ማኅበረ ቅዱሳን በዜማ መሣሪያዎችና በልሳነ ግእዝ ያሠለጠናቸውን ፭፻፶ ተማሪዎች አስመረቀ

ጥቅምት ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በይብረሁ ይጥና

mireqa

ከምሩቃኑ መካከል ከፊሎቹ

በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ሥር የሚገኘው የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለ፲፪ኛ ጊዜ በዜማ መሣሪያዎችና በልሳነ ግእዝ ያሠለጠናቸውን ፭፻፶ ተማሪዎች ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በማኅበሩ አዳራሽ አስመረቀ፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ለምሩቃኑ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ‹‹ኹላችሁም እዚህ የተሰበሰባችሁት እግዚአብሔርን ለማገልገል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አገር ሰላም ሲኾን ነው፡፡ በመኾኑም እግዚአብሔር ለአገራችን ሰላሙን፣ ፍቅሩንና ቸርነቱን እንዲሰጥልን ተግተን ልንጸልይ ያስፈልጋል›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የአገር ውስጥ ማእከላት ሓላፊና የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሰይፈ ዓለማየሁ በበኩላቸው የማኅበሩ ተቀዳሚ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ሳይበረዝና ሳይከለስ ጠብቆ በማቆየት ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ መኾኑን ጠቅሰው ‹‹እናንተ ተመራቂዎችም የዚሁ ዓላማ አካል በመኾናችሁ የተማራችሁትን ትምህርት ለሌሎችም ማስተላለፍ አለባችሁ›› ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ማእከሉ ከ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ፴፻ (ሦስት ሺሕ) በላይ ምእመናንን በመንፈሳውያን የዜማ መሣሪያዎችና በልሳነ ግእዝ በማሠልጠን ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጉን በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ጌትነት ፍቅሬ ገልጸው በዚህ ዓመትም በበገና ድርደራ ፫፻፶፰፣ በከበሮ አመታት ፹፱፣ በመሰንቆ ቅኝት ፴፭ እና በዋሽንት ድምፅ አወጣጥ ፮፣ እንደዚሁም በልሳነ ግእዝ ፷፪ በድምሩ ፭፻፶ ተማሪዎችን አሠልጥኖ ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ማስመረቁን አስታውቀዋል፡፡

ከበገና ተመራቂዎች መካከል ጋዜጠኛ መስከረም ጌታቸውና የሕክምና ተማሪዋ ቤቴል ደጀኔ በገናን ለመማር ምን እንዳነሣሣቸው ለዝግጅት ክፍላችን ሲገልጹ የበገና መሣሪያ እግዚአብሔር ከሚመሰገንባቸው መንፈሳውያን የዜማ መሣሪያዎች መካከል አንደኛው ቢኾንም እንደ መንፈሳዊ ሀብትነቱና እንደ ሀገራዊ ቅርስነቱ ትኵረት ሳይሰጠው መቆየቱን ጠቅሰው ‹‹ቅርሶቻችንን መጠበቅና ማስጠበቅ የምንችለው በትምህርት በመኾኑ በገና ድርደራ ልንማር ችለናል›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ለአጋዥ ድርጅቶች፣ ለመምህራንና ለምሩቃኑ በልማት ተቋማት አስተዳደር ዋና ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ኀይሉ ፍሥሐ የምስክር ወረቀት ከተበረከተ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ቃለ ምዕዳንና ጸሎት ተፈጽሟል፡፡