ለአብነት መምህራንንና ተማሪዎች የሕክምና አገልግሎት ተሰጠ
ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.
በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ
በማኅበረ ቅዱሳን የሙያ አገልግሎትና ዐቅም ማጎልበቻ ዋና ክፍል የጤና ንዑስ ክፍል አስተባባሪነት በደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ በምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳምና በፍቼ ደብረ ሲና ዐራተ ማርያም ደብር ለሚገኙ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ከሚያዝያ 25 እስከ 27 ቀን 2006 ዓ.ም የሕክምና አገልግሎት ተሰጠ፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የጤና ንዑስ ክፍሉ ሰብሳቢ ዶክተር ክብሮም ሙሉጌታ የሕክምና አገልግሎት አስመልክቶ እንደገለጹት በአብዛኛው የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ሲታመሙ ወደ ሕክምና ማእከል በመሔድ የመታከም ልምድ የላቸውም፡፡
በመሆኑም ማኅበሩ በሦስት የአብነት ትምህርት ቤቶች የጤና ባለሙያዎችን በመላክ የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል፣ ስለጤና አጠባበቅ ትምህርት አስተምሯል፣ በአብነት ትምህርት ቤቶቹ አቅራቢያ በሚገኝ ጤና ጣቢያ እንዲታከሙ የምክር አገልግሎት ሰጥቷል፣ ከበድ ያለ የጤና ችግር የገጠማቸውን ደግሞ ከማኅበሩ የገዳማት ክፍል ጋር በመነጋገር ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የሚታከሙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የሕክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት መምህራን እና ተማሪዎች ስለተደረገላቸው የሕክምና እገዛ መደሰታቸውን ተናግረው፤ ማኅበሩ ወደፊትም እንደዚህ ዓይነት አገልግሎቶችን በአብነት ትምህርት ቤቶች በመገኘት በስፋት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በሕክምና አገልግሎቱ ሰባት የሕክምና ባለሙያዎች፣ አንድ ፋርማሲስትና ሁለት ነርሶች የተሳተፉ ሲሆን ከሰባት መቶ በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች የነፃ ሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡