ሐዊረ ሕይወት በሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን
ሚያዚያ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ሪፖርታዥ
መጋቢት 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ሌሊት
ማኅበረ ቅዱሳን ወደ ሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀው የሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ መርሐ ግብር ላይ ለመሳተፍ ምእመናን ከሌሊቱ 12፤00 ጀምሮ አምስት ኪሎ በሚገኘው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም እና በማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ዙሪያ በመሰባሰብ ወደ ተዘጋጁት መኪናዎች ለመግባት ይጠባበቃሉ፡፡ እያንዳንዳቸው 61 ሰው የመጫን አቅም ያላቸው 85 አንደኛ ደረጃ አውቶቡሶች ከናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤት እስከ ማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ፤ እንዲሁም ከትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት እሰከ መንበረ ፓትረያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ሰልፋቸውን ይዘው፤ በሮቻቸውን ከፍተው ምእመናንን በመጫን ላይ ተጠምደዋል፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች አካባቢው በመኪናና ሰው እንዳይጨናነቅ ያስተባብራሉ፡፡
ምእመናን በሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አስተባባሪዎች አማካይነት የጉዞ ቲኬታቸውን እያሳዩ ለጉዞው የተዘጋጀውን ባጅ እየተቀበሉ ወደ ተዘጋጀላቸው አውቶቡሶች ይገባሉ፡፡ ለምእመናን የተዘጋጀው ባጅ ሁለት መልእክቶችን ያዘለ ሲሆን በጽህፈት ቤት ግንባታ አብይ ኮሚቴ የተዘጋጀው ሰረገላ አስክንድር /በማኅበሩ ሕንፃ ላይ አሳንሰር ለመግጠም እንዲቻል ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ ባለ 15፤ 150 እና ባለ 600 ብር ቲኬት በሽያጭ ላይ ስለመሆኑ የሚልገጽ ባጅ/ ፤ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚቆይ ለአብነት ትምህርት ቤቶች የጽዳት እቃዎች ማሰባሰቢ ሳምንት በሚል ለኣብነት ትምህርት ተማሪዎች የሚሆኑ የተለያዩ ለጽዳትና ለምግብ ማብሰያና መጠጫ፤ ለአካባቢና ለግል ንጽህና መጠበቂያ የሚሆኑ ቁሳቁስ ምእመናን እንዲለግሱ የሚያሳስብ ባጅ ነው፡፡
ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ መኪናዎቹ ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ ማእከላት ተጓዦቻቸውን ይዘው ወደ ሆለታ በመሔድ ላይ ናቸው፡፡
መርሐ ግብሩን በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ የሚገኙት የIT ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች የተዘጋጀላቸው መኪና በምእመናን በመያዙ ምክንያት ለስርጭቱ የሚያገለግሉትን የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ሌሎች መገልገያ እቃዎች በፒክ አፕ መኪና ላይ ጭነው እነሱም ከእቃዎቹ ጋር /ፍጹም፤ ቴዲ፤ ኤይተነው፤ ብዙአየሁ፤ ሄኖክ/ ተጭነዋል፡፡ እኔና በሥርጭቱ ወቅት ጽሁፎችን በመጻፍ እገዛ የምታደርግልን ጸሐፊያችን የምስራች ገቢና ቦታ ተይዞልናል፡፡ የ30 ኪሎ ሜትሩን መንገድ የመኪናውን ፍጥነትና የንፈሱን ግርፋት ተቋቁመው ወደ ሆለታ በሰልፍ የሚተሙት አውቶቡሶችን በማለፍ፤ አልፎ አልፎም ወርደን በካሜራችን የአውቶቡሶቹን በረድፍ መትመም እየቀረጽን ሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲቲያን ደረስን፡፡
በሰፊ ይዞታ ላይ ያረፈው የሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን የሙያ አገልግሎት ክፍል ባለሙያዎች ዲዛይኑ ተዘጋጅቶ በነፃ የተሰጠ ሲሆን ግንባታው በመፋጠን ላይ ነው፡፡ ከአዲሱ ሕንፃ በስተ ምስራቅ አቅጣጫ በ1968 ዓ.ም. የተተከለው አነስተኛ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የደብሩ አስተዳደር ጽ/ቤት፤ የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት አነስተኛ አዳራሽ፤ ለአጸደ ሕጻናት መማሪያነት የተሰሩ አራት ክፍሎች . . . በቤተ ክርሰቲያኑ ዙሪያ ይገኛሉ፡፡
ቀድመውን የደረሱት አውቶቡሶች ምእመናንን አውርደው በተዘጋጀላቸው ስፍራ ላይ ተደርድረዋል፡፡ ምእመናን ከአውቶቡሶቹ እየወረዱ ቤተ ክርስቲያን እየተሳለሙ በአስተናጋጆች አማካይነት ወደ ተዘጋጀው የዳቦ መክፈልት እየተቀበሉ ወደ ተዘጋጀው ደንኳን በማምራት ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡
ጠዋት
ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለመርሐ ግብሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቡራኬያቸውን ለመስጠት በሆለታ በደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተዋል፡፡ የደብሩ የአቋቋም የአብነት መምህራንና ተማሪዎች የአቋቋም ትምህርት ሂደት ለማሳየት መምህራቸውን ከብበው፤ በዝማሬ ትምህርታቸውን ይወጣሉ፡፡ መምህሩ ቀለምና ዜማ እንዳይሰበር ይቆጣጠራሉ፡፡ ቀለም የሚስተውን ወይም ዜማ የሚሰብር ካጋጠማቸው አስተካክል በሚል በዓይናቸው ገረፍ ያደርጉታል፡፡
ከጠዋቱ 3፡30 ሰዓት ሲሆን በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ዑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነትና ቡራኬ መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል ተከፈተ፡፡
የጸሎት መርሐ ግብሩ እንደተጠናቀቀ ከቀደምት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከተመሠረቱት ማኅበራት መካከል የማኅበረ ሰላም የመዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡
በሰዋሰው ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የቅኔ መምህር የነበሩና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ሓላፊነቶች በመመደብ እያገለገሉ የሚገኙ በመንፈሳዊ ትምህርት የበለጸጉና በዘመናችን ከሚገኙ ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆኑት ንቡረ ዕድ ከፍለ ዮሐንስ በተጋባዥ እንግድነት የተገኙ ሲሆን “መንግስተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች” /ማቴ.13፡31/ በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ የወንጌል ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
“የእግዚአብሔር መንግሥት የተባለች ቃለ ወንጌል ምሥጢረ ሥጋዌን ሲያመለክት ነው፡፡ሰናፍጭ በመዘራቷ ነው የበቀለችው ትለመልማለችም፤ ብዙም ፍሬ ታፈራለች፡፡ ለእናትነት ከዚህ ዓለም በመረጣት በድንግል ማርያም ትመሰላች፡፡ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በየጥቂት አድጎና ምስጢረ ጥምቀትን ፈጽሞ እኛን የጠበቀን ያሳደገን መድኀኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስን አስገኝታለችና፡፡ የተበተነውን ሕይወታችንን ሊሰበሰበው ስለፈቀደ ነው፤ ወደ እኛ የቀረበው፡፡ ይህንን ማኅበር የመሠረቱት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በሰናፍጭ ቅንጣቱ እንደ ተማርነው በማኅበሩ ጥላ ሥር ብዙዎች በእግዚአብሔር መግቦት ተሰባስበዋል፡፡ እግዚአብሔር እያሠራው ነው፡፡ ይህ ማኅበር ቤተ ክስቲያናችንን፣ አባቶቻችንን እንዲሁም ምእመናንን እንዲያገለግል የእግዚአብሔር ፈቃድ እያሰራው ነው፡፡ ምእመናንም መጠቀም የኛ ፋንታ ነው፡፡ ማኅበሩን ብንጠቀምበት፣ ብንተባበረው መልካም ነው፡፡ ከልጆቻችን ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ ራስን ዝቅ ማድረግን፣ በጥሻው ውስጥ የወደቁት አባቶችን መጠየቅ ፤ ማጽናናትን እንማራለን፡፡ በጥምቀት ያገኘነውን ልጅነት አክብረን መኖር አለብን፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሁል ጊዜ ሥራችንን ሊሆን ይገባል፡፡ በጾም፣ በጸሎት የአጋንንት ክንድ መቁረጥ አለብን ቅዱስ ጳውሎስ ሰይፍን እንድናነሳ የሚነገረን ወንጌልን እንድንጫማ፣ ሥነ ምግባርን ታጥቀን መኖር እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፡፡ ዛሬ አስለቃሾች ብንሆን ነገ አልቃሾች እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገናል፡፡ ወዮባዮች እንዳንሆን በክርስቲየናዊ ሥነ ምግባር ሌሎችን መርዳት ይገባናል፡፡ መዳን ዝም ብሎ ፈረስ ጭኖ፣ መኪና ነድቶ የሚመጣ አይደለም በጎ ሥራ በመሥራት ግን ይገኛል፡፡ ያሰባሰበን እምነታችን ነው፡፡ ለነገ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግም፡፡ ለመዳን የሚፈልግ ሁሉ ይድናል፡፡ እኛም ድነናል፡፡ ልትድን ትወዳለህን የሚለውን አምላካዊ ቃል ሁል ጊዜ የምንጠየቀው ጥያቄ ነው፡፡ አዎ መዳን እንፈልጋለን ብለን የመጣን ነን፤ መዳን ስለምትፈልጉ ትጾማላችሁ፣ ንስሐ ትገባላችሁ፤ ሥጋወ ደሙ ወደሚሰጥበት ቤተክርስቲያን ትገሰግሳላችሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው መዳን ስለምትፈልጉ ነው፡፡” በማለት ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም በዲ/ን ዘማሪ ቴዎድሮስ ዮሴፍ ዝማሬ የቀረበ ሲሆን በመልአከ ገነት አባ ወ/ጊዮርጊስ አበጀ የደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የደብሩን ታሪክ በአጭሩ አቅርበዋል፡፡
በሆለታ ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የተደረገው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር እስከ ምሳ ሰዓት የተካሔደውን ከላይ ያስቃኘናችሁ ሲመስል በመርሐ ግብሩ ላይ በአጠቃላይ 5700 ምዕመናን የአጥቢያው ምእመናንን ሳይጨምር መሳተፋቸውን ከአስተባባሪ ኮሚቴው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ የምሳ መርሐ ግብሩም
በተሳካ ሁኔታ ተካሒዷል፡፡
ከሰዓት በኋላ
ከሰዓት በኋላ በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ የተጀመረ ሲሆን ከጠዋት ጀምሮ በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ምእመናንን በመባረክ የቆዩት ብፁዕ አባታችን አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከስዓት በኋላ ለሌላ አገልግሎት ወደ አዲስ አበባ ስለሚመለሱ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡
ብፅዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ልጆች የእግዚአብሔር ሥራ ይሠራሉ፡፡ መመሰባሰባችን ከሁሉም በላይ ፈቃዱ የእግዚአብሔር ነው፡፡ የክርስትና ጉዞ ተምሮ መቅረት ተገንብቶ መፍረስ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ልጆች የምንሆነው የክርስቶስን ሥራ ስንሠራ ነው፡፡ መሠረቱ ደግሞ ፍቅር ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት እውነት እንጂ ሐቁን አለባብሶ አቆንጅቶ ማስቀመጥ አይደለም፡፡ የክርስቶስ ሥራዎች በእኛ ሕይወት ውስጥ ሊታይ ይገባል፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፡፡ እግዚአብሔር ባይመራው በፀሐይ እየተመቱ አፈር ላይ ተቀምጦ መማር አይቻልም” ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸውም ቡራኬ ሰጥተው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱ ሲሆን ጉባኤው ግን ቀጥሏል፡፡
ከስዓት በኋላ ከተያዙት መርሐ ግብራት መካከል ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ “በኢየሩሳሌም የሚኖሩ” መ.ኢያሱ.15፥63 በሚል ርዕስ የዕለቱን የወንጌል ትምህርት ሰፋ አድርገው ሰጥተዋል፡፡
ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ በሰጡት የወንጌል ትምህርት “የከነዓንን ምድር የወረሱት የኤፍሬም ልጆች ናቸው፡፡ በጌዝርም የተቀመጡትን ከነዓናዊያንንም አላሳደዷቸውም እሰከ ዛሬም ድረስ ከነዓናዊያን በኤፍሬም ልጆች መካከል ተቀምጠዋል፡፡ ከነዓን ርጉም ፍሬ ቢስ ማለት ነው የተቀደሰውን የሚረግጥ፣ በጎውን እያየ የማይጠቀም፤ እንቁውን የሚረግጥ…. ኤፍሬም ማለት ደግሞ ፍሬያማ ማለት ነው፡፡ ኢያቡሳውያንም ከአፍሬማውያን ጋር አብረው ኖረዋል፡፡ ዛሬም ኢያቡሳውያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች አብረውን ይኖራሉ፤ ማጥፋት ባንችልም በግብራቸው ግን ልንተባበር አይገባም፡፡ ኑፋቄውን ማሳደድ መናፍቁን ማዳን፤ የዝሙትን መንፈስ መገሰጽ ዘማዊውን ማንጻት፤ የንፍገት መንፈስን ማሳደድ ንፉጉን ቸር፤ ለጋስ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ ነው መልካም ጦርነት የምንለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ስንመለከት፤ አንዳንድ መናፍቃንን ስንመለከት፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ በምግባር እጅግ የራቁና ባልተገባ ሕይወት ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን ለማሽከርከር የሚጥሩ ሰዎችን ስናይ እግዚአብሔር ለምን ዝም ይላል እንላለን፡፡
“በየቤቱ እንደ ጸሎት መጽሐፍ የራሱን ኑፋቄ ይዞ የሚዞር አለ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ መጥፎ ሥራ የሚሰራውን ተመልክቶ ቤተ ክርስቲያን ትክክል አደለችም ማለት፣ በጎውን ደግሞ አይቶ ቤተ ክርስቲያን መጥፎ የለባትም ማለት አይቻልም፡፡ በኢየሩሳሌም ሁለቱም አይነት ሰዎች አሉና፡፡ ዛሬ በገዳማት ውስጥ ሆነው የሚያጭበረብሩ ሰውን እንዲህ ታገኛላህ እያሉ የሚያታልሉእንዳሉ ሁሉ ሲያዩአቸው ምናምንቴ መስለው ስለ ሕዝብና ስለ ሀገር የሚጸልዩም አሉ” ብለዋል፡፡
ከዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የወንጌል ትምህርት በኋላ ዘማሪ ዲ/ን ዳዊት ፋንታዬ ያሬዳዊ ዝማሬ በመቅረብ የእለቱ መርሐ ግብር ቀጥሏል፡፡
ምእናን እንዲመለሱላቸው የሚፈልጓቸውን ጥያቄዎች በስልክ፤ በኢሜይል፤ እንዲሁም በአካል በመገኘት ለሐዊረ ሕይወት አስተባባሪ ኮሚቴው ያደረሱትን ምላሽ እንዲሰጥባቸው ማድረግ የመርሐ ግብሩ አንዱ አካል ስለነበር ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ በእያንዳንዱ ጥያቄ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ በማቅረብ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አርአያ የማደርገው ሰው አጣሁ፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ላይ ነኝ፡፡ ምን ትመክሩኛላችሁ?” ለሚለው ዲያቆን ያረጋል ሲመልሱም “ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን ግንኙነት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር በተለያየ ምክንያቶች ልንገናኝ እንችላለን፡፡ ከእግዚአብሔር ፍቅር ተነሳ ነው ሰውን የምንወደው እንጂ ስለ ሰዎች ፍቅር ብለን አይደለም እግዚአብሔርን የምንወደው፡፡ መነሻው እግዚአብሔር ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ፤ ክርስትናን ስናውቅ መጀመሪያ ሰዎችን አይደለም ማወቅ ያለብን፡፡ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ሊመሩን ይችላሉ፡፡ እነዚህ መንገዶች ናቸው፡፡ መድረሻው ግን አሁንም እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ መተዋወቅ ያለብን ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡ እኛ ግን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንመጣና ከእግዚአብሔር ጋር ሳይሆን ከሰዎች ጋር እንተዋወቃለን፡፡ እግዚአብሔርን ትተን ከሰዎች ጋር እንጣበቃለን፡፡ እነዚያ ሰዎች ሲጠፉ እኛም አብረን እንጠፋለን፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በአንዳንድ ወዲህ ወዲያ በሚሉ ሰዎች መለካት የለብንም፡፡ ማሰብ ያለብን የጸኑትን ነው፡፡ ስለዚህ አርአያ የምናደርጋቸው ሰዎች ከእግዚአብሔር እንደማይበልጡ መረዳት አለብን፡፡ ከሰዎች ይልቅ እግዚአብሔርን ማየት ስንጀምር ተስፋ መቁረጥ ከኛ ይርቃል፡፡ አርአያ የምናደርጋቸው ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ቢወጡ እንኳን እኛ ተስፋ ያደረግነው እግዚአብሔር እንዳለን ስለምንረዳ እንጸናለን፡፡” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ነብዩ ኤልያስ ከብሔረ ሕያዋን ወደ ምድር ወርዷል፡፡ እኛንም ልኮናል የሚሉ ወገኖች ተነሥተዋልና አስተምህሯቸው ምንድነው? ብታብራሩልን በማለት ለተጠየቀው ጥያቄም ዲያቆን ያረጋል በሰጡት ምላሽ “ሰንበት ቀዳሚት ናት፤ እሁድን ማክበር ስህተት ነው፡፡ ኤልያስ ሰንበትን ወደ ቅዳሜ ይመልሳል፤ እስካሁን እውነተኛው የመልከ ጼዲቅ መሥዋእት ስላልተሰዋ አሁን ኤልያስ እውነተኛውን የመልከ ጼዲቅ መስዋእት ይዞ መጥቷል፤ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ታህሣሥ 29 ሳይሆን መስከረም 1 ቀን ነው መከበር ያለበት፤ የዳዊት ኮከብ ተብሎ የሚጠራው ባለ ስድስት ጫፉ ኮከብን ይዛችሁ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቅርቡ በባሕር ዳር ውስጥ ሰውር ጉባኤ ተካሒዷል፡፡ ከኒቂያ፤ ከኤፌሶንና ከቁስትንትኒያ ጉባኤያት በላይ ተካሒዷል፡፡ በዚህ ጉባኤም ከገነትና ከብሔረ ሕያዋን ቅዱሳን መጥተው ተገኝተዋል፤ ካህናትን የገሰጸችና ከነመጻሕፍቶቻቸው ቤተ መቅደሳቸውን ያጠፋች ዮዲት ቅድስት ናት ይላሉ” በማለት ስለ ኤልያስ ወረዷል እያሉ በማስተማር ላይ ስለሚገኙት ሰዎች አስተምህሯቸውን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የማኅበረ ቅዱሳን አመሠራረት፤ እያከናወናቸው ስለሚገኙ የአገልግሎት ዘርፎች በአጭሩ በመዳሰስ ለምእመናን ግንዛቤ ያስጨበጡ ሲሆን መርሐ ግብሩንም በማጠናቀቅ በጸሎት ተዘግቶ ምእመናን ወደ መኪናዎቻቸው አምርተው በሰላም ጉዞው እንደተጀመረ በሰላም ተጠናቋል፡፡