*ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እየገነባን እኛ ከቤቱ ርቀናል*
ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በደብረ ማርቆስ ማእከልና በዝግጅት ክፍሉ
ይህ ኃይለ ቃል የብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ንግግር ሲኾን፣ ኃይለ ቃሉን የተናገሩትም በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የባሕረ ጥምቀት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ዕለት ነው፡፡
በሥርዓቱ ላይም ብፁዕነታቸውን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ በከተማው የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናትና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ታቦተ ሕግ በማክበር፤ እንደዚሁም የምሥራቅ ጐጃም ዞን አስተዳደር፣ የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባና ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በዕለቱ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ የባሕረ ጥምቀቱ የመሠረት ድንጋይ በቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን (በበዓለ ኀምሳ) መቀመጡ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ የሚያሳይ መኾኑን ጠቅሰው *የቀድሞ አባቶቻችን ቤታቸዉ ሳይቀር ቤተ ክርስቲያን ነበር፤ በአሁኑ ሰዓት ግን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እየገነባን እኛ ከቤቱ ርቀናል፡፡ ስለኾነም ከኹሉም አስቀድሞ ራሳችንን ወደ ቤተ ክርስቲያን ማቅረብ ያስፈልጋል* ሲሉ አባታዊ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
ብፁዕነታቸው አያይዘውም በባሕረ ጥምቀቱ ቦታ ላይ የጸበል መጠመቂያ ገንዳ፣ ዐዉደ ምሕረት፣ አጥርና የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች እንደሚከናወኑና የግንባታዉ ጠቅላላ ወጪም ከ፲፰ እስከ ፳ ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቅ የባለሙያዎችን ጥናት መነሻ በማድረግ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ለቦታዉ መከበርና ለግንባታዉ መፋጠን ኹሉም ምእመናን ሃይማኖታዊ ሓላፊታቸዉን መወጣት እንደሚገባቸው አባታዊ ምክራቸዉን ለግሰዋል፡፡
የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን ቆሞስ አባ እንባቆም ጫኔ የባሕረ ጥምቀቱን ቦታ አስመልክቶ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከኰሚቴው ጎን በመሰለፍ ቦታውን ለማስከበር ልዩ ልዩ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረውን የደብረ ማርቆስ ሕዝብ አመስግነው *ይህንን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥራ በመፈጸም ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል መላው ሕዝበ ክርስቲያን በጸሎቱ፣ በዐሳቡ፣ በዕውቀቱ፣ በገንዘቡና በጉልበቱ ድጋፉ እንዳይለየን* ሲሉ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የምሥራቅ ጐጃም ዞን አስተዳዳሪ አቶ ምግባሩ ከበደ በዕለቱ ንግግር ሲያደርጉ *ጥያቄያችሁ መልስ በማግኘቱ እንኳን ደስ አላችሁ* ካሉ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱን *ቤተ ክርስቲያን ለረዥም ጊዜ ጠብቃ ያቆየችዉን ወርቃማ የሥነ ምግባር፣ የሰላምና የፍቅር አስተምህሮ የማስጠበቂያ ቦታ ማድረግ ይገባል* ብለዋል፡፡
በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ማርቆስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የዕለቱ መርሐ ግብር ተፈጽሟል፡፡
የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት በብፁዕ አቡነ ማርቆስ መመሪያ ሰጭነት መስከረም ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በተቋቋመው ኰሚቴ ጥያቄ መሠረት ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለባሕረ ጥምቀት አገልግሎት የሚዉል ፶ ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ መረከቡን ከደብረ ማርቆስ ማእከል የደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡