ለገዳማት የመብዐና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ

በእንዳለ ደምስስ
ግንቦት 18/2004 ዓ.ም.

በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በየወሩ እየተዘጋጀ የሚቀርበው የዜና ገዳማት መርሐ ግብር ግንቦት 7 ቀንYemeba Serchet to Monks 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ በዋነኛነት ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ በቆየው የመብዐ ሳምንት በሚል በችግር ላይ ለሚገኙ 400 አድባራትና ገዳማትን ለመርዳት ከምእመናን የተሰበሰበን መብዐ እና አልባሳት /ልብሰ ተክህኖ/ ስርጭት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ 800 ሺህ ብር ለመሰብሰብ የተቻለ ሲሆን እስከ 750 ምእመናን ተሳትፎ አድርገዋል በማለት የገለጹት የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ናቸው፡፡ በተገኘው ገቢ መሠረት ስርጭቱን በ4 ዙር ለማከናወን የታቀደ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በትግራይ 7 ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለሚገኙ 50 አድባራትና ገዳማት እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናት ለአንድ ዓመት የሚሆን የመብዐ ስጦታ ተሰጥቷል፡፡

 

ስጦታው የተከፋፈለው ለአንድ ሳምንት የቆየ ጉዞ በማከናወን በየአድባራቱና ገዳማቱ በመገኘት ሲሆን ስርጭቱ ካካተታቸው ሀገረ ስብከቶች መካከል በደቡብ ትግራይ አርማጭሆ፤ እንደርታ፤ አዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬና ሁመራ ይገኙበታል፡፡ ከገዳማቱ መካከል ደብረ ሳሙኤል ዘሃሌ ሉያ፣ ደብረ በንኮል አቡነ መድኀኒነ እግዚእ፤ አባ ዮሃኒ ዘቆላ ተንቤን፣ አባ ቶማስ ዘደብረ ማርያም ዘሃይዳ፣ ፀአዳ አምባ አቡነ መርአዊ ክርስቶስ፣ እንደቆርቆር ቅድስት ማርያም ገዳማት ይገኙበታል፡፡

አድባራቱና ገዳማቱ ሰው የማይደርስባቸው ሊባሉ የሚችሉ በረሃማና ጠረፋማ አካባቢዎች ሲሆኑ እቅዱን ለማሳካት አስፋልቱንና ኮረኮንቹንYeMeba Serechet በመኪና፤ ተራራውንና ተዳፋቱን በግመል በመጫንና በማከፋፈል ምንም መቀደሻ እጣን፣ ጧፍ፣ ዘቢብ እንዲሁም ልብሰ ተክህኖ ለሌላቸው ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ስርጭቱን የተቀላጠፈ ለማድረግ በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የማኅበሩ ማእከላት አባላት ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡

 

በስጦታው ወቅት አባቶች ያሉባቸውን የመብዐ እጥረት ገልጸው “ዛሬ ዐይናችን እንደበራ እንቆጥረዋለን” በማለት የተደረገላቸውን ስጦታ ውዳሴ ማርያም እየደገሙና የኪዳን ጸሎት እያደረሱ መብዐውን ለሰጡ ምእመናንና ማኅበረ ቅዱሳን በጸሎት በማሰብ ተቀብለዋል፡፡

 

በተያያዘም በዋነኛነት ትኩረት ከተደረገባቸው ገዳማት ውስጥ ትግራይ ፀአዳ አምባ አቡነ መርአዊ ክርስቶስ ገዳም ይገኝበታል፡፡ ታላላቅ አባቶችን ያፈራ ገዳም እንደሆነና በረሃብና እርዛት፤ እንዲሁም ሆድ በሚነፋ በሽታ ምክንያት አባቶች በችግር ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን እውነታውን በፊልም በማስደገፍ ለምእመናን ቀርቧል፡፡ በሽታው በጥናት ሊደረስበት እንዳልተቻለ መነኮሳቱ የሚገልፁ ሲሆን የአካባቢው ምእመናን በበሽታው ምክንያት ወደ ሰፈራ በመሄዳቸው ገዳማውያኑ ብቻቸውን ቀርተዋል፡፡ ከገዳሙ የሁለት ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ የእርሻ ቦታ ያላቸው ቢሆንም የገዳሙ አባቶች በእርጅናና በጤና መታወክ ሳቢያ ማረስ አልቻሉም፡፡ ከዚህ ቀደም የአካባቢው ምእመናን ያርሱላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ “አበው ያቆዩልንን ቅርስና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ጥለን አንሄድም” በማለት ጸንተው ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 52 መነኮሳት ብቻ የሚገኙ ሲሆን በአልባሳትና በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ትኩረት አድርጎ ለእነዚህ አባቶች ምእመናን እንዲደርሱላቸው ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ እስከ ነሐሴ 2004 ዓ.ም. ድረስ ለአልባሳት 15.600 ብር እንዲሁም ለቀለብ 20.800 ብር እንደሚያስፈልግ በመርሐ ግብሩ ወቅት በመገለጹ በእለቱ ከተገኙ 2 በጎ አድራጊ ምእመናን ከላይ የተጠቀሱትን ወጪዎች እንደሚሸፍኑ ቃል ገብተዋል፡፡ ዋና ክፍሉም ምስጋናውን በማቅረብ ምእመናን ድጋፋቸውን እንዳይለይ አጽንኦት በመስጠት “እናንተ ሁል ጊዜ ስጡ፣ ከቅዱሳን በረከትን ታገኛላችሁ፣ እጃችሁ ከምጽዋት አይጠር፣ እኛም አደራችሁን ተቀብለን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ነን” በማለት የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ገልጸዋል፡፡

 

በዜና ገዳማት ወርሐዊ መርሐ ግብር ከተዳሰሱት መካከል ለዝቋላ ገዳም በቃጠሎው ምክንያት ጊዜያዊ ድጋፍና የፕሮጀክት ጥናት መደረጉ ተገልጿል፡፡ በቃጠሎው ወቅት የቀለብ እጥረት በመከሰቱ ማኅበረ ቅዱሳን ምእመናንን በማስተባበር 50 ኩንታል ስንዴ፣ 20 ኩንታል ጤፍ፣ 40 ሺህ ብር የሚገመት ውኃ፣ በሶ፣ ስኳርና ዳቦ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ከማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ከበጎ አድራጊ ምእመናን የተሰበሰበ ለድጋፍ የሚሆን 125 ሺህ ብር ተሰብስቧል፡፡ ወደ ዝቋላ ገዳም ባለሙያዎችን በመላክ ለገዳሙ የሚሆን የእርሻ ቦታ፣ የመጠጥ ውኃና የመንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ጥናት ተደርጓል፡፡ የደብረ ዘይት ማእከል አባላት የዝቋላን ገዳም አስቸጋሪ መንገድ ለመጠገንና ለማስተካከል ምእመናንን በማስተባበር ከፍተኛ ርብርብ ላይ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ የጎንደር ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም ገዳም የአብነት ተማሪዎች ማደሪያ ቤት ግንባታ መጀመሩም በሪፖርቱ ከተካተቱት አበይት ክንውኖች አንዱ ሆኗል፡፡

 

በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር በዲ/ን አእምሮ ይሄይስ በክፍሉ የተከናወኑ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ የ10 ዓመት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በሪፖታቸውም በእርሻ ፤ንብ ማነብ፤ግንባታ፤ የወተት ላምና ከብት ማድለብ እንዲሁም ሰው ኃይል ማፍራት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፡፡ ከፕሮጀክቶቹ መካከል በአብዛኛው የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ፣ የመምህራንና የተማሪዎች መኖሪያ፤ የጉባኤ ቤትና የካህናት ማሠልጠኛ፣ የካህናትና መነኮሳት መኖሪያ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዙ በስፋት አብራርተዋል፡፡ በጥናት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በሂደት ላይ ሲሆኑ ከእቅድ ውጪም እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡በተጨማሪም 145 የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ 136 መምህራን፤ 865 ተማሪዎች በየወሩ እየተደጎሙ እንደሚገኙ ዲ/ን አእምሮ ይሔይስ ገልጸዋል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን የ3 ወራት የሒሳብ ሪፓርት ቀርቧል፡፡ ከምእመናን በክፍሉ እንቅስቃሴና በገዳማት ዙሪያ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ከ800 በላይ ጥሪ የተደረገላቸው በመብዐ ሳምንት ድጋፍ ያደረጉ ምእመናንና በጎ አድራጊዎች በመርሐ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

 

ዜና ገዳማት በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በየወሩ እየተዘጋጀ የገዳማትንና አድባራትን ነባራዊ ሁኔታ፣ የክፍሉን እቅዶችና ተግባሮች እንዲሁም የተተገበሩና በዝግጅት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የሚተዋወቁበት መርሐ ግብር መሆኑ ይታወቃል፡፡