ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማትና በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ እያከናወናቸው የሚገኙ ውጤታማ ተግባራት

መስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

gedamate11በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ገዳማት ከተረጅነት ወጥተው በራስ አገዝ የገቢ ምንጭ እንዲተዳደሩና አንድነታቸውና ገዳማዊ ሥርዓታቸው ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት ሥርዓትና ትውፊት ሳይበረዝ፤ ተተኪ ሊቃውንትንና አገልጋዮችን ለማፍራት ትልቅ ድርሻ ያላቸው አብነት ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር፤ ባልተቋቋመባቸውም አካባቢዎች የማቋቋም ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ዋና ክፍሉ የገዳማትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን ችግር ለመፍታት ከሰሜን አሜሪካና ከአውሮፓ ማእከላት፤ ከማኅበራት፤ በዋና ክፍሉና በማእከላት አስተባባሪነት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ የማኅበሩን አገልግሎት ከሚያግዙ ምእመናን በተደረገ ድጋፍ የገዳማትንና አብነት ትምህርት ቤቶችን ችግር ለመቅረፍ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ወደፊትም በቅዱሳት መካናት በየዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከዋና ክፍሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

በ2005 ዓ.ም. እና በ2006 ዓ.ም. በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ በልማትና በአቅም ማሳደግ ረገድ ራሳቸውን ችለው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የተከናወኑትን ተግባራት ዋና ክፍሉ ካደረሰን መረጃ ጥቂቶቹን እናቀርባለን፡፡

የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች፡-

gedamat12በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የላይ ቤት የመጻሕፍት ትርጓሜ ሐተታ ስልት የሚሰጥበትና ማስመስከሪያ የሆነው የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ 64 ተማሪዎችን እንዲሁም 2 መምህራንን ማስተናገድ የሚችል ባለ አንድ ፎቅ የመማሪያ፣ የማደሪያ፣ የቤተ መጻሕፍት ክፍሎች ያሉት ሕንፃ ከነ ሙሉ መገልገያው ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በምሥራቅ ትግራይ ሀገረ ስብከት ለደብረ ካስዋ ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም የገቢ ማስገኛ ይውል ዘንድ በዓዲግራት ከተማ ላይ ባለ ሁለት ፎቅ የሚከራይ ሕንፃ ፕሮጀክት አጥንቶ የምድር ወለሉን በማጠናቀቅ ቀጣይ የግንባታ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል፡:

 
gedamat13በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡

 

በሰሜን ምዕራብ ትግራይ /ሽሬ/ ሀገረ ስብከት በአስገደ ጽብላ የአቡነ ቶማስ ደብረ ማርያም ዘሃይዳ አንድነት ገዳም 150 ሺህ ሊትር ውኃ መያዝ የሚችል የውኃ ማጠራቀሚያ /ታንከር/ ተሠርቶ ለአገልግለሎት ተዘጋጅቷል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ዘመናዊ የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት ከገዳሙ ጋር በወጪ መጋራት ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል፡፡

በምሥራቃዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት የዲቦ ቅድስት ማርያም አንድነት ገዳም የሽመና ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡: በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የደብረ ዘመዳ ቅድስት ማርያም ወአቡነ በርተሎሜዎስ አንድነት ገዳም የጎርፍ መቀልበሻ ግድብ ሥራ ተጠናቆ ገዳሙን ከጎርፍ ጥቃት ለመታደግ ተችሏል፡፡

gedamat14በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የበዴሳ መካነ ሰላም ቅድስት ማርያም የወተት ላም እርባታ፤ በአፋር ሀገረ ስብከት አዋሽ አርባ ቅዱስ ሚካኤል የመስኖ ልማት ፤ በሽሬ ሀገረ ስብከት ማይ ወይኒ ግዝግዝያ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የወፍጮ ተከላ፤ በከምባታ ሐዲያና ጠምባሮ ሀገረ ስብከት ዱራሜ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የበግ ማድለብ፤ ፤ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት አስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የወፍጮ ተከላ፤ ፕሮጀክቶች በወጪ መጋራት መርሐ ግብር ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ደብረ ከርቤ ጥንታዊ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን የጊዜያዊ የጣሪያ ማልበስ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ደብረ ፀሐይ ዋንጣ ቅድስት ማርያም የንብ ልማት ፕሮጀክት ተጠናቆ ርክክብ ተደርጓል፡፡

በምእራብ ወለጋ ቂልጡ ካራ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እና በሆሣዕና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነባር አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የመቀበል አቅም ለማሳደግ የማስፋፊያና የማጠናከሪያ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

 

በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች፡-

በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት የደብረ ኃይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤት ለ120 ተማሪዎች ማደሪያ፣ መማሪያና ቤተ መጽሐፍ ያለው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ እየተገነባ ሲሆን፤ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል፡፡

gedamat16በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት የደብረ ባሕርይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ወአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ባለ 3 ፎቅ ሁለገብ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ከምሥራቁ የሀገራችን ክፍሎች ተተኪ አገልጋዮችን ለማፍራት በሐረር ከተማ በደብረ ምጥማቅ ቅዱስ ፊልጶስ ገዳም ባለ አንድ ፎቅ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት በአርባ ምንጭ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም ለተማሪዎች ልዩ ልዩ አገልግሎት መስጠት የሚችል አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ እየተሠራ ይገኛል፤ ሥራውም በቀጣይ ጥቂት ወራት ይጠናቀቃል፡፡

የ100 ገዳማት የመረጃ ጥንቅር የምጣኔ ሀብት አመላካች መሠረታዊ መረጃ / Economical maping & profiling / የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

 

የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎች፡-

ገዳማት በራሳቸው ተነሳሽነት በልማት ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ከ70 ገዳማት ለተውጣጡ የገዳማት አበምኔቶችና እመምኔቶች ስለ ሀብት ምንነትና አጠቃቀም፣ ስለ ፕሮጀክት አጠናን፤ እንዲሁም ስለ ሒሳብ መዝገብ አያያዝ የአንድ ሳምንት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በዚህም ጠንካራ ገዳማዊ ሥርዓት የሚመሠረትበትንና የገዳማት እርስ በእርስ ግንኙነት የሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የአብነቱንና የዘመናዊዉን ትምህርት አቀናጅቶ መስጠት በሚያስችለው የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ነጻ የትምህርትና ሥልጠና እድል መርሐ ግብር የጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት 569 ተማሪዎችን በማሳተፍ በአራት አብነት ትምህርት ቤቶች ተጀምሯል፡፡

በ10 አብነት ትምህርት ቤቶች እና በ4 ገዳማት ለሚገኙ አባቶችና እናቶች ባለሙያዎችን በማስተባበር ሕክምና እንዲሁም የጤና፤ የግልና የአካባቢ ንጽሕና ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

ለ120 የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ልዩ ልዩ የአስተዳደርና የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

የተጠናቀቁ ጥናቶች፡-

በምዕራባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት በሁመራ የአብነት ትምህርት ቤት እና የካህናት ማሠልጠኛ ለመሥራት የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት በጂንካ አንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የአብነት ትምህርት ቤቱን የቅበላ አቅም ለማሳደግ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ለዙር አባ ጽርሐ አርያም አቡነ አረጋዊ ገዳም የዝማሬ መዋስዕት ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት የትምህርት መስጫ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ጥናት ተደርጎ የእቃ አቅርቦት በመደረግ ላይ ነው፡፡

በባሕርዳር ከተማ የግእዝና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ሁለገብ የአብነት መምህራን፣ ተማሪዎችና መነኮሳት የሥልጠናና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለመመሥረት የሚቻልበትን ሁኔታ ጥናት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ መሠረትም አንድ ብሎክ ሕንፃ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው ተጀምሯል፡፡

ልዩ ልዩ ድጋፎች፡-

በ162 የአብነት ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ለ182 መምህራንና ለ1,069 ተማሪዎች ወርሃዊ የገንዘብ ድጎማ ተደርጓል፡፡

ጤና ሀብት ነው በሚል መሪ ቃል 20 ሺሕ ለሚሆኑ የአብነት ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ የግል ንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተሰራጭተዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት በደብረ ሊባኖስ ገዳም፤ በምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳምና በፍቼ ደብረ ሲና ዓራተ ማርያም ገዳም ለሚገኙ አብነት መምህራንና ተማሪዎች፤ እንዲሁም ለገዳማቱ ማኅበረሰብ ልዩ ልዩ የጤና ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ ለ80 የአብነት መምህራን የመነጽር እና የመድኃኒት ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ለ275 ቅዱሳት መካናት የእጣን፤ የጧፍ፤ የዘቢብ እና ሌሎች ንዋያተ ቅድሳት ድጋፍ ተደርጓል፡፡