ማሩ አይምረር፤ ወተቱ አይጥቆር
ሚያዚያ 24/2004 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ተዋቅሮ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ፈቃድ አገልግሎቱን ከጀመረ እነሆ ሃያ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ምንም እንኳን ማኅበሩን በራሳቸው ፈቃደኝነት የተሰባሰቡ ኦርቶዶክሳውያን ቢመሠርቱትም የማኅበሩ መሠረታዊ ዓላማ ግን ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን ለማሳካት በምታከናውናቸው ተግባራት የልጅነት ድርሻውን ለመወጣት በመሆኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር በመግባት መተዳደሪያ ደንቡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተቀመጠለት ተግባርና ሓላፊነት መሠረት አገልግሎቱን እያከናወነ ያለ ማኅበር ነው፡፡ አባላቱም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገራት በቤተ ክርስቲያኗ አጥቢያዎች በሚገኙ ሰበካ ጉባኤያት እና ሰንበት ት/ቤቶች ተመዝግበው የሚጠበቅባቸውን ክርስቲያናዊ ግዴታ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አባላት አብዛኛዎቹ ቤተ ክርስቲያናቸውን በገንዘብ፣ በዕውቀትና በጉልበት ለማገልገል በፈቃዳቸው ቃል የገቡ ቤተ ክርስቲያንና ሀገሪቷ ካሏት ልዩ ልዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ቤተ ክርስቲያናቸውን አገራቸውንና ወገናቸውን በልዩ ልዩ ሙያ እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው፡፡
ማኅበሩ በዋናነት አገልግሎቱን የሚያከናውነው በመተዳደሪያ ደንቡ እንደተቀመጠው አባላቱ በገቡት ቃል መሠረት በየወሩ ከሚሰበሰበው ወርኃዊ አስተዋጽኦ ሲሆን ስብከተ ወንጌል ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ቅዱሳት መካናትና አብነት ት/ቤቶችን በዘላቂነት በልማት ራሳቸውን ለማስቻል የሚሠሩ ኘሮጀክቶችን በጎ አድራጊ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ከሆኑ ምእመናንና ማኅበራት ጋር በጋራ በመተባበር ይተገብራል፡፡ ማኅበራችን ባለንት ሃያ የአገልግሎት ዓመታት በእግዚአብሔርም በሰውም ሊታዩና ሊዳሰሱ የሚችሉ በጎ አስተዋጽኦዎችን ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን እንዳበረከተ ቢያምንም መሥራት ከሚገባው በጣም ጥቂቱን ብቻ እንደሠራና ገና ብዙ እንደሚጠበቅበትም ይገነዘባል፡፡
እስካሁን ያከናወናቸውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባራት ሲያከናውን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት ያለችግርና ውጣውረድ አይደለም፡፡ በእርግጥ አገልግሎቱ መንፈሳዊ አገልግሎት ነውና ሁሉ ነገር ምቹ እንዲሆንም አይጠብቅም፡፡ በየጊዜው የሚገጥሙት ችግሮችና ፈተናዎች የተለያየ መልክ ያላቸው ቢሆኑም የፈተናዎቹ ምንጮች ግን ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ማኅበሩ የቆመለትን ዓላማና የሚያከናውናቸውን በጎ ተግባራት በዓላማ ከመቃወም የሚመነጭ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት ወይም ቀርቦ ባለማየት ከሚፈጠር የተዛባ አመለካከት የሚመነጭ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የማኅበሩን አገልግሎት እየገጠሙት ካሉት ችግሮች አንዱ በዘመናችን መላው ዓለምን እያወከው ያለው የአክራሪነት አደጋ በአገራችንም ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳየት በሚደረጉ ገለጻዎችና የውይይት መድረኮች ግልጽ ባልሆነና በማይወክለው መንገድ የማኅበሩን ስም በመጥቀስ በበጎ አስተዋጽኦው ላይ ጥላ የሚያጠላ ስሜት መፈጠሩ ነው፡፡ ይህ የተዛባ ሥዕል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለያየ መጠንና በተለያየ መንገድ ሲገለጽ መቆየቱና አሁንም እየተገለጸ መሆኑ በአባላቱም ሆነ በሌሎች ምእመናን ዘንድ መደነጋገርን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ምክንያቱም አባላቱም ሆኑ ሌሎች ምእመናን ከከተማ እስከ ገጠር የሚያውቁት የማኅበረ ቅዱሳን ማንነትና ምንነት አሁን እየተባለ ካለው ጋር ፍፁም የማይገናኝ በመሆኑ ነው፡፡
በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የመጨረሻ መዋቅር በሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ መተዳደሪያ ደንብ ጸድቆለት፣ የቤተ ክርስቲያኗን መዋቅራዊ አሠራር ተከትሎ እየሠራ ያለ፣ በርቀት ላሉ በሚሠራቸው ሥራዎች ራሱን የሚገልጥ፣ ቀርበው ማየትና ማወቅ ለሚፈልጉ የሚዳሰስና የሚጨበጥ አካል ያለው መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ባለው ግልጽ አቋሙ እንዳስቀመጠው በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ ከተሰጠው ዓላማና ተግባር እና ከቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት አንጻር አቋሙን መግለጽ ሲያስፈልገው የሚገልጽባቸው የራሱ ሚዲያዎች ያሉት ማኅበር ነው፡፡ የአክራሪነት አደጋ በሀገርም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ላይ ስለሚያደርሰው ጥፋት፣ መልካም የሆነው የሰዎች እርስ በርስ ተከባብሮ የመኖርን የቆየ አገራዊ እሴት ስለማስቀጠል፣ አገራቸውንና ወገናቸውን በታማኝነትና በቅንነት የሚያገለግሉ ዜጎችን ስለማፍራት እንደ ቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ ሓላፊነት በተሞላው መንገድ ሲያስተምርና ሲሠራ ኖሯል፤ አሁንም እየሠራ ነው፡፡ ወደፊትም ያስተምራል ይሠራልም፡፡ እንኳን እምነትን ያህል ታላቅ ነገር ይቅርና አንድ ሰው የሚከተለውን ፍልስፍና ሊከተለው የሚችለው ትክክል ነው ብሎ ሲያምን ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ዛሬ በምድር ላይ ሲኖር የሕይወቴ መርሕ አድርጌ የምጓዝበት ከሞት በኋላም ዘላለማዊ ሕይወት የምወርስበት እምነት /ሃይማኖት/ ትክክል ነው ብሎ ማመኑ በምንም መስፈርት አክራሪነት ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም የእኔ ትክክል ነው ማለት የሌላው ትክክል አይደለም ወይም የእኔ ብቻ መኖር አለበት የሌላው መኖር የለበትም ማለት ሊሆን አይችልምና፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትክክል ናት ብሎ ያምናል፤ እንዴት ትክክል እንደሆነች በንግግርም በግብርም ይገልጣል፤ ይህ ትክክል የሆነው ሁለንተናዊ ማንነቷ ተጠብቆ እንዲኖርም የድርሻውን ይወጣል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በምንም መንገድ ሌላውን የማጥፋት መንፈስን ያዘለ አክራሪነት ተብሎ ሊተረጎም አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ማንነትና ዕድገት የነበራትን በጎ አስተዋጽኦ መግለጽም ሆነ ዛሬም ይህንን አስተዋጽኦዋን እንድትቀጥል ማድረግ እንደ ክርስቲያንም ሆነ እንደ ዜጋ የሚጠበቅበት ተግባር መሆኑን ማኅበራችን ያምናል፡፡ በመሆኑም ዓለምን የሁከትና የሰቆቃ መናኸሪያ እያደረጋት ያለው አክራሪነት ማኅበራችንን አይገልጠውም፡፡ ይልቁንም ሙስና፣ አለመታመን፣ ወንጀለኝነት፣ በሽታ ፣ ወዘተ እያተራመሳት ባለችው ዓለም ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በልዩ ልዩ ሙያ አገራቸውንና ወገናቸውን በቅንነት፣ በታማኝነትና በእውነት የሚያገለግሉ ዜጎችን በማፍራት በራሱ ፈቃድ፣ በራሱ ገንዘብና ጉልበት የበኩሉን እያበረከተ የሚገኝ ማኅበር አገራዊ አስተዋጽኦው በሁሉም ዘንድ በበጎነቱ ጎልቶ ሊበረታታ ሊደገፍ ይገባዋል እንጂ ገጽታውን የሚያጠቁር ማንነቱን የሚያዛባ ሥዕል በመሳልና መደነጋገርን መፍጠር ተገቢ አይመስለንም፡፡
በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን ጉድለት ካለበትም ስለ ጉድለቱ በምድራዊም ሆነ በሰማያዊ ሕግጋት ሊጠየቅ የሚችል ሕጋዊ መንፈሳዊ ተቋም እንጂ ምንም የተሠወረ ነገር እንደሌለ አምነን አባላቱም ሆነ ምእመናን ዛሬም እንደ ትላንቱ አገልግሎታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል አደራ በማለት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ማኅበሩን በማይገልጸው ማንነት እየሣልን ያለን አካላት ደግሞ ማሩን ባለማምረር ወተቱን ባለማጥቆር የማኅበሩን አገራዊ አስተዋጽኦ እናበረታታ ዘንድ ማኅበራችን መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡