ልደተ አቡነ ተክለ ሃይማኖት
ታኅሣሥ ፳፫፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
እንኳን ከጻድቁ አባታችን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልደት በዓል በሰላም አደረሰን!
የልደቱም ነገር እንዲህ ነው!
ጸጋ ዘአብ የተባለ ካህን ደጋግ ከሆኑ ሰዎች ወገን ሣራ የምትባል ሴት አግብቶ ይኖር ነበር። እግዚአብሔርን በማገልገል እጅግ ደግ ሆኑ። ጾም በመጾም ጸሎት በመጸለይ ትዕግሥትንም ገንዘብ በማድረግ ከቀን ቀን እያሉ በጐ ሥራን እያበዙ ሄዱ። ሁለቱም እጅግ ይዋደዱ ነበር፤ እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ እንደ ኤልሳቤጥና እንደ ዘካርያስ ነገር ግን ሣራ እጅግ መልከ መልካም ነበረች። ነገሯን የሰማ መልኳን ያየ ሁሉ እጅግ ያደንቃት ነበረ። ከአማቷ ቤትም ሳለች በሕግ ጸንታ ሥራዋን ሁሉ ገለጸች። ለአንደበቷ መወሰን ክንዷን ለመፍተል አጸናች፤ አማቷ የሥራዋን ሁሉ ደግነት ባየ ጊዜ። ስሟን ለውጦ እግዚእ ሐረያ አላት ከዚያች ቀን ጀምሮ በዚህ ስም ስትጠራ ኖረች። ከዚህ በኋላ ሕይወት ብነ በጽዮን ሞተ።
ሚስቱና ጸጋ ዘአብ በገንዘብ እጅግ የከበሩ ሆኑ፤ ነገር ግን እግዚእ ሐረያ መካን ሆነች፤ ልጅም አልነበራት፤ ስለዚህም ነገር በወር በወር በዐሥራ ሁለት ቀን የሚካኤልን በዓል ማዘከር ጀመሩ። የተራበ ማብላት የተጸማ በማጠጣት (ማቴ.፳፭፥ ፴፭) የታረዘ በማልበስ፣ ነዳያንን በማክበር የተቸገሩትን በመርዳት ቀን ያዋረዳቸውን ወራት የባሳቸውን በመደገፍ፣ እንግዳ መቀበል ግን የዘወትር ልማዳቸው ነበር፤ እነርሱን ያየ ልጅ እንደ ሌላቸውም የሰማ ሁሉ ያዝን ነበር። ያገራቸው ሰዎች ሁሉ እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ እግዚእ ሐረያና የጸጋ ዘአብ አነዋወር ምን ያምር ምንኛ ይወደድ፡፡”
እግዚእ ሐረያም መካን ስለ ሆነች በልቡናዋ ታዝን ትቆረቆር ነበር፤ ነገር ግን ልጅ ይሰጣት ዘንድ ልቡናዋን አጽንታ ወደ እግዚአብሔር ለመነች። የባሏ የጸጋ ዘአብ ግን ሥራው ጧት ማታም በመዓልትም በሌሊትም ወደ ቤተ ክርስቲያን መገስገስ ነበር። ዕጣን ለማጠን ለሚሄድበትም ጊዜ አለ፤ መሥዋዕት ለመሥራት የሚሄድበት ጊዜ አለ፤ ዳዊት ለመድገምም የሚሄድበት ጊዜ አለ፤ መጻሕፍት ለማንበብ (ለመመልከት) የሚሄድበትም ጊዜ አለ። ወንጌልን ለማስተማር የሚሄድበት ጊዜ አለ፤ ለትሩፋት ሥራ ለመሥራትና ጸሎት ለማድረግ የሚሄድበት ጊዜ አለ። እየተፋጠነ ከሚሠራው ሥራ ሁሉ ጋራ ወደቤተ እግዚአብሔር ባዶ እጁን አይሄድም፤ ለቤተ ክርስቲያን የሚሆን እጅ መንሻ ይዞ ይመጣ። ሥራውንም ከጨረሰ በኋላ ወደቤቱ ይመለሳል እንዲህ እያደረጉ ብዙ ዘመን ተቀመጡ።
ከዕለታት በአንድ ቀን እግዚእ ሐረያ ጸጋ ዘአብን በጎ ነገር ስለ መከረችው ገንዘቡን ሁሉ ለነዳያን መጸወተ፤ ቸር የሆነች ሚስቱ እንደነገረችው እኩሌታውን ገንዘብ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጠ፤ ዳግመና ወንዶችንም ሴቶችንም ባሮቹን ጠርቶ እንደዚህ አላቸው፤ “ወደ ወደ ዳችሁበት ሂዱ፤ ስለእግዚአብሔር ከመገዛት የነጻችሁ ሁኑ፤ (ነጻ አውጥታችኋለሁ)” እርሱም እኔንም ሚስቴንም ከዲያቢሎስ መገዛት ነጻ ያደርግን ዘንድ ወንዶች ሴቶችም ባሮቹ እንዲህ ባላቸው ጊዜ እጅግ አዘኑ፤ “ጌታችን ምን አደረግንህ? አባታችን ሆይ የሚያስቆጣህ የሚያሳዝንህ ሥራ ምን ሠራን? ብንበድልህም እነሆ አለንጋ ጅራፍ በፊትህ አለ፤ ግረፈን፤ እንገረፋለን፤ ጸጋ ዘአብም እንዲህ አላቸው፤ “ያሳዝናችሁኝም ነገር የለም፤ በእውነት ከፊቱ ቆመው የሚያገለግሉት በካህናት በአባቶቼ በረከት እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ ከኔም ቤት ልትኖሩ ብትወዱ እንደቤት ልጅ ሆናችሁ ኑሩ፤ ባሮች አይበሏችሁ፤ ወንዶችንም የጸጋ ዘአብ ወዳጆች ሴቶችንም የእግዚእ ሐረያ ባለሟሎች ይበሏችሁ፤” እንዲህ ባላቸው ጊዜ ሴቶቹም ወንዶቹም ደስ ብሏቸው እጁን እግሩን ሳሙት፤ ወንዶቹም ሴቶቹም እንደ ባለቤት ነጻ ሆነው ከርሱ ጋር ብዙ ዘመን ተቀመጡ።
እንደዚህም ሲኖሩ ሞቶሎሚ የሚባል አንድ ከሃዲ ተነሣ፤ እናቱም እስላደኒ ትባላለች፤ በሸዋ አውራጃና በዳሞት አውራጃ በኃይሉ ነገሠ፤ ያመረ ወሰን እስከምትሆን እስከ ዝማ ደረሰ፤ ቤተ ክርስቲያኑን አቃጥሎ ለጣዖት ሰገደ፡፡ “የፈጠራችሁኝ እናንተ ናችሁ” ብሎ በሰልፍ ጊዜም ድል እንዳደርግ የምታደርጉኝ ብሎ የእግዚአብሔርን ሕግ ሁሉ አጠፋ፤ “የሸዋን መኳንንት ሁሉ ሴቶቻችሁን አምጡልኝ አገባቸው ዘንድ” ይላቸው ነበር፤ እነርሱም እንዳይገድላቸው ፈርተው በፈረቃ ይልኩለት ነበር፤ እንደቅስንጥቂስ ሰዎች ሰልፍ የተማረ ነበርና፡፡
ስለዚህ ነገር በጦር (በኃይል) ነገሠባቸው፤ በዘመኑ ደናግልም አልቀሩት፤ በድንግና የተገኘችውን እየወሰዱ በመስጠት ከክብር ያሳንሳት ነበርና፤ ከምርኮም ውስጥ ደናግል የተገኘች እንደሆነ ይዘው እየሰጡ ከክብር ያሳንሳት ነበር፤ በሥራው ሁሉ የሚያጸይፍ ነው፤ በሥራው ሁሉ የተጠላ ነው፤ በዚያም ወራት ጽላልሽ አውራጃ ደረሰ፤ ዞረሬን ከቧት ሠፈረ፤ ጸጋ ዘአብ ሀገሩን ሲከቧት አይቶ ይህ ከሃዲ ሊገለው እንደመጣ ዐወቀ፤ በሌላ ጎዳና ፈጥኖ ሸሸ፤ ከሞተለሚ ጭፍራ አንዱ ፋጥኖ ተከተለው ጸጋ ዘአብን ሊገለው በፈረስ ተከተለው፤ ጦሩን ወረወረበት አላገኘውም፤ ሁለተኛም ጦሩን ለወረወረበት ወዶ ሳለ ጦሩ ከእጁ ጋር ተጣብቃ ቀረች፤ ለመወርወርም አልተቻለውም፡፡
ጸጋ ዘአብም ወታደሩ ሲከታተለው ከጥልቅ ባሕር ደርሶ እንደ ድንጋይ ተወርውሮ ጠለቀ፤ ወታደሩም ይህን አይቶ ከወንዱ ዳር ጥቂት ቆሞ ጠበቀው፡፡ ከውኃው ውስጥ ዋኝቶ (ምንአልባት) የወጣ መስሎት እንዳልወጣ ባየ ጊዜ ወደ መንደር ተመለሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከአደጋ አዳነው፡፡ ወደ ወደቡም አደረሰው፡፡
በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል ጸጋ ዘአብን ከሞት እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል፤ በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል:: አቡነ ተክለ ሃይማኖት የጸነሱት መጋቢት ፳፬, በ፲፪፻፮ (፲፩፻፺፮) ሲሆን የተወለዱት ታኅሣሥ ፳፬፣ በ፲፪፻፮ (፲፩፻፺፯) ዓ.ም ነው፤ በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል፤ ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::
የጻድቁ አባት የመጀመሪያ ስማቸው ፍሥሃ ጽዮን ይባላል፤ ይህንን ስም ይዘው አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል፤ በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያትና ሐዲሳትን) ተምረዋል፤ በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል፤ ዲቁና ከወቅቱ ዻዻስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::
ጻድቁ አባት ድቁናና ቅስና ተሾመው ካገለገሉ በኋላ ከሐይቅ እስጢፋኖስ ለዐሥር ዓመታት በምንኩስና ኖረዋል፡፡ ቀጥሎም ደ ደብረ ዳሞ በመሄድ በገድል ኖሩ፡፡ ኢየሩሳሌምም ተጉዘው ከጎበኙ በኋላ በትምህርተ ወንጌልን በማስተማር በኢትዮጵያ በተለይም በደቡቡ አካባቢ ለዐሥር ዓመታት ኖረዋል፡፡ በመቀጠለም ያገለገሉት በደብረ ሊባኖስ ነው፡፡ በዚህም ወቅት አምላካቸውን በጸሎት ሲጋደሉ እግራቸው ተቆርጧል፡፡ በዚህም ጊዜ ስድስት ክንፍ ተሰጣቸው፡፡ ተጋድሎአቸውን ፈጽመው ያረፉት በነሐሴ ፳፬ ነው፡፡
የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አማላጅነት፣ ረድኤትና ጸሎት አይለየን፤ አሜን!!!
ምንጭ፡- ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት