መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን
ክፍል አንድ
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ታኅሣሥ ፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
ውድ የዚህ ጽሑፍ አንባብያን! እንዴት ሰነበታችሁ? እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ‹‹መልካም አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ ተከታታይ ጽሑፍ እናደርሳችኋለንና ተከታተሉን፡፡
መልካም አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው የሚሠራ ሳይሆን ተሠርቶ የተጠናቀቀ መዋቅር ባለቤት ናት፡፡ የመንግሥት መዋቅር በሌለበት ቦታ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡ ከአጥቢያ እስከ አንድ ግለሰብ መኖሪያ ድረስ ቤተ ክርስቲያን አለች፡፡
በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሊቃውንትን፣ ካህናትን፣ መነኮሳትን፣ ዲያቆናትን፣ መዘምራንን፣ ምእመናንንና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የምታስተዳድር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ብዙ የሰው ኃይል በማስተዳደር የሀገር ሸክምን ያቃለለች፣ የብዙ ሰዎችን ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወት የቀየረች፣ ለተራቡ ሁሉ ምግበ ሥጋ፥ ምግበ ነፍስ የምትመግብ ናት፡፡ የታመሙ የሚፈወሱባት፣ ያዘኑ የሚጽናኑባት፣ የተሰበሩ የሚጠገኑባት፣ የፈውስ፣ የድኅነት መገኛ መሆኗን ዓለም ያወቀው እውነት ነው፡፡
ለበርካታ ዓመታት ይህን ጽኑ ተግባር ስትፈጽም ከዚህ የደረሰችው ሥጋዊና መንፈሳዊ ጥበብ በተሞሉ መሪዎችና አገልጋዮች ከፍተኛ አስተዳደራዊ ጥበብና መሥዋዕትነት ነው፡፡ ሥርዓተ መንግሥት አንድ ሺህ አንድ ጊዜ ፈርሶ ተሠርቷል፡፡ ምክንያቱም የሚመሩት ሥጋዊ ጥበብ ቢኖራቸው መንፈሳዊ ጥበብ የሚድጎላቸው ናቸውና፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ጥበብ የጎደላቸው እና ፍቅረ ንዋይ የሚገዳደራቸው አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ በመኖራቸው እየተፈተነች በከፋ የአስተዳደር ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡
መልካም አስተዳደር ማለት ምን ማለት ነው?
ዓለም በአሁኑ ጊዜ ትልቅ አጀንዳ ከሚያደርጋቸው ጉዳዮች ዋናው መልካም አስተዳደር ነው፡፡ መልካም አስተዳደር መገለጫው ብዙ ነው፤ እንደ የተቋማቱ ባሕርይ፣ የሥራ ሁኔታ በልዩ ልዩ ሁኔታ ሊገለጽ የሚችል ቢሆንም የጋራ ባሕርያት ይኖሩታል፡፡
ይሁን እንጂ መልካም አስተዳደር ውጤታማነት፣ ጥራት፣ የተገልጋዮችን ነጻነት የሚያከብር፣ አድልዎ የሌለባት፣ የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና ግልጸኝነት፣ ያለው አገልግሎት መስጠትን፣ መልስ ሰጭነትን፣ ኃላፊነት መውሰድን፣ አሳታፊነት፣ ፍትሐዊነትና ስልታዊ የሆነ ርእይ መያዝን የሚያካትት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ መልካም አስተዳደር ካለ ሥልጣን ለያዙ ሰዎች ላይ ሕጋዊ ገደብ የሚያስቀጥ እና ሥልጣን በተወሰኑ በተጨማሪም መልካም አስተዳደር ግለሰቦች ሥር እንዳይሆን የሚያደርግ ነው፡፡
መልካም አስተዳደርን ከቤተ ክርስቲያን አኳያ ብፁዕ አቡነ አስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ለሥራ ኃላፊዎች በሐምሌ ፳፻፭ ዓ.ም በተሰጠ ሥልጠና ላይ ተገኝተው እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡
‹‹መልካም አስተዳደር ማለት ከእግዚአብሔር በተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት የተሟላ መንፈሳዊ አገልግሎት በመስጠት በሁሉም መስክ በጎ አርአያነት ያለው መልካም እረኛ መሆን ነው፡፡›› የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በድረ ገጹ በለቀቀው አንድ ጽሑፍ ላይ ደግሞ ‹‹መልካም አስተዳደር ማለት በአገልጋይና በተገልጋይ መካከል በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር›› ማለት እንደሆነ ያትታል፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲገለጽ መልካም አስተዳደር የሚባለው ሐሳብ ከውሳኔ አሰጣጥ ሂደትና የተወሰነውን ውሳኔ ከማስፈጸም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም ለተገልጋዮች ፍላጎት ተገቢ ምላሽ የሚሰጥ፣ መብታቸውን የሚያስጠብቅ፣ አገልግሎት የሚያቀርብ እና ሕጎችን ተግባራዊ የሚያደርግ የአስተዳደር ሥርዓት ሁሉ መልካም አስተዳደር ሊባል እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የምንለው ምኑን ነው?
በዓለም ያሉ ተቋማት ቢያስተዳድሩ የተወሰነ ጉዳይን ነው፤ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ግን ሥጋውንም፣ መንፈሳዊውንም ያቀፍ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ ይህም ከሰው ሀብት አስተዳደር፣ ከፋይናንስ አስተዳደር እና የንብረት አስተዳደር በተጨማሪ መንፈሳዊ አስተምህሮውም ያካተተ በመሆኑ ነው፡፡
ሀ. የሰው ሀብት አስተዳደር
የአንድ ተቋም ህልውናው የሚረጋገጠው ዋናውና የመጀመሪያው የሰው ሀብት አስተዳደሩ ነው፤ ተቋም ውጤታማ ለመሆን በጠንካራ፣ በብቁና በሥነ ምግባሩ ምስጉን የሆነ የሰው ኃይል መዋቀር አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራንና ሌሎችም በልዩ ልዩ ሙያ የሚያገለግሎ ምእመናንን በርካታ የሰው ኃይል ታስተዳድራለች፡፡ እነዚህ አገልጋዮች ብዙኃኑ ጠንካሮችና በጥብቅ ሥነ ምግባር የሚመሩ፣ የሥጋዊና መንፈሳዊ ዕውቀት ባለቤቶች ስለ ነበሩ ቤተ ክርስቲያኗ በማዕበልና በወጀብ ውስጥ አልፋ ለእኛ ልትደርስ ችላለች፡፡
ለ. የንብረት አስተዳደር
ቤተ ክርስቲያን እጅግ ግዙፍ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ቁጥራቸው ከአርባ ሺህ በላይ አድባራትና ገዳማትን፣ በርካታ የመሬት ይዞታዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ኮሌጆችን፣ ልማት ተቋማትን፣ ሕንፃዎችን፣ የጸበል ቦታዎችን እና ተሽከሪካረዎችን የአገልግሎት መስጫዎችን፣ መኪኖችን ከመንበረ ፓትርያሪክ እስከ አጥቢያ ድረስ ታስተዳድራለች፡፡
ሐ. የፋይናንስ አስተዳደር
በገንዘብ አስተዳደር በኩልም በስእለት፣ በዐሥራት በኩራት፣ በልማት፣ በኪራይ፣ በርዳታ፣ በስጦታ፣ በጸበል እና በልዩ ልዩ አገልግሎት ምክንያት የሚሰበሰብ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ታስተዳድራለች፤ ታንቀሳቅሳለች፡፡
መ. የምእመናን አስተዳደር
መንግሥትም ሕዝብን ቢያስተዳድር በኃይል ታግዞ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ምእመናንን ታስተዳድራለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድ ተቋም እንደሚያደርገው በሥሯ የሚያገለግሉትን ብቻ ሳይሆን ምእመናንን በሥጋዊና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ትልቅ ኃላፊነት ወስዳ በኃይል ሳይሆን በሰላም በጠብ ያይደለ በፍቅር ታሰተዳድራለች፤ ትጠብቀለች፡፡
ሠ. የመንፈሳዊ ሀብት አሰተዳደር
ቤተ ክርስቲያን ሌላም ድርብ አስተዳደራዊ ኃላፊነት አለባት፡፡ እርሱም የማይዳሰሰውንና በቁሳዊ ዋጋ የማይተመነውን መንፈሳዊ ሀብት ማስተዳደር ነው፡፡ ይህም ዜማውን፣ ቅኔውን፣ ሥነ ጥበባዊ ዕውቀቱን፣ ሥነ ጽሑፋዊ ሀብቱ፣ ሥነ ሥዕሉን ሁሉ መንፈሳዊ ዋጋ ያለውን፣ መለያዋ የሆነውን ትጠብቃለች፤ ታስተዳድራለች፡፡ ከምንም በላይ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮውን፣ ትውፊቱን፣ ዶግማውን ከቀኖና አስተባብራ ትጠብቃለች፤ እንዳይቀሰጥና እንዳይሸራረፍ ታሰተዳድራለች፡፡
የተወዳጆችሁ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች! ለዛሬ በዚህ አበቃን! ‹‹የመልካም አስተዳደር እጦት በቤተ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ ሁለተኛውን ክፍል ይዘንላችሁ እስክንቀርብ ቸር እንሰንብት! አሜን!