መመለስ /ክፍል ሁለት/

የካቲት  15 ቀን  2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ዝምታቸው አስፈራኝ፡፡ “እባክዎ አባቴ ይርዱኝ” አልኩ የሰፈነውን ጸጥታ ሰብሬ፡፡

ዐይኖቻቸውን ከመስቀላቸው ላይ ሳይነቅሉ ‹‹ልጄ ነገ ከእኔ ስላለመኮብለልህ ምን ማረጋገጫ አለኝ?” ስጋታቸውን ገለጹ፡፡

“አመጣጤ የመጨረሻዬ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ውስጤ ተሰብሯል፡፡ ታከተኝ አባቴ!” የተቋረጠው የዕንባ ጎተራዬን ነካካሁት፡፡ ይፈልቅ ጀመር፡፡

ለመወሰን ተቸግረው በትካዜ ከያዙት የእጅ መስቀላቸው ጋር የሚሟገቱ ይመስል እያገላበጡት ዝምታን መረጡ፡፡

እኔ ደግሞ ውሳኔያቸው ናፈቀኝ፡፡ መልስ እሰኪሰጡኝ ድረስ እኔም በለቅሶና በዝምታ አገዝኳቸው፡፡

“አንድ ነገር ታደርጋለህ፡፡” ቀና ብለው እንኳን አላዩኝም፡፡ ዐይኖቻቸውን መስቀላቸው ላይ ተክለዋል፡፡

“ከቃልዎ አልወጣም – የፈለጉትን ይዘዙኝ፡፡”

 

“በጥሞና እንድታደምጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዶግማዋንና ቀኖናዋን አገልጋዮች ካህናትም ሆንን ምዕመናን የመጠበቅ ግዴታ አለብን፡፡ አበ ነፍስን በሚመለከት ቤተክርስቲያናችን ስርዓት ሰርታለች፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ምእመን በቅድሚያ ንስሐ ለመግባት ሲወስን በጾም ፤ በጸሎት ፤ በስግደትና በጎ ምግባራትን በመስራት ራሱን ማረቅ አለበት፡፡ ስለኃጢአቱ የሚጸጸት፤ ዳግም ያንን ኃጢአት እንደማይሰራ የቆረጠ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ንስሐ አባት ሲመርጥም በጸሎት በመታገዝ እግዚአብሔር መልካም አባት እንዲሰጠው መለመን አለበት፡፡ የንስሐ አባት ከያዘ በኋላ ሌላ ለመቀየር መነሳሳት አይቻልም፡፡ መቀየር ካለበትም በቂ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ አበ ነፍሱ በሞት የተለዩ ከሆነ ፤   የሐይማኖት ህጸጽ ካለባቸው ፤  የአካባቢ ርቀት በየጊዜው እንዳይገኛኑ ከገደባቸው፤ የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው፤ እንዲሁም ሌሎች መግባባት የማያስችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አበ ነፍስ መቀየር ይቻላል፡፡ ለመቀየር ሲታሰብም ከአበ ነፍሱ ጋር ተነጋግሮና ተሰነባብቶ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ አበ ነፍስን መቀየር አይቻልም፡፡ አሁንም የተጓዝክበት መንገድ ትክክል ባለመሆኑ ሁሉንም አባቶች ይቅርታ ጠይቀህ፤ ቀኖና ተቀብለህ ስታጠናቅቅ ሊያሰናብቱህ ይገባል፡፡ በመካከላችሁ ያለውን አለመግባባት በመፍታት ከተግባባችሁ ግን ከአንዳቸው ጋር ትቀጥላለህ፡፡ አበ ነፍስ መቀያየር መፍትሔ አይሆንህም፡፡  ካልተሳካልህ ብቻ ነው አሰናብተውህ ወደ እኔ የምትመጣው፡፡” አሉኝ በተረጋጋና  አነጋገር፡፡

 

በድንጋጤ ደነዘዝኩኝ፡፡ ፍጹም ያልጠበቅሁት ውሳኔ፡፡ “እንዴት እችላለሁ አባቴ?” አልኩኝ  እየተርበተበትኩ፡፡

“በትክክል የቤተክርስቲያን ልጅ ነኝ ብለህ የምታምን ከሆነ ሥርአቷንም የመጠበቅ ግዴታ አለብህ፡፡” አሉኝ ኮስተር ብለው፡፡

 

አቋማቸው የሚወላውል አልነበረም፡፡ ትክክል እንደሆኑ ውስጤ አምኖበታል፡፡ ነገር ግን አሻፈረኝ ብዬ ከኮበለልኩባቸው አባቶች እግር ስር ወድቄ ይቅርታ መጠየቁ ተራራ የመውጣት ያህል ከብዶ ታየኝ፡፡

 

ጭንቅላቴን እያሻሹ “አይዞህ፡፡ ክርስትና የሚኖሩት እንጂ በአቋራጭ ለክብር የሚበቁበት መድረክ አይደለም፡፡ በማስተዋል መጓዝ ይገባሃል፡፡” ብለው አቡነ ዘበሰማያት ደግመው፤ በእግዚአብሔር ይፍታህ ደምድመው ተሰናብተውኝ ከአጠገቤ ሔዱ፡፡

 

ተንበርክከኬ የቻልኩትን ያህል አነባሁ፡፡ ትኩስ የሚያቃጥል ዕንባ ፈሰሰኝ፡፡ መረጋጋት ተሳነኝ፡፡፡ለረጅም ደቂቃዎች እንደተንበረከክሁ ቆየሁ፡፡

 

ጉዞ ወደ መጀመሪያው አበ ነፍሴ . . . ፡፡

 

ለሦስት ቀናት ያህል ከራሴ ጋር ስሟገት ቆይቼ በሌሊት አዲስ አበባ ወደሚገኘው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አመራሁ፡፡ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቼ የኪዳን ጸሎት እስከሚጀመር ድረስ የግል ጸሎቴን አደረስኩ፡፡

 

የኪዳን ጸሎት እየደረሰ ሳለ እግረ መንገዴን የንስሐ አባቴን ፍለጋ ዐይኖቼን አንከራተትኩ፡፡ አልነበሩም፡፡ ከኪዳን ጸሎት በኋላ በየመጠለያው ፈለግኋቸው፡፡ የሉም፡፡

 

ወደ አንድ አባት ጠጋ ብዬ “ይቅርታ አባቴ መምሬ ወልደ ገብርኤልን ፈልጌ ነበር፡፡ የት አገኛቸው ይሆን?” አልኳቸው፡፡

በደንብ ካስተዋሉኝ በኋላ “መምሬ ወልደ ገብርኤል የሚባሉ እዚህ የሉም፡፡” አሉኝ፡:

“ተቀይረው ይሆን?” ጥርጣሬዬን ገለጽኩላቸው፡፡

“አልሰማህም እንዴ? እሳቸው እኮ ካረፉ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡”

አፌ ተሳሰረ፡፡ ድንጋጤ ወረረኝ እኔ የገደልኳቸው ያህል ተሰማኝ፡፡

“እሰከ ዛሬ እንዴት አላወቅህም?”

“አላወቅሁም አባቴ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡” አልኩኝ ባደረግሁት አሳፋሪ ተግባር በመጸጸት፡፡ ራሴን እየወቀስኩ ካህኑን አመስግኜ ከግቢው ወጣሁ፡፡

 

ሁለተኛውን አበ ነፍሴን ለማግኘት ጥረት አደረግሁ፡፡ የንስሐ ልጆቻቸውን ለሚቀርቧቸውና ለሚያምኗቸው አባቶች ሰጥተው ወደ አውሮፓ መጓዛቸውን አረጋገጥኩ፡፡

 

ሦስተኛው አበ ነፍሴን ፍለጋ ቀጠልኩ . . .፡፡

 

ተሳካልኝ፡፡ የፈጸምኩትን ድርጊት በመጸጸት ነገርኳቸው፡፡ በተፈጥሮ ቁጡና በክርስትና ሕይወት ወለም ዘለም ማለት አያስፈልግም የሚል አቋም ስላላቸው ለመጥፋቴ ምክንያት እንደሆኑኝ ከመንገር ወደ ኋላ አላልኩም፡፡

 

“ልጄ ፈተና ሆንኩብህ? በመጥፋትህ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ተመልሰህ በመምጣትህ ደስ ብሎኛል፡፡” በማለት በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ቀጥለውም ”መቆጣቴ ለክፋት ሳይሆን ክርስትና በዋዛ ፈዛዛ የሚኖሩት ባለመሆኑና መንፈሳዊ ጥንካሬን የሚጠይቅ፤ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ ስለማምን ልጆቼን ለማጠንከር ነው፡፡ ክርስትና እንደ ወርቅ ተፈትኖ ነጥሮ መውጣትን ይፈልጋልና፡፡ ስለዚህ ልጄ አትቀየመኝ፡፡” በማለት እንድረጋጋ መንገዶችን አመቻቹልኝ፡፡ ቁጡነታቸው ስለሚያስፈራ እንዴት አድርጌ እፊታቸው እቆማለሁ? እያልኩ ነበር ሳስብ የነበረው፡፡ ራሳቸውን መውቀስ ሲጀምሩ ተረጋገሁ፡፡

 

አጠገባቸው አስቀምጠው ጭንቅላቴን እያሻሹ “አየህ ልጄ! – የክርስትና ጉዞ እስከ ቀራንዮ ድረስ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ጉዞው ከባድና እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ተሸክመኸው የምትጓዘው መስቀሉን ነው፡፡ መውደቅ ፤መነሳት፤ መገረፍ ፤በችንካር መቸንከር ሕይወትንም ለእግዚአብሔር አሳልፎ እሰከ መስጠት ይደርሳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምንና የእኛን ልጆቹን በደል ይሽር ዘንድ፤ ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ነጻ ያወጣን ዘንድ አምላክ ሲሆን እንደኛ ስጋን ለበሰ፡፡ በቀራንዮ መስቀል ላይ የነገሠውን አምላካችንን አስብ፡፡ የጀመርከውን የቀራንዮ ጉዞ እንደ ሎጥ ሚስት ወይም እንደ ዴማስ ያለፈውን የኃጢአት ጉዞህን ለመመልከት ወደ ኋላ የምትዞርበት ሳይሆን ፊት ለፊት የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት ፤ በመስቀሉ ስር የተገኙትን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምንና ቅዱስ ዮሐንስን ትመለከት ዘንድ ነው፡፡ በርታ፡፡” አሉኝ በፍቅር እየተመለከቱኝ፡፡

 

የሚናገሩት ቃለ እግዚአብሔር ማር ማር እስኪለኝ ጣፈጠኝ፡፡

 

የእግዚአብሔር ቃል ምን ይላል መሰለህ? “የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፡፡ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሐ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዟል፡፡” በማለት በሐዋ. ሥራ. ምዕ.17፡30 ተጽፏል፡፡ ያለፈውን የኃጢአት ሥራዎችህን ተጠይፈህና ጥለህ በእግዚአብሔር እቅፍ ስር ትሆን ዘንድ መምረጥህ መልካም አደረግህ፡፡ ወደፊት ደግሞ ብዙ ይጠብቅሃል፡፡” አሉኝ በጥልቅ ትኩረት እየተመለከቱኝ፡፡

 

“አንድን የኃጢአት ግብር ከመፈጸሜ በፊት ላለመስራት እታገላለሁ፡፡ ነገር ግን ሰርቼው እገኛለሁ፡፡ ለራሴ ውሳኔዎች ውስጤን ማሰልጠን ፤ ማስጨከን ተሳነኝ፡፡” አልኳቸው በተሰበረ ልብ፡፡

 

“እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አያስቀርም፤ ይቀራል ብለው የሚናገሩ አሉና፤ ነገር ግን ስለ እነርሱ ይታገሳል፡፡ ማንም ይጠፋ ዘንድ አይሻምና ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለሰው ሁሉ ዕድሜን ይሰጣል እንጂ፡፡ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ጴጥ.3፡9 ላይ ገልጾታል፡፡ እግዚአብሔር ይመጣል በፊቱም እንቆማለን፡፡ መልሳችን ምን ይሆን? ማሰብ ያለብን ይህንን ነው፡፡ ንስሐ ለመግባት መወሰንህ መንፈሳዊ ጀግንነትህን ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ያለውን አያስቀርምና፡፡ በኋላ ከመጠየቅ ለመዳን ዛሬ ራስን ከኃጢአት በማራቅ ንስሐ መግባት ትክክለኛ መፍትሔ ነው፡፡” በማለት ሕሊናን ሰርስረው የሚገቡ የተመረጡ ቃላት በልቦናዬ ውስጥ አፈሰሱት፡፡ መልስ አልነበረኝም፡፡ ዝምታን መረጥኩ፡፡

 

“አሁን ውሳኔህን አሳውቀኝ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እኔ መልሶ ያመጣህ ምክንያት ቢኖረው ነው፡፡ ይህንን ሃላፊነቴን እወጣ ዘንድ ግድ ይለኛል፡፡ አባት እሆንሀለሁ አንተም ልጄ ትሆናለህ” አሉኝ፡፡

 

“አመጣጤ እንዲያሰናብቱኝ ለመማጸን ነበር፡፡ ምን ያህል ስህተት ውስጥ እንደነበርኩ ተረድቻለሁ፡፡ ለዚህም የረዱኝን አባት ማመስገን አለብኝ፡፡ እግዚአብሔር ሰብሮኛል፡፡ ይጠግነኛልም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን እናፍቃለሁ፡፡ ይህ ባይሆን ተመልሼ እርስዎ ዘንድ አልመጣም ነበር፡፡ እንደወጣሁም እቀር ነበር፡፡ የመጣሁት ወስኜ ነው፡፡  እግዚአብሔር እርስዎን ሰጥቶኛልና እዳ እንዳልሆንብዎ እርዱኝ፡፡” አልኩ፡፡

 

“ቆም ብለህ ራስህን እንድታይ ያስፈልጋል፡፡ የሰራኸውን ኃጢአት እግዚአብሔርን በመፍራት ፤ በተሰበረ መንፈስ ውስጥ ሆነህ ልትናዘዝ ይገባሃል፡፡” አሉኝ ለመስማት ራሳቸውን እያዘጋጁ፡፡

 

ውስጤ የታጨቁትን የኃጢአት ኮተቶች ሁሉ አራገፍኩ፡፡

 

“ወደ ልቦናህ ተመልሰህ ከውስጥህ ያለውን ሁሉ አውጥተህ ዳግም ላትመለስበት ወስነሃልና የሚገባህን ቀኖና እሰጥሃለሁ፡፡ የሚሰጥህን ቀኖና በአግባበቡ በማስተዋልና በፍቅር ልትፈጽመው ይገባል፡፡ በጾም ፤ በጸሎት ፤በስግደትና በትሩፋት ከበረታህ የሚፈታተንህን ክፉ መንፈስ ማሸነፍ ትችላለህ፡፡” በማለት አባታዊ ምክራቸውን ከለገሱኝ በኋላ አስፈላጊ ነው ያሉትን ቀኖና ሰጡኝ፡፡ በአቡነ ዘበሰማያትና በእግዚአብሔር ይፍታህ ተደመደመ፡፡

 

“በየሳምንቱ ቅዳሜ ማታ እዚሁ እየተገናኘን በመንፈሳዊ ሕይወትህ ዙሪያ የሚገጥምህ ችግር ካለ ፤ እንዲሁም አስፈላጊ ያልካቸውን ጉዳዮች ልታማክረኝ ትችላለህ፡፡” በማለት ካበረታቱኝ በኋላ አሰናበቱኝ፡፡

 

ከንስሐ አባቴ እንደተለያየሁ ያመራሁት ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ባለውለታዬ የሆኑትን አባት ለማመስገን፡፡

 

ክርስቲያናዊ ሕይወቴን ለማስተካከልና ራሴን ለመግዛት እግዚአብሔርን እየለመንኩ፤ የንስሐ አባቴ ምክርና ድጋፍ ሳይለየኝ በተረጋጋ መንፈስ ለመኖር ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊ ሕይወቴን ለሚያንጹ ተግባሮች ቅድሚያ ሰጠሁ፡፡ የአቅሜን ያህል በጾም፤ በስግደትና በጸሎት እየበረታሁ ነው፡፡ የንስሐ አባቴ በጥሩ ሁኔታ ቃለ እግዚአብሔር እየመገቡኝ ፤ ስደክም እያበረቱኝ መፈርጠጤን ትቼ ለሌሎች መካሪ ሆኛለሁ፡፡ ራስን መግዛት ተማርኩኝ፡፡ ያለፈው በኃጢአት የኖርኩበት ዘመን ዳግም ላይመለስ መንፈሳዊ ጋሻና ጦሬን አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ ነገን ደግሞ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ እኖራለሁ. . . ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር