ቅዱስነታቸው በጥር ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የሰጡት የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ
ለሚመለከተው ሁሉ!
እሑድ ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሦስት ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት በተፈጸመው የሕግ ጥሰት ፳፮ ኤጲስ ቆጶሳት በመሾማቸው፣ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ቋሚ ሲኖዶስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ላሉት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት አስቸኳይ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
ጥሪ የተደረገላቸው አባቶችም በቅጽበት ደርሰው ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ አድርገው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት ከላይ በተጠቀሰው ኢሕጋዊ ድርጊት ላይ ውሳኔ ማሳለፋቸው በዚያው ዕለት ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ዓ.ም በተላለፈው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ በሰፊው ተገልጿል፡፡
መግለጫውን ያዳመጡ በውስጥም በውጭም ያሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ሁሉ ብርቱ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት እና መንፈሳውያን ተቋማት ድጋፋቸው ከመግለጻቸው በላይ የታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ኅብረት ተጠብቆ እንዲኖርም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
እኛም ድጋፋቸውንና መልካም ምኞታቸውን ስለገለጹልን የላቀ ምስጋና እናቀርብላቸዋለን፤ ምስጋናችን በያሉበት ይድረሳቸው፡፡
የሃይማኖት ተቋማት የበላይ ጠባቂዎች የክርስትናና የእስልምና መሪዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደረሰው ድንገተኛ ክስተት ተደናግጠውና ተጨንቀው መጥተው የችግራችን ተካፋይ መሆናቸውን በመንፈሳዊ ስሜት ገልጸውልናልና ምስጋናችን ይድረሳቸው፤ እግዚአብሔርም ያክብራቸው እንላለን።
አሁንም በድጋሚ ለመንግሥትና ለሰፊው ሕዝባችን የምናስተላልፈው የአደራ መልእክት አለን፤ እሱም፡-
፩.የታሪካዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት (ቀኖና) እንዲከበር፤
፪.ጸጥታ እንዳይደፈርስና የንጹሐን ክርስቲያን ደም እንዳይፈስ ከወዲሁ ብርቱ ጥንቃቄ የተመላበት ጥበቃ እንዲደረግ በእግዚአብሔር ስም በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ