‹‹ሙሴ ሆይ፥ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ››
ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ሰዎች ከገድሉ የተነሣ የሚያደንቁት ኢትዮጵያዊው ቅዱስ አባት አባ ሙሴ ጸሊም አስቀድሞ ለሥጋው የሚኖር ወንበዴና አመንዛሪ እንዲሁም ቀማኛ ነበር፡፡ እንዲያውም የሥጋውን መሻት ለመፈጸም ሰዎችን እስከ መግደል የሚደርስ ጨካኝ ሰው እንደነበር ገድሉ ይናገራል፡፡ መብልንና መጠጥንም ከልክ ባለፈ መልኩ ይወስዳል። መጽሐፈ ስንክሳር ላይ እንደተመዘገበው በአንድ ጊዜ አንድ ሙሉ በግ እና አንድ ፊቅን ወይን ጠጅ እንደሚጨርስ እራሱ ይናገር ነበር፡፡
በሥራውም እግዚአብሔር አምላኩን ይበድል ነበር፡፡ ፀሐይን የሚያመልኩ ሰዎችን ያገለግል ስለነበር ፈጣሪውን አያውቀውም፡፡ ብዙ ጊዜም ወደ ፀሐይ እያንጋጠጠ ‹‹ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ›› በማለት ይጠይቃል፡፡ በልቡም ‹‹የማላውቅህ ሆይ፥ ራስህን አሳውቀኝ›› ይል ነበር፡፡
በአንድ ወቅትም ሰዎች ‹‹በአስቄጥስ ገዳም ያሉ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታልም›› ብሎ ሲነጋገሩ ሰማቸው፡፡ ሙሴ ጸሊምም ወደ ገዳሙ ለመሄድ በማሰብ ሰይፉን ታጠቀ፤ ተጉዞም በዚያ እንደደረሰ አባ ኤስድሮስን አገኘው። የመልኩን መጥቆርና ደፋርነቱን ዓይቶም አባ ኤስድሮስ ፈራው፡፡ ሙሴ ጸሊምም ‹‹እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጣሁ›› አለው፡፡ ይህንንም በሰማ ጊዜ አባ ኤስድሮስ ወደ አባ መቃርስ ወሰደው፡፡
በተገናኙም ጊዜ የአምላክን መኖር ማወቅ እንደሚሻ ስለነገረው አባ መቃርስ ሃይማኖትን አስተማረው፡፡ ‹‹ታግሠህ የማስተምርህን ከጠበቅህ እግዚአብሔርን ታየዋለህ›› በማለትም አስረዳው፤ የክርስትና ጥምቀትንም አጥምቆ አመነኰሰው፤ አባ ሙሴ ጸሊምም ተባለ። ከዚህም በኋላ በጽኑ ገድልም ከሌሎች ቅዱሳን ይልቅ የበለጠ አብዝቶ መጋደል ጀመረ፡፡ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስም ሊያስተው በመጣር ቀድሞ ሲሠራው በነበረው ኃጢአት በዝሙት፣ በመብሉና በመጠጡ ይፈታተነው ነበር፡፡ እርሱም በእነዚህ የኃጢአት ፍትወት እንደሚፈተን ለአባ ኤስድሮስ ይነግረዋል፡፡ እርሱም አጽናንቶ ሊሠራ የሚገባውን ያስተምረዋል፡፡
በገድልም ተጠምዶ በኖረበት ረጅም ዘመናት አረጋውያን መነኰሳት ውኃ የሚቀዱበት ቦታ ከእነርሱ በዓት ሩቅ ስለነበረ በሚተኙበት ጊዜ ቤቶቻቸውን በመዞር ውኃ መቅጃዎችን ወስዶ ውኃ ሞልቶ በየደጃፎቻቸው ያኖር ነበር፡፡ በዚህም ሥራው ሰይጣን ቀናበት፤ በእግሩ ውስጥም አስጨናቂ ሕመምን አመጣበት፤ በደዌም ተይዞ እየተጨነቀ ለብዙ ቀናት ታመመ፡፡
አባ ሙሴ ጸሊምም በዚህ ክፉ ደዌ የሚፈታተነው ሰይጣን እንደሆነ ዐወቀ፤ ስለዚህም ሥጋው በእሳት ተለብልቦ እንደ ደረቅ እንጨት እስኪሆን ድረስ ተጋድሎን አበዛ፡፡ በዚህም ትዕግሥቱን ተመልክቶ እግዚአብሔር ከደዌው ፈወሰው፤ የሰይጣንንም ጦር ከእርሶ አራቀለት፤ የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ አደረበት፤ በአስቄጥስ ገዳም የነበሩት ፭፻ (አምስት መቶ) መነኰሳት ወንድሞቹ ከተሰበሰቡ በኋላ አባ ምኔት ሆኖ ተሾመ፡፡
መነኰሳቱም ቅስና ሊሾሙት መርጠው በቤተ መቅደስ በሊቀ ጵጵሳቱ በፊቱ አቆሙት፤ እርሱ ግን አልፈቀደም፤ ‹‹ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት›› በማለትም አረጋውያኑን ተናገራቸው፡፡ በዚህም ጊዜ አባ ሙሴ ጸሊም በልቡ እራሱን ‹‹መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ፥ መልካም አደረጉብህ›› በማለት ገሠጸ፤ ከቤተ መቅደሱም ወጥቶ ሄደ፡፡ ሆኖም ግን ዳግመኛ ሊቀ ጳጳሱ ጠርቶ ቅስና ሾመው፤ እንዲህም አለው፤ ‹‹ሙሴ ሆይ፥ እነሆ በውስጥም በውጭም ሁለመናህ ነጭ ሆነ፡፡››
ከዕለታት በአንድ ቀንም አረጋውያን መነኰሳቱ ወደ እርሱ መጡ፤ ሆኖም ግን ለእነርሱ የሚያጠጣቸው ውኃ አልነበረውም፡፡ አባ ሙሴ ጸሊምም ከበዓቱ መግባትና መውጣት አበዛ፤ ብዙም ሳይቆይ ዝናም ዘንሞ ጒድጓዶችን ሁሉ ሞላው፡፡ መነኰሳቱም አብዝቶ መውጣቱን ተመልክተው ‹‹ለምን ብዙ ጊዜ ወጣ ገባ አልክ?›› በማለት ጠየቁት፤ እርሱም ‹‹እግዚአብሔርን ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ እለው ነበር፤ በቸርነቱም ዝናም ልኮልን ውኃን አገኘን›› ብሎ መለሰላቸው፡፡
በሌላ ወቅትም አባ ሙሴ ጸሊም ከአረጋውያን መነኰሳቱ ጋር በመሆን ወደ አባ መቃርስ ዘንድ ሄደው ጠየቁት፤ እርሱም ‹‹የሰማዕትነት አክሊል ያለው ከእናንተ ውስጥ አንዱን እነሆ አያለሁ›› ብሎ ነገራቸው፡፡ አባ ሙሴ ጸሊምም ‹‹አባት ሆይ፥ ምናልባት እኔ እሆናለሁ፤ ሰይፍን የሚመዝዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ›› የሚል ጽሑፍ አለና ብሎ መለሰ፡፡ (ማቴ.፳፮፥፶፪) በዚህም ጊዜ የበርበር ሰዎች ሲመጡ ተመልክቶ መነኰሳቱን ‹‹እነሆ የበርበር ሰዎች ደረሱ፤መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ›› በማለት አስታወቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አባታችን አንተስ አትሸሽምን?›› ብለው ጠየቁት፤ አባ ሙሴ ጸሊምም ‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገድላል ስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ያቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠብቃት ኖሬአለሁ›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ከመቅጽበትም ደርሰውም የበርበር ሰዎች በሰይፍ ገደሉት፤ ከእርሱ ጋር የነበሩትም ሰባት መነኰሳት መሸሽን አልመረጡምና አብረው ተገደሉ፤ አንዱ ግን ከምንጣፍ ስር ተደበቀ፤ በዚህም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአከ በእጁ አክሊል ይዞ ቆሞ ሲጠብቅ ሲመለከት ከተደበቀበት ወጥቶ ቆመ፤ የበርበር ሰዎችም ገደሉት፤ የሰማዕትነትንም አክሊል ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተቀበለ፡፡ የአባ ሙሴ ጸሊም ሥጋም ደርምስ በተባለ ቦታ በአስቄጥስ ገዳም ውስጥ እንደሚገኝ ገድሉ ይጠቅሳል፡፡ ከአጽሙም ድንቅ ተአምራት ይደረጋል፡፡
‹‹ወንድሞች ሆይ፥ ከሀዲና ነፍሰ ገዳይ፣ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ለውጣ ደግ አባት፣ መምህራንን የሚያጽናና፣ ለመነኰሳትም ሥርዓትን የሠራ ካህንና በሁሉም በአብያተ ቤተ ክርስቲያናት ስሙ እንዲጠራ እንዳደረገችው የንስሓን ኃይሏን ተመልከቱ፡፡›› (መጽሐፈ ስንክሳር ሰኔ ፳፬)
እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ ይጎብኘን፤ አሜን!