ሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ ዐረፉ
ነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ስንክሳርንና ግብረ ሕማማትን እንዲሁም ሌሎችን መጻሕፍት ከግእዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ታላቁ የመጻሕፍት ሊቅ ሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ በተወለዱ በ90 ዓመታቸው ነሐሴ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በሞተ ስጋ ከዚህ ዓለም ተለዩ፡፡
ሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ በአርሲ ክፍለ ሀገር በጢዮ ወረዳ ልዩ ስሙ ጨቢ አቦ በተባለ አካባቢ ከአባታቸው መምህር ወልደ ኢየሱስ ዘነበ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተ ሩፋኤል ብስራት ነሐሴ 16 ቀን 1915 ዓ. ም. ተወለዱ፡፡
ከአባታቸው ከመምህር ወልደ ኢየሱስ ዘነበ ንባብ፤ ውዳሴ ማርያም ንባብና ዜማ ፤መዝሙረ ዳዊትና ግብረ ዲቁና በመማር ለስልጣነ ክህነት ከበቁ በኋላ በአካባቢያቸው በሚገኘው ዱግዳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በዲቁና ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ገና በለጋ እድሜያቸው ትምህርትን ፍለጋ ወደ ወሎ ክፍለ ሀገር ላስታ ገረገራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመሔድ ከመምህር ሰይፉ የመጻሕፍተ ሐዲሳትን ትርጓሜ ፤ ከሌሎችም ታዋቂ መምህራን ድጓንና ጾመ ድጓን ተምረዋል፡፡ ወደ ጎንደር በማቅናት ዙር አምባ ገዳም ከታላቁ መምህር ቀለመወርቅ ዝማሬ መዋሥዕት በመማር አጠናቀዋል፡፡ ወደ ደብረ ታቦር በመሔድም የተክሌ አቋቋም ሊቅ ከሆኑት መምህር ቀለመወርቅ ዘንድ ገብተው አስመስክረዋል፡፡ ጎንደር አደባባይ ኢየሱስ ከታዋቂው የቅኔ መምህር በቅጽል ስማቸው የቅኔው ማዕበል መምህር ፈንቴ ቅኔ አስመስክረዋል፡፡ በዋሸራ ከሚገኙት የቅዳሴ መምህር አባ አላምረው ዘንድ የደብረ ዓባይ የመዝገብ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡ ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ደግሞ ከመልአከ ገነት ጥሩነህ ለተማሪዎቻቸው ዝማሬ መዋሥዕትን እያስቀጸሉ ከእሳቸው የአቋቋም ስልቶችን በሚገባ አጣርተው ለማስመስከር በቅተዋል፡፡
ወደ መምህርነት ከገቡ በኋላ ብዛት ያላቸው ደቀመዛሙርትን ያፈሩ ሲሆን የተክሌ የአቋቋም በቀላሉ ለመማር የሚያስችል ምልክት ፈጥረው ለደቀ መዛሙርቶቻቸው አስተምረዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በታእካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፤ በደብረ ኀይል ቅዱስ ራጉኤል ፤ በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያናት እየተዘዋወሩ በርካታ ደቀመዛሙርትን አፍርተዋል፡፡
ወደ ትውልድ ሀገራቸው አሰላ በመመለስም በአሰላ መንበረ ጵጵስና ደ/ም/ቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመሪ ጌትነት ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፤ ከ1971 ዓ.ም. እስከ 1998 ዓ.ም. በአሰላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡
በጎንደርና ጎጃም የትምህርትና የመምህርነት ዘመናቸው ላበረከቱት አገልግሎት ከደብረ ወርቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በቅሎ ከነኮርቻው ተሸልመዋል፡፡
ባበረከቱት ፍጹም ቅንነት የተሞላበት አገልግሎታቸው የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከቀድሞው ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቀሚስና ጥንግ ድርብ ከነካባው አልብሰዋቸው፤ የእጅ የወርቅ መስቀል በመሸለም ሊቀ መዘምራን የሚል የክብር ስምም ሰጥተዋቸዋል፡፡
መጻሕፍትን በማንበብና በመተርጎም ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ውለታ የዋሉ አባት ሲሆኑ የዓመቱን መጽሐፈ ስንክሳር ከግእዝ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ሰባት ዓመታትን ፈጅቶባቸው አስመራ ለሕትመት በተላከበት ወቅት ጠፍቷል፡፡ ተስፋ ሳይቆርጡ በድጋሚ በሁለት ዓመታት ውስጥ በድጋሚ ተርጉመው ለሕትመት አብቅተዋል፡፡ እንዲሁም ግብረ ሕማማትንና ገድለ ዜና ማርቆስን ከግእዝ ወደ አማርኛ በመተርጎም ለሕትመት አብቅተው ቤተ ክርስቲያን እየተጠቀመችባቸው ትገኛለች፡፡ በተጨማሪም ገድለ ሓዋርያት፤ ተአምረ ኢየሱስ፤ ገድለ ቂርቆስ ፤ ገድለ ነአኩቶ ለአብ ፤ ገድለ ሊባኖስ፤ ገድለ ማርያም መግደላዊት፤ ድርሳነ ሐና ፤ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅና ሌሎችም በርካታ መጻሕፍት ከግእዝ ወደ አማርኛ በመተርጎም ለቤተ ክርስቲያን አበርክተዋል፡፡
ሊቀ መዘምራን ላዕከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ በአንድ ወቅት መጻሕፍትን ለመተርጎም የተነሳሱበትን ምክንያት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “በመኪና አደጋ እግሬ ተሰብሮ በነበረበት ወቅት ቁጭ ከምል ለምን መጻሕፍትን አልተረጉምም በሚል እግዚአብሔር አሳስቦኝ ተነሳሳሁ፡፡ ስንክሳርንና ሌሎችን አሥራ ሦስት መጻሕፍትን የተረጎምኩት ያኔ ነው፡፡ እግዚአብሔር ታላቅ ችሮታ ነው ያደረገልኝ፡፡ እግሬ ባይሰበር ኖሮ እነዚህን መጻሕፍት መተርጎም አልችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር የጎዳ መስሎ ይጠቅማል፡፡ የእግሬ መሰበር ትልቅ ጥቅም ለኔም ለቤተ ክርስቲያንም አስገኝቶልኛል፡፡” ብለው ነበር፡፡
በቅርቡም በጠና ታመው ሕመማቸው ፋታ በሰጣቸው ስዓት ለደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ይተረጉሙት የነበረው ዜና ሥላሴ የተሰኘው መጽሐፍ አብዛኛውን ክፍል ተርጉመው ያገባደዱት ሲሆን ሳይፈጽሙት ሞት ቀድሟቸዋል፡፡
በእርግና ምክንያት ጡረታ ከወጡ በኋላ ለቤተ ክርስቲያን ባበረከቱት ከፍተኛ ትጋትና አገልግሎት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ሙሉ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው አድርገዋል፡፡
ሊቀ መዘምራን ላእከ ማርያም ወልደ ኢየሱስ በ1946 ዓ.ም. ከወ/ሮ ምሕረት በትዕዛዙ ጋር በስርዓተ ተክሊል ጋብቻ የፈጸሙ ሲሆን ስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ልጆችን አፍርተው ሠላሳ አንድ የልጅ ልጆችን ለማየት በቅተዋል፡፡ ዝግጅት ክፍላችን ለቤተሰቦቻቸውና ለዘመድ ወዳጆቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡