‹‹ለብ ያልህ አትሁን!››
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
ኅዳር ፳፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
የሁላችንም ሕይወት ትኩስ፣ ለብ ያለና በራድ ተብለው በሚገለጹ ሦስት ሁነቶች ውስጥ የሚገኝ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ እነዚህን ሦስቱን የገለጸው ‹‹በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ፣ መልካም ነበር፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ፥ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው›› በማለት ነበር፡፡ (ራእ.፫፥፲፭-፲፮)
ቅዱስ ዮሐንስ ትኩስ፣ በራድና ለብ ያለ የሚሉ ቃላት የምን መገለጫ እንደሆኑና ምን ዓይነት ትርጉም እንደሚሰጡ ለሚረዳው ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን አለቃ፣ በኋላም በዚህ ሕይወት ለምንመላለስ ክርስቲያኖች ምሳሌ አድርጎ ያቀረበው ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ ነው።
ትኩስ መሆን በእምነት መቃጠል ነው። ፊት ለፊት ተጋፍጠው እውነትን የመሰከሩ የእነ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅና የእነ ቅዱስ ኤልያስ ሕይወትን የሚያመለክት ነው። ትኩስ መሆን በኃጢአት የሚመጣውን ቅጣት መፍራት ሳይሆን እንደ ጻድቃን ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር ብሎ ኃጢአትን የመተው ሕይወት ነው።
በራድ መሆን ደግሞ እንደ ቀራጩ ማቴዎስና እንተ እፍረት ማርያም ምንም እንኳን በኃጢአት ቢኖሩ ስለ ኃጢአታቸው የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸው፣ ኃጢአታቸውን የሚያብሰለስሉ ክርስቲያኖች ሕይወት ምሳሌ ነው። (ሉቃ.፲፰፥፲፫፣፯፥፴፰)
በራዶች በኃጢአታቸው ቢቀጥሉ የሚመጣባቸውን ቅጣት እግዚአብሔርን ፈርተው ኃጢአትን የሚተው፣ እንደነ ቅዱስ ዮሐንስ ፊት ለፊት ተጋፍጠው ሳይሆን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሰዎችን በብልሃት አስተምረው የሚመልሱ ክርስቲያኖች ምሳሌ ነው።
ለብ ያለ መሆን ኃጢአትን ለመተው ፍቅረ እግዚአብሔርም፣ ፍርሃተ ቅጣትም የማይስተዋልባቸው የጽድቅ ሥራ ሳይኖራቸው ራሳቸውን እንደ ፈሪሳዊ ጸሎተኛና ራሳቸውን አጽድቀው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ምሳሌ ነው። ‹‹ራሳቸውን ለሚያመጻድቁና ባልንጀራቸውን ለሚንቁ እንዲህ ብሎ መሰለላቸው፤ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ፥ ሁለተኛውም ቀራጭ ነበር፡፡ ፈሪሳዊውም ቆመና እንዲህ ብሎ ጸለየ፡- “አቤቱ እንደ ሌሎች ሰዎች፥ እንደ ቀማኞችና እንደ ዐመፀኞች፥ እንደ አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ያላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማለሁ፤ ከማገኘውም ሁሉ ከዐሥ አንድ አሰጣለሁ” አለ። ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዐይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱንም እየመታ፡- “አቤቱ፥ እኔን ኀጢኣተኛውን ይቅር በለኝ” አለ፡፡ እላችኋላሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደረግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ይከብራልና፡፡›› (ሉቃ.፲፰፥፱-፲፬)
ለብ ያሉት ዋጋ ያለውን ሕይወት (ጽድቅን) የሚፈልጉ፣ ሆኖም ግን በዚህ ሕይወት ለመኖር ግን ተጋድሎም፣ ትጋትም የሌላቸው የስም ክርስቲያኖች ሕይወት ምሳሌ ነው። ለብ ያለ ለሰውነታችን አስፈላጊነት የሌለው፣ ለጤና የማይስማማ ቀዝቅዞ፣ የማያረካ፣ ሞቆ የማያነቃቃ፣ የማቅለሽለሽ ስሜትን የሚፈጥር ተደርጎ ይወሰዳል። ለብ ያለ የክርስቲያኖች ሕይወትም ለእግዚአብሔር እንዲሁ ነው። በቅዱስ ዮሐንስ ላይ አድሮ ‹‹በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፤ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ፣ መልካም ነበር፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ፥ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው›› ያለው ለዚህ ነው፡፡ (ራእ.፫፥፲፭-፲፮) በዚህ ሕይወት ለምንመላለስ ቃሉ እስከ መቼ በኃጢአት ውስጥ እያለህ የመጸጸት ስሜት አልተሰማህም? እስከ መቼ ምንም ፍሬ ሳታፈራ ምድርን ታጎሳቁላታለህ? እያለ ይገሥጸናል። በዚህ ለብታ ውስጥ ከቀጠለ ምሕረቱ እንደምትቀር በመጨረሻም በዛፍ የተመሰለ ሕይወታችን እንደምትቆረጥ ያስጠነቅቀናል፡፡
ለዚህም አንድ ምሳሌ እናንሣ፡- ‹‹አንድ ሰው በታወቀች በወይኑ ቦታ ውስጥ በለስ ነበረችው፤ ፍሬዋን ሊወስድ ወደ እርስዋ ሄዶ አላገኘም፡፡ የወይኑን ጠባቂም፡- “የዚህችን በለስ ፍሬ ልውሰድ ስመላለስ እነሆ፥ ሦስት ዓመት ነው፤ አላገኘሁም፤ እንግዲህስ ምድራችን እንዳታቦዝን ቊረጣት” አለው፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አለው፥ “አቤቱ አፈር ቈፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፥ ፍግም እስከ አፈስባት ድረስ እንኳን ተዋት፡፡ ምንአልባት ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፥ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን፡፡ (ሉቃ.፲፫፥፮-፱) ከዚህ ቅጣት ለማምለጥም “ለብ ያለህ አትሁን” እያለ ይመክረናል። ሁል ጊዜ ቃሉን በማሰላሰል፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በስግደትና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ በእምነት የምትቃጠል ትኩስ ሁን እንጂ ለብ ያልህ አትሁን።
ትኩስ መሆን አቅቶህ አንድ ጊዜ ወደ ዓለም፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ መንፈሳዊነት በማለት መርሕ አልባ ሕይወት ውስጥ ብትሆን እንኳን በንስሓ ለመመለስ የምትጸጸት በራድ ሁን እንጂ በኃጢአት ውስጥ እያለህ ራስህን በማጽደቅ የምትኖር ለብ ያልህ አትሁን።
የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች፥ የእኔስ ሕይወት ምድቡ ከየትኛው ይሆን ብለን ራሳችንን ጠይቀን ይሆን? ትኩስ፣ ለብ ያለ ወይስ በራድ? ያለ መርሕ ከትኩሱ ጋር ትኩስ መስሎ፣ ከበራዱ ጋር በራድ መስሎ በለብታ ሕይወት ውስጥ ካለን ከወደቅንበት በንስሓ እንድንመለስ ቃሉ ያስጠነቅቀናል።
በመጽሐፈ ሲራክ ላይ ‹‹ስለ ኃጢአትህ ንስሓ መግባትን አትፍራ፤ ‹የእግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ነው፤ ኀጢአቴንም ይቅር ይለኛል› እያልህ በኃጢአት ላይ ኃጢአትን አትጨምር፤ ምሕረትም መቅሠፍትም ከእርሱ ዘንድ ይመጣልና፤ መቅሠፍቱም በኃጢአተኛ ሰው ላይ ይወርዳል፤ ለእግዚአብሔር መገዛትን ቸል አትበል፤ ሞት ድንገት ትመጣለችና ከቀን ቀን አታሳልፍ›› (ሲራ.፭፥፭-፯) እንዳለን እኛም ሃይማኖት ጸንተን፣ ከወደቅንበት ኃጢአት በንስሓ ተነሥተን መንግሥቱን እንድንወርስ ዘወትር በጸሎት፣ በጾምና በበጎ ምግባራት ሁሉ ልንተጋ ይገባል፡፡
ለብ ካለ ሕይወት ወጥተን፣ በበጎ ምግባር አጊጠን፣ የስሙ ቀዳሾች፣ የክብሩ ወራሾች ያድርገን፤ አሜን!