ጥቂት አካላት በማኅበሩ ላይ የተለያዩ ትችቶችና የስም የማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ ነው፡፡ ይህ ሥህተትም ወንጀልም ነው፡፡ ጥናቱን ካዘጋጁት ባለሙያዎች መካከል የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ቢገኙበትም የተመረጡት በየአጥቢያቸው ባላቸው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መነሻነት ነው፡፡ ትችቱም ሆነ ስም ማጥፋቱ ማኅበሩ ላይ ነው፡፡ ይህ ተገቢ ነው ብለን አናስብም፡፡ ጥናቱ ላይ አያስኬድም፤ ይህ ግድፈት አለበት ብለው ያቀረቡት ነገር የለም፡፡

ከጥናቱ ጋር በተያያዘ የማኅበሩን ስም የሚያጠፉና የተለያዩ ቅስቀሳዎችን የሚያደርጉ አሉና ከማኅበሩ ምን ይጠበቃል?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- እንዲህ ያሉ ትችቶች መስመራቸውን የለቀቁ ናቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ተጠይቆ ያዘጋጀው ጥናት እንዳልሆነ ገልጸናል፡፡ እንቃወማለን የሚሉ ሰዎች በሰነዱ ላይ ምንም ዓይነት ትችት እያቀረቡ አይደለም፡፡ በሰነዱ ላይ ትችት የሚያቀርብ ሰው ሀሳቡ ጠቃሚ ቢሆንም ባይሆንም ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ነገር እንዳደረገ ይቆጠራል፡፡ አንድ ሰነድ በሆነ አካል ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ በሚመለከታቸው አካላትም ይተቻል፤ ይታሻል፤ ከዚያ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሰነዱ ሙሉ ይሆናል፡፡ ተግባራዊ ለማድረግም አያስቸግርም፡፡

እንቃወማለን የሚሉት አካላት ተቃውሟቸው ሰነዱ ላይ ሳይሆን አዘጋጀ ብለው የሚያስቡትንማኅበረ ቅዱሳንን ነው:: እነዚህ አካላት የተለየ ዓላማ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ያለን ማኅበር ያለ ምንም ማስረጃ መተቸት አግባብ ነው ብለን አናምንም፡፡ እነዚህ አካላት የተለየ አጀንዳ ከሌላቸው በስተቀር ለቤተ ክርስቲያናችን የሚጠቅም ሰነድን ዝም ብሎ ገንቢ ባልሆነ መልኩ መቃወም ተገቢ አይደለም፡፡
ማኅበሩ እነዚህን አካላት አባቶች እንዲያርሟቸውና እንዲያስተካክሏቸው ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በላይ እየገፋ ከሔደ በሕግ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም በማኅበሩ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ወንጀል እየፈጸሙ ናቸው፡፡ ከሁሉም በፊት አባቶቻችን እና የሚመለከታቸው አካላት እነዚህን ሰዎች ትክክለኛ አቋም እንዲይዙ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋሉ ብለን እናምናለን፡፡

ጥናቱ ተግባራዊ እንዲደረግ የማኅበሩ ሱታፌ ምን ሊሆን ይችላል?
አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፡- ሰነዱን ተግባራዊ የሚያደርገው በባለቤትነት ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ይህንን የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ ባለቤትም ሀገረ ስብከቱ ስለሆነ የሚያስፈጽመውም ራሱ ነው፡፡ መመሪያው ተግባራዊ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩም በተደጋጋሚ አቅጣጫ ሰጥተውበታል፡፡ ማኅበራችንም የሚታዘዘውን የመሥራት ግዴታ አለበት፡፡ ሙያዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በአባቶች አሳሳቢነት አግዝ፤ ፈጽም ሲባል አልችልም ማለት አይችልም፡፡ ለውጥ እንዲሁ በቀላሉ አይመጣም፡፡ ብዙ ተቃውሞዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ተቃውሞው በርትቶ የተጀመሩት የአሠራር ለውጦች ወረቀት ላይ ሰፍረው እንዳይቀሩ ማኅበሩ በአባቶች የሚታዘዘውንና የሚጠየቀውን ሁሉ ለመተግበር ዝግጁ ነው፡፡