ማኅበረ ቅዱሳን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በኤጄርሳ ለፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያካሒዳል
መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
ማኅበረ ቅዱሳን መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በደንዲ ወረዳ በሚገኘው ኤጀርሳ ለፎ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚያካሒደው 10ኛው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከዚህ በፊት ከተካሔዱት በተሻለ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡
የማኅበሩ ሐዊረ ሕይወት አዘጋጅ ኮሚቴ ከሀገረ ስብከቱና ከሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ቅደመ ዝግጅት እያደረገÂ ሲሆንÂ ትኬቱን በብር 200.00 በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡
የትኬት ሽያጩም መጋቢት 7 ቀን 2008 ዓ.ም የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከተጠቀሰው ቀን በኋላ ማስተናገድ እንደማይቻል የገለጸው ኮሚቴው ምእመናን 5 ኪሎ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አጠገብ በሚገኘው በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ትኬቱን ቀደም ብለው መግዛት እንደሚችሉ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
የኤጄርሳ ለፎ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ የአዲስ ዓለም ማርያም ገዳምን አልፎ እሑድ ገበያ ከተባለው የገጠር ከተማ ወደ ውስጥ ሦስት ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በግምት ከአዲስ አበባ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
ኤጄርሳ ለፎ በደብርነት የተተከለው በ1830 ዓ.ም ቢሆንም ታቦቱ ግን ከዚያ ቀደም ብሎ ከምንጃር እንደመጣ ይነገራል፡፡ ኤጄርሳ ለፎ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የመንገደኞች/እግረኛች/ ወይራ ማለት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ወለጋ፣ ከወለጋ አዲስ አበባ ለሚመላለሱ መንገደኞች እንደ ማረፊያ የሚያገለግሉ በርካታ የወይራ ዛፎች የሚገኙበት ቦታ ስለነበር ስያሜውን እንዳገኘ የአካባቢው ተወላጆች ይገልጻሉ፡፡
በ1931 ዓ.ም ከማዕጠንት በወደቀ ፍም የሣሩ ጉዝጓዝ ተያይዞ ቤተ ክርስቲያኑ የተቃጠለ ሲሆን፣ በቃጠሎው ከላይ ያለው ጉልላት ሲወድቅ ታቦቱ ላይ አርፏል፡፡ ነገር ግን ታቦቱ ከቃጠሎው በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፏል፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ በርካታ ንዋያተ ቅድሳትና የብራና መጻሕፍት ያሉት ሲሆን የሚቀመጡበት ቤት በመፍረሱ በአደጋ ላይ ይገኛል፡፡