ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው
ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም
በእንዳለ ደምስስ
በማኅበረ ቅዱሳን የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ከኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንደሚጀምር የኅትመትና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ም/ክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ገለጹ፡፡
በNilesat, OBS /Oromiya broadcast Service/ ለሠላሳ ደቂቃ ዘወትር እሑድ ከረፋዱ 4፡30-5፡00 ሰዓት እንዲሁም በድጋሚ ረቡዕ ከጠዋቱ 12፡30-1፡00 ሰዓት የሚሠራጨው መርሐ ግብር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊትን ጠብቆ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲያውቁ እና ጸንተው እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ከእምነታቸው ለወጡ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ታስቦ መጀመሩን ምክትል ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡
የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከቤተ ክርስቲያን ለመነጠል በርካታ መጻሕፍት ታትመው እየወጡ በመሆናቸው የማኅበረ ቅዱሳን የአፋን አሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ይህንን ለመከላከል ምእመናን ለማስተማር፣ እምነታቸውን ጠብቀው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ ፕሮጀክቱ መቀረጹንም ገልጸዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ ምእመናንን የሚያንጹ በርካታ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን፣ የጸሎት መጻሕፍትንና መጽሔት በማሳተም፣ በኦሮምኛ ድረ ገጽ ጭምር ሲያሠራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም Dangaa Lubbuu/ የነፍስ ምግብ/ የተሰኘ መጽሔት በማሳተም ለምእመናን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡