ማርኩሽ በለኝ!

በመዝሙርና ኪነ ጥበባት ክፍል

ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ያኔ ስትገለጥ በግርማ መንግሥትህ

በቀኝም በግራም ለምንቆም ልናይህ

ልትከፍል ዋጋችንን ልትሰጥ በክህሎትህ

ሲገለጥ ችሎታህ የማይዛባ አይደለም ችሎታህ

በወንድም እህቱ ላይ በክፋት የቆመ

እርሱ ነው እርሷ ናት እያለ ጣቱን የጠቆመ

ፍቅር እንዲጠፋ

ጠዋት ማታ የለፋ

እኔ ብቻ ብሎ ራሱን ያኮፈሰ

ወንድሙን ለገንዘብ በግፍ የከሰሰ

የእጅህን ሥራ ሁሉ በበደል ያቃለለ

ድሀውን በማንኳሰስ ጨርቃም ነህ እያለ

ፍርድን ስታደርግ በመለኮትህ ኃይል

በዓይኑ በብረቱ ያን ጊዜ ያይሃል

አንደበት ዝም ሳትል

የጭንቅ ቀን በፍጥነት ሳይመጣ

ከጻድቃን ኅብረት ሳንወጣ

በቀኙ የሚቆሙ

ለክብር የታደሙ

ወደ ዘላለም ዕረፍት በክብር  ሲጠሩ

ከመላእክት ጋር  በአንድ ላይ ሲዘምሩ

የኃጥአን ሁካታ

የማይጠቅም ልቅሶ የማይጠቅም ዋይታ

ሲሰማ ያን ‘ለታ

እናት የልጇን ድምፅ በማትሰማበት

የሥራችን መዝገብ በሚዘረጋበት

አዎን! ጌታዬ ያን ዕለት

ምግባር ችሎታዬን ራሴን አውቀዋለሁ

በድንግል ማርያም ስለ አዛኝቱ ብዬ ተማጽኘሃለሁ

በተሸከመችህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን

ዙፋን ባደረከው በሆዷ ማኅፀን

ባጠባችህ ጡቷ

ደግሞም በስደቷ

አንተን ይዛ በተሰደደችው

በርሃ አቋርጣ ግብጽ በገባችው

በድንግል እናትህ በአምስቱ ኀዘኗ

ማርኩሽ በለኝ ስለ ቃል ኪዳኗ!