ሕገ ወጥ ሕግ አስከባሪዎች
ሚያዝያ 24/2004 ዓ.ም.
ከሰሞኑ ለሰሚ የሚያሳፍር፤ አንድ ጉዳይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተፈጽሟል፡፡ ጉዳዩን በአንክሮ ለተመለከተው በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የሰላ አንደበት ይዘው ያልኾኑትን ነን በማለት የሌላቸውን ሥልጣንና ዕውቀት እንዳላቸው በማስመሰል ደግ አባቶችን የሚያታልሉ፤ ከቤተ ክርስቲያን ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን የሚያስቀድሙ ወረበሎች አሉ፡፡ እነዚህ ጆቢራዎች በደጋግ አባቶቻችን አእጋር ሥር እየተርመሰመሱ፤ ዕውቀት መንፈሳዊ ሳያቋርጥ የሚያፈሰውን የእናት ቤተ ክርስቲያን ጡት እየጠቡ አድገውና ጐልምሰው ሊያገለግሉ በተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከል እየተሹለከለኩ ተንኮላቸውን ያለድካም ለመፈጸም ሲኳትኑ ይታያሉ፡፡ ከሰሞኑ የሰማነው ግብዝነትን ከአላዋቂነት ጋር አስተባብሮ የያዘ ከንቱ ተግባር፤ እነዚሀን መሰሪዎች አበው በበሰለ አመራራቸው ለይተው በመጠረቅ ከጉያቸው የሚያባርሩበት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም በዕውቀት ሚዛን መዝነው ማኔ ቴቄል ፋሬስ ብለው ለይተው የሚጥሉበት ሰዓት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መድረሱን የሚያመለክት ነው፡፡ ጊዜ ለሚሰጠው እንጂ ለማይሰጠው ጉዳይ መዘግየት ጉዳቱ ለራስ ነውና፡፡
ጉዳዩ በማኅበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴ ጥቅማቸው የተነካ ወይም የሚነካ በመሰላቸው ሰዎች ተቀነባብሮ የነበረ ሴራ ነው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ማኅበሩ በአባቶች መመሪያና ምክር እንዲሁም ጸሎት እየታገዘ የነበረ አገልግሎቱን በተጠናከረ መንገድ ቀጥሎ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ከሕግና ትእዛዝ ፍጹም እንደወጣ አድርገው በማቅረብ በአገልግሎቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያመጣ ደብዳቤ ተፈርሞ እንዲበተን ለማድረግ ያደረጉት ከንቱ ሙከራ ነው፡፡ ግለሰቦቹ ይህንን እኩይ፣ በእግዚአብሔርና በሰው ሕግጋት የሚያስጠይቅ ተግባር ለማሳካት ያላደረጉት ጥረት ለአባቶችም ያልቀባጠሩት ማሳመኛ የሚመስል ነገር የለም፡፡ የእኩይ ተግባራቸው መነሻ ያደረጉት ለማኅበሩ እንዲደርስ ያሉትን ማሩን የሚያመር ወተቱን የሚያጠቁር የክስ ደብዳቤ ማርቀቅ ነው፡፡ ለደብዳቤው ርዕሰ ጉዳይነት የመረጡት ዐረፍተ ነገር «ለሕግ የበላይነት ሥልጣን ታዛዥ ሆኖ አለመገኘትን በሚመለከት ይሆናል» የሚል የአማርኛ ሰዋስው ሀሁን ያላለፈ በዚህም የጆቢራዎቹን ማንነት የገለጠ ያልተሟላ ዐረፍተ ነገር ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይነት የታሠረው ከንቱ ደብዳቤ በወግ ባልተጻፈ፤ ርዝመታቸው በትልልቅ አናቅጽ ማሠሪያ የተገታ ከሳሽ ዐረፍተ ነገሮች ታጅሏል፡፡ የደብዳቤው ፍሬ ሐሳብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ፊርማ በጸደቀ ደንብ የተቋቋመው፤ በደንቡም ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዐን አበው ተግሣጽ፣ ምክርና መመሪያ እየታገዘ አገልግሎቱን እየፈጸመ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያኗ ማእከላዊ አስተዳደር ቁጥጥር ውጪ ነው፤ በዚህም የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አልኾነም የሚል ነው፡፡ ደብዳቤው ይኽንኑ እንቢተኝነት ለመቀልበስ በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና በማኅበሩ መካከል «በዕለት፣ በሳምንት፣ በወርና በዓመት ያልተገደበ የመጻጻፍ ተግባር» ሲካሔድ እንደቆየ ያትታል፡፡ ደብዳቤ መጻጻፉ አሁንም «ከመቼውም ጊዜ ጐልቶ የታየበት ወቅት» እንደኾነም ያስረግጣል፡፡ ይህም የማኅበሩን «የበላይ ተጠሪ የሆነውን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያን» ለወቀሳ የዳረገ መኾኑን ይጠቅስና፤ ማኅበሩ በዚህ ተግባሩ የመምሪያውንም ኾነ የቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ አስተዳደር ህልውና እየተፈታተነ እንደኾነ በሬ ወለደ አሉባልታውን ይነዛል፡፡ ለዚህም ማሥረጃ ይጠቅሳል፡፡
መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም «ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና ድርጅቶች ሓላፊዎች እንዲሁም የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚዎች ወዘተ በተገኙበት የተሰጠውን ባለ 6 ነጥብ «የሥራ አፈጻጸም መመሪያ» ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም ይላል፡፡ በማከልም በዚህ የተነሣ ለደረሰው ችግር ማኅበሩን ተጠያቂ በማድረግ፤ ጉዳዩ በቤተ ክርስቲያኗ «ሊኖር የሚገባውን የሥልጣን ተዋረድ የሚሸራርፍ ሆኖ ከመታየቱም በላይ የማእከሉን አስተዳደርና ኃላፊነት ድርሻ የሚጐዳ አካሔድ ያለው» ነው ይልና፤ የማኅበሩ አልታዘዝ ባይነትና ሕጋዊ ያልኾነ እንቅስቃሴ በፍጥነት መታረም እንዳለበት ታምኖበታል ይላል፡፡ ደብዳቤው ይህንን ሁሉ ካለ በኋላ መመሪያ ወደ ማውረድ ይገባል፡፡ «ስለዚህ ይህ ደብዳቤ በደረሳችሁ ከ10 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ቀደም ሲል መስከረም 12 ቀን 2002 ዓ.ም በምልዓተ ጉባኤ ተወስኖ በተላለፈላችሁ ቃለ ጉባኤ የተቀመጡትን ስድስት ነጥቦች ተግባራዊ እንድታደርጉ እያስገነዘብን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ካልቀረበ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ መመሪያዎች የተቀመጠውን ድንጋጌ ለማስከበር ሲባል አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚደረግ መሆኑን እናስታውቃለን» በማለት መመሪያውን በማዥጐድጐድ ያጠቃልላል፡፡
ጆቢራዎቹ ይህንን ደብዳቤ አርቅቀው በኮምፒውተር ከጨረሱ በኋላ ቀጣይ ከይሲያዊ ተግባራቸው ያደረጉት፤ ደብዳቤው በማደራጃ መምሪያው ሓላፊ ፊርማ ለማኅበሩ እንዲሰጠው ነውና ዓላማው፤ የመምሪያው ሓላፊ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርግ ድምጽ ወደ መፈለግ ገቡ፡፡ አወጡ አወረዱ፡፡ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ ወዳሏቸው አባትም ምላሳቸውን አስረዝመው፣ አለባበሳቸውን አሳምረው፣ ያሳምናል ያሉትን ውሸት ቀምረው ቀረቡ፡፡ ቀመራቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ እንዲጻፍ አዝዘዋልና የመምሪያ ሓላፊው በተዘጋጀው ደብዳቤ እንዲፈርሙ ትእዛዝ ይስጡ የሚል ነበር፡፡ ደጉ አባትም የጆቢራዎቹን ቃል ሰምተው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊን ጠርተው እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ተዘጋጅቷልና ይፈርሙ ይሏቸዋል፡፡ በጉዳዩ ግራ የተጋቡት የመምሪያው ሓላፊም ደብዳቤውን ሲያነቡ በእሳቸው ስም ሊወጣ የማይችል መኾኑንና ለጉዳዩም እውቅና እንደማይሰጡ መመሪያውን ለሰጧቸው አባት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሂደት ጆቢራዎቹ ያሰብነው ተሳካ በሚል በመረጡት ሆቴል ፌስታ ያደርጋሉ፡፡ ሁለቱ አባቶች ግን ተመካክረው ጉዳዩ እንዲዘገይ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሒደት ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይሰሙና ጉዳዩን አዝዘው እንደኾነ ቅዱስ ፓትርያርኩን ይጠይቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ማኅበሩን ዕለት ዕለት እያቀረቡ በመምከር ላይ ያሉት ቅዱስነታቸውም በእሳቸው ስም በተሠራው ወንጀል አዝነው ደብዳቤው ተሠራጭቶ እንደኾነ በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ ያዝዛሉ፡፡ የጆቢራዎቹ ከይሲያዊ እንቅስቃሴ በዚህ መንገድ ተኮላሸ፡፡ እውነት የለውምና፡፡
ለመኾኑ ጆቢራዎቹ እነማን ናቸው?
ይህ ከባድ ወንጀል በማኅበሩ ላይ ስለተፈጸመ ሳይኾን ድርጊቱ በቤተ ክህነታችን ውስጥ እየተፈጸመ ስላለውና ወደፊትም ሊፈጸም ከሚችለው ከባድ ጥፋት አንጻር ስለነዚህ ግለሰቦች ወደፊት በዝርዝር እናሳውቃለን፡፡
በመሠረቱ ማኅበረ ቅዱሳን በሁሉም የቤተ ክህነት ደረጃ ሕግ እንዲከበር ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ለሕግና ሥርዓት መከበር ቀዳሚ ሓላፊነት ካለባቸው አባቶች ጋር በየጊዜው ይመካከራል፡፡ ቢኾን የሚለውንም በልጅነት ያቀርባል፡፡ ማኅበሩ ይህንን የሚያደርገው ራሱ አባቶች በሰጡት መመሪያ መሠረት ለመሄድ የቻለውን ሁሉ በማድረግ ነው፡፡ በዚህም ጆቢራዎቹ መደረግ አለበት ብለው ያወረዱትን «ትእዛዝ» ቀድሞም ሲያደርገው የነበረው፣ አሁንም እያደረገ ያለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክሮቹ ማኅበሩን መመሪያ በመስጠትና እንቅስቃሴውን በመከታተል የሚያሠሩት አባቶች ናቸው፡፡
ማኅበሩ ዘወትር እንደሚለው፤ የቤተ ክርስቲያኗን ማእከላዊ አስተዳደር ጠብቆ በአባቶች መመሪያና ቁጥጥር እንደሚሠራ ምንም ዓይነት ብዥታ ሊኖር አይገባም፡፡ ሕግን አክብሮ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግ እንዲከበር በተግባር የሚታገል ነውና፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያኗ በምትጠይቀው አግባብ ሁሉ ራሱን ለማሳየት ዝግጁ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን የተቋቋመ ነውና፡፡ ነገር ግን በማይመለከታቸው እየገቡ አባቶችን በማታለል ለሚሠነዘርበት ጥቃት አበውን ምስክር በማድረግ ምላሹን እየሠጠ ይሄዳል፡፡
ከማኅበሩ አልፎ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የኾነው የሰሞኑ የማታለል ተግባር በቤተ ክህነታችን እየኾነ ያለው አሳሳቢ H#ኔታ መገለጫ ነው፡፡ አባቶቻችን የነገርን ሁሉ በጐ ገጽታ መመልከትን ሀብት ያደረጉ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ወንጌል ለአነዋወራቸው ሁሉ መመሪያ ነውና፡፡ ነገር ግን ይህንን የዋሕነታቸውን ተጠቅመው በረዘመ ምላሳቸውና ራሳቸውን ለራሳቸው በሚፈጥሩት ከፍ ያለ ማንነታቸው በስማቸውና በፊርማቸው ወንጀል እንዳያሠሯቸው እንሰጋለን፡፡ ለዚህ ተግባራቸውም እውነትን ይዘው ከቆሙ ሊቃውንት ጋር ራሳቸውን አመሳስለው በአበው እግር ሥር መርመስመሳቸውን እናያለን፡፡ ይህ በቤተ ክህነታችን ሥር እያንዣበበ ያለው አደጋ በሁለም ጥረት በኖ ሊጠፋ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ በሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ማኅበራችን ንቁ ተሳትፎውን ይቀጥላል፡፡ ለዚህም የአባቶቻችን ምክርና መመሪያ እንደማይለየው ያምናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር