“ሃይማኖትና ሀገር ወጣት ሲረከበው ነው ሀገርነቱም፣ እምነቱም ሊቀጥል የሚችለው”

የዛሬው የቤተ አብርሃም እንግዳችን መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ ይባላሉ፡፡ ከአባታቸው ከቄስ ፈንቴ ታረቀ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ጎንደር በቀለ በ፲፱፻፶፰ ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ ልዩ ስሙ ጉሌ ኪዳነ ምሕረት ተብሎ  በሚጠራ ቦታ ተወለዱ፡፡ በአብነት ትምህርቱ ቅኔን ጨምሮ ሌሎቹንም ትምህርቶች ተጨልፎ ከማያልቀው ከቤተ ክርስቲያን ማዕድ በአባቶች እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት ማሠልጠኛ ለአራት ዓመት የነገረ መለኮት ትምህርት ተምረዋል፡፡ በትውልድ አካባቢያቸው ለ፲፫ ዓመት የቅኔና የሐዲሳት መምህር ሆነው አገልግለዋል፣ ከዚያም ወደ ከተማ በመምጣት ከ፳፪ ዓመታት በላይ የቅኔ፣ የሐዲሳትና የብሉያት መምህር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በርካታ ተማሪዎችን አስተምረው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ በአጠቃላይ ባሳለፉት የአገልግሎት ዘመን የቅኔና የትርጓሜ መምህር ሆነው በማገልገል ከ፴፱ ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሃይማኖተ አበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከመጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንታ ጋር በሕይወት ተሞክሯቸው ዙሪያ ልምዳቸውን፣ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ያጋሩን ዘንድ የቤተ አብርሃም እንግዳችን አድርገናቸዋል፤ መልካም ንባብ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ስለ ልጅነት አስተዳደግዎ ቢያጫውቱን?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ፡-  ለወላጆቼ  ሦስተኛ ልጅ ነኝ፡፡  የልጅነት አስተዳደጌ እንደ ልጅ ተጫውቼ አድጌለሁ ማለት አልችልም፡፡ አባቴ  በጣም ቁጡ ናቸው፡፡ ከአካባቢው ልጆች ጋር ስሔድ ይባልጋል፣ እኛንም ሥራ ያስፈታናል የሚል አመለካከት ስለነበራቸው ከሠፈሬ ልጆች ጋር ተጫውቼ፣ አፈር ፈጭቼ ፣ ውኃ ተራጭቼ አላደግሁም፣ ብዙ አላውቀውም ማለት እችላለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የትምህርት አጀማመርዎ ሂደቱ እንዴት ነበር?

መጋቤ ምሥጢር ቀጸላ፡- አባቴ ዳዊት የሚደግሙ ናቸው:: በተለይ ደግሞ በእናቴ ወገን ከቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ የካህናት ቤተሰብ በመሆናቸው ሀገርና ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቅ ትውልድ ለማፍራት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ማስተማር ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑ ስለነበሩ  እኔን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንድማር መንገዱን ያመቻቹልኝ ወላጆቼ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡ በዚህም መሠረት የአብነት ትምህርቴን በተወለድኩባት መንደር መምህር ዓለሙ አናጋው ከሚባሉ አባት ዘንድ በመግባት ፊደል፣ ዳዊት ንባብ ለሦስት ዓመት ቀጸልኩ፡፡ ትምህርት ላይ የሚበልጠኝ አልነበረም፡፡ እንድ ጊዜ ከሰማሁ በአእምሮዬ እመዘግበዋለሁ፣ ፈጽሞ አልረሳም፡፡ ነገር ግን በአብነት ትምህርቱ ከሦስት ዓመት በላይ መቆየት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም አባቴ ቄስ ፈንቴ በወቅቱ ከቤተ መንግሥት ጋር የሚቀራረቡ፣ በዐደባባይ የሚውሉ፣ በሀገሬው ዘንድ አንቱታን የተቸሩ ትልቅ ሰው ስለነበሩ ወደ አዲስ አበባ አምጥተው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በማስገባት ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ ተማርኩ፡፡

ነገር ግን ጊዜው ፲፱፻፸ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ስለነበር ደርግ ወጣቱን ኢሕአፓ ናችሁ በማለት እያፈሰ ያንገላታ ስለነበር እኔም በሰዎች ጥቆማ ገና በታዳጊነት ዕድሜዬ ተይዤ ታሰርኩ፡፡ ክፉኛ ግርፋትና ድብደባም ተፈጽብኝ፡፡ እስር ቤት ውስጥ በደረሰብኝ ግርፋትም ከፍተኛ ሥቃይ አሳልፌአለሁ፡፡

ከእስር እንደተፈታሁ ወደተወለድኩበት ቀዬ ወደ ምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ በመመለስ የአስኳላውን ትምህርት አያሳየኝ በማለት በድጋሚ የአብነት ትምህርቱን ለመዝለቅ ወደ አብነት ትምህርት ቤት ሄድኩ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ከትምህርትዎ ጋር ተያይዞ የቤተሰብዎ አስተዋጽኦ ምን ነበር?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ፡- ወላጅ እናቴ የቤተ ክርስቲያን ሰው በመሆናቸው በተለየ መልኩ ነበር በመንፈሳዊ ትምህርት እንዳድግና ወደዚያ እንዳዘነብል ይገፋፉኝ የነበረው፡፡ እንዲያውም የዘመናዊውን ትምህርት በምማርበት ጊዜ “ከካህን ተወልደህ ይህንን የክህደት ትምህርት እንዴት ትማራለህ?” እያሉ ይወቅሱኝ ነበር፡፡ ደርግ አሰቃይቶኝ ወደ ሀገሬ ስመለስም ትልቁን የሥነ ልቡና ድጋፍ የሆኑኝን እናቴ ነበሩ፡፡ እናቴ የአብነት ትምህርት እንድማር የነበራት ጽኑ ፍላጎት ከፍተኛ እንደነበር ስለተረዳሁ ተመልሼ የአብነቱን ትምህርት ቀጠልኩ፡፡ እናቴን በጣም እወዳት ስለነበር ሐሳቧንና ምኞቷን ለመፈጸም ተግቼ እቀጽል ነበር፡፡

እናቴ ስለ እኔ አብዝታ ትጨነቅ ነበር፡፡ ወደ ዓለማዊው ትምህርት እንዳዘነብል ፈጽሞ ፍላጎት አልነበራትምና “ልጄ ይህንን ሥጋዊ ትምህርት አትጨርሰውም፣ ተችሎህም አታሳካውም ስለዚህ ብትማርም የምታሳካው የሀገርህን፣ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነው” ትለኝ ነበር፡፡ እኔም በእናቴ ምክር ተመርቼ ለዚህ ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ የቤተሰቦቼ በተለይም የእናቴ አስተዋጽኦ ትልቁን ሥፍራ ይይዛል፡፡

ወንድሞቼም ወደ አብነት ትምህርቱ አዘንብለው በቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ አንዱ የቅኔ መምህር ነው፣ ከዚያ በታች ያለውም ቄስ ነው፡፡ ወንድሞቼ ሁሉም ካህናት በመሆናቸው ድጋፋቸው አልተለየኝም ነበር፡፡

ወላጆች፣ ቤተሰብ፣ ዘመድ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ስትማር ብዙ ክብር ይሰጡሃል፡፡ እናታችን ልጆቿን በጸሎት፣ በሐሳብ፣ ስንቅ በመቋጠር፣ ዕውቀት አግኝተን እንድንመለስ ከፍተኛ ፍቅርና እገዛ በማድረግ ትደግፈን ነበር፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ከረጅም ጊዜ በኋላ የአብነት ትምህርቱን ለሁለተኛ ጊዜ ሲቀጥሉ አልተቸገሩም?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ፡- በፍጹም አልተቸገርኩም፡፡ እግዚአብሔር በቤቱ እንድኖር ፈልጎ ነው መሰለኝ ከተመለስኩ በኋላ መጀመሪያ የሄድኩት በሀገራችን ታዋቂ  የቅኔ መምህር ከነበሩት ሊቀ አእላፍ ገዳሙ አያሌው ዘንድ ነው፡፡ እርሳቸው ጎጃም ውስጥ የታወቁ የቅኔ መምህር ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው እስከ ዘይዕዜ ደረስኩ፡፡ (ዘይዜ ማለት ከቅኔዎች አንዱ መወድስ ሲቀር የቀሩትን ማለት ነው)፡፡ በደንብ ተግቼ ነው የተማርኩት፣ መምህሬም ጉብዝናዬን ተረድተው በጣም ያቀርቡኝና ይደግፉኝ ነበር፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ለመማር ያደረጉት ጥረትና ውጣ ውረዱን ቢያብራሩልን?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ፡-የተማሪ ነገር ከአንዱ ወደ አንዱ እየተዘዋወሩ ዕውቀትን መያዝ ነውና ደግሞ የኔታ ኃይሌ ከሚባሉ መምህር ዘንድ ወይቤ ልደታ የምትባል ሀገር በመሄድ የቀረኝን ቤት ሞላሁ፡፡

በመቀጠል በቋሪት ወረዳ ልዩ ስሙ ደብረ መድኃኒት ጨጎዴ ሐና ወደ ሚባል አካባቢ በማምራት አሁንም በማስተማር ላይ ከሚገኙት ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ከሚባሉት ሊቅ ዘንድ ገብቼ አስነጋሪነት፣ ዘራፊነት፣ ሙሉ የቅኔ ሙያ እርባ ቅምር አገባብ፣ አዋጅ የሚባሉትን የቅኔ ሙያዎች ተምሬ በ፲፱፻፸፰ ዓ.ም አካባቢ ከእርሳቸው አስመሰከርኩ፡፡

የቅኔ ትምህርቴን ስጨርስ ድቁናን በ፲፱፻፸፫ ዓ.ም ፍኖተ ሰላም ከአቡነ መቃርዮስ ተቀበልኩ፡፡ ድቁና ስቀበል ከዕድሜ እኩዮቼ ዘግይቼ በደንብ ቅኔ አውቄ ነበር የወሰድኩት፡፡ ምክንያቱም ደግሞ አባቴ በልጅነቴ ድቁና እንድቀበል አይፈልጉም ነበር፡፡ አባቴ ይህንን ያደረጉበት ምክንያትም በቤተ መቅደስ አገልግሎት ቅዳሴ ላይ ብቻ ስለምታተኩር ሌሎቹን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳትማር ትቀራለህ ብለው ስለሚሰጉ ነበር፡፡

በመቀጠል ዲማ ጊዮርጊስ ገብቼ መጻሕፍተ ሐዲሳትን አለቃ ማርቆስ ከሚባሉ ሊቅ ዘንድ ተማርኩ፡፡ ሐዲሳትን አጠናቅቄ ካስመሰከርኩ በኋላ ወደ ትውልድ ቀዬ ሄጄ ከ፲፫ ዓመታት በላይ ጉባኤ ዘርግቼ ቅኔና ሐዲሳትን አስተማርኩ፡፡

ታዲያ እዚህ ለመድረስ በጉባኤ ቤት ውስጥ ብዙ ፈተናዎችን አልፌ ነው፡፡ ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ኢሕአፓ ነህ ተብዬ ታሰርኩ፡፤ በዚህ ምክንያት የደረብኝ የሥነ ልቡና ጠባሳ እስከ አሁን ድረስ አልሻረልኝም፡፡ ምክንያቱም ልጅ ስለነበርኩ መሣሪያ የታጠቀ፣የሚያስፈራ አካል ፊት ቀርቦ መጠየቅና ብዙ እንግልት ግርፋት ሁሉ ደርሶብኛል፡፡ ያ በጣም በሕይወቴ የማልረሳው አስከፊ ጊዜ ነው፡፡

አንድ ጊዜ ከጉባኤ ቤት እያለሁ አንድ ከደርግ አምልጦ የጠፋ ሽፍታ ደበሎ ለብሶ ተማሪ ቤት  ውስጥ አለ በማለት አንድ የአካባቢው ገበሬ ይጠቁማል፡፡ በዚህ ምክንያት ከወረዳ፣ ከአውራጃ ጦር መሣሪያ፣ ሌሊት መንገድ መሪ ይዘው ሲጓዙ  አድረው ጠዋት ትምህርት ቤቱን ከበቡት፡፡ እኔ መረጃው ስላልነበረኝ ትልቁን ባለ ሰባት አጎዛ ደበሎዬን ለብሼ ወደ መምህሬ ስሔድ መንገድ ላይ መሣሪያ ደቅነው አስቆሙኝ፡፡ ሲፈትሹኝ ከአንዲት አቡጀዲና የለበስኩት ደበሎ ውጪ ሌላ ምንም ሊያገኙብኝ አልቻሉም፡፡ እስኪነጋ ድረስ ፀጉረ ልውጥ የሆነ ተማሪ መስሎ የገባ ሰው አለ እያሉ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲጠይቁኝና ሲመረምሩኝ አድረው ጠዋት ሲነጋ ጉባኤ ቤቱ ተከበበ፣ ተማሪዎቹንም በድጋሚ ሜዳ ላይ አስወጥተው ፈተሹ፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቁም የተማሪውን ምግብ ሁሉ ሽምብራው፣ በቆሎው ለቀለብ የተቀመጠውን ሁሉ እየደፉ ፍተሻ አካሔዱ፡፡ ከቤተሰብ የተሰጠንና ለክፉ ቀን ብለን በየግላችን ያስቀመጥነውን ሳንቲም ዘርፈውን አሰቃይተውን ሔዱ፡፡ ይህ ምን ጊዜም የማልረሳው የተማሪ ቤት ክፉ ገጠመኜ ነው፡፡

ሌላው በማስተምርበት ጊዜ በተለይ የደርግ መንግሥት ተማሪዎችን እያፈሰ ወደ ጦርነት የሚልክበት ጊዜ ነውና ተማሪዎቼ በዚያ ምክንያት የሚያሠቃዩት  ዛሬም ከውስጤ አይጠፋም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደርግ ማኅበረሰቡ ተማሪን እንዲጠላ ያደርግ ነበር፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ሠርቶ እንዳይበላ ለምኖ የሚበላ እያለ የሚያሰራጨው የአብነት ተማሪን የመጥላት ዘመቻ ብዙ ጫና ያደርስብን ነበር፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ወደ  ሰዋሰወ  ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት ማሰልጠኛ  እንዴት ሊገቡ ቻሉ?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ ፡- በ፲፱፻፺፫ ዓ.ም በቅኔና በመጻሕፍት ትርጓሜ በሳል ሙያ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን  ሰዎች  እንድትልኩልን በሚል  ከሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ለየሀገረ ስብከቱ ደብዳቤ ሲበተን ለኛም  ደብዳቤው ደረሰ፡፡  በጊዜው የሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት ማሠልጠኛን ይመሩት የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ ይባሉ ነበር፡፡ ብፀዕ አቡነ በርናባስ በቅኔ ሙያዬ ያውቁኝ ነበርና ያንን ልጅ አምጡልኝ እርሱን ነው የምፈልገው አሉ፡፡ በወቅቱ እኔ ፻፪ (መቶ ሁለት) ብር እየተከፈለኝ ትንሽ ወረዳ ላይ ነበር የማስተምረው፡፡ ከዚያች ከማስተምርባት ወረዳ  አንሥተው ወደዚህ ወደ ታላቁ የካህናት ማሠልጠኛ አመጡኝ፡፡ ተፈትኜ አልፌ ለአራት ዓመታት የነገረ መለኮትን ትምህርት፣ በተለይም መጻሕፍተ ብሉያትን ከኔታ ገብረሥላሴ ተምሬ በከፍተኛ ማዕረግ በዲፕሎማ ተመረቅኩ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡-   ሥልጣነ ክህነት መቼ ተቀበሉ? 

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ፡-  በ፲፱፻፸፫ ዓ.ም ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ  የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ ፍኖተ ሰላም መጥተው ከእሳቸው ነው የድቁና ማዕረግ የተቀበልኩት፡፡ የቅስናን ማዕረግ የተቀበልኩት ደግሞ ከአቡነ ቶማስ ፳፻፪ ዓ.ም ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡-  እስቲ ስለ አገልግሎት ዘመንዎ ያጫውቱን?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ፡-  አገልግሎት የጀመርኩት ፲፱፻፸፫ ዓ.ም ተወልጄ ባደኩበት ሰከላ ወረዳ ላይ ሲሆን በወቅቱ ዲያቆን ብሆንም በቅኔና በሐዲሳት መምህርነት በአገልግሎት ላይ ነበርኩ፡፡  በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአድባራት የቅኔ መምህር ይፈልግ ስለነበር በጊዜው እኔ ደግሞ በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት ማሠልጠኛ ልመረቅ  አንድ ዓመት ብቻ ይቀረኝ ስለነበር  ተወዳድሬ በጥሩ ውጤት አለፍኩ፡፡ ለጽርሐ ጽዮን ጎላ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቅኔ መምህርነት፣ በስብከተ ወንጌል፣ በሰንበት ትምህርት ቤት አስተባባሪነት ብሎም በቤተ ክርስቲያን ሁለገብ አገልግሎት ለ፲፩ ዓመታት አገለገልኩ፡፡

ከዚህ በኋላ በሀገረ ስብከቱ ጥያቄ ቀርቦልኝ  ደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተመድቤ ጉባኤ ዘርግቼ እስከ አሁን ድረስ እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ተማሪዎችን በስብከተ ወንጌል፣ በአብነት ትምህርት፣ በትርጓሜ መጻሕፍት ሁሉ አስጀምሬአቸው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡

እንግዲህ በአገልግሎት ዘመኔ ብዙ ሠርቻለሁ ብዬ የምለው ሳይሆን ወደፊት በለጠ  አገለግላለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ቢመቻችልኝ ግን ከዚህ በላይ የመሥራት ጉጉት ብቻ ሳይሆን በዕውቀት የታገዘ አቅም አለኝ፡፡ ሌላው ከመደበኛ አገልግሎቴ ውጪ የማስተምራቸው የቅኔ ተማሪዎችና ባለሙያዎች አሉኝ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሌላ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የመጡ ቅኔያቸው የጠፋባቸው፣ የቀዘቀዘባቸው ለማጠንከር፤ እንደ አዲስ መጥተው የሚማሩ ናቸው፡፡ ከማስተምራቸው ከአዲሶቹ ተማሪዎች ውስጥ አሁን ላይ  ቤት ሊሞሉ የተቃረቡ ተማሪዎች  ያሉኝ ሲሆን ከእነዚህም የማስተምራቸው በጣም በጥሩ ሁኔታ ቅኔን እየለዩ ያሉ አሉ፡፡  ለወደፊቱም ይህንን ሙያዬን የበለጠ  ላገለግልበት እፈልጋለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡-  ምን ያህል ተማሪዎችን አፍርተዋል?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ፡-  በተለይ በገጠር ብዙ ተማሪዎችን አስተምሬያለሁ ቢያንስ በጉባኤ ቤት ከ፪፻ እስከ ፫፻ ድረስ የሚደርስ ተማሪዎችን ሳስተምር ነበር፡፡ እዚያ ከአስተማርኳቸው ውስጥ ብዙዎቹ አሁን በአዲስ አበባ በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት በመምህርነት እያገለገሉ ናቸው፡፡

በሀገር ቤት ደግሞ እንዲሁ ጉባኤ ተክለው የሚስተምሩ ልጆች አሉኝ፡፡ አስተምሬያቸው ወደ ዘመናዊ ትምህርት ገብተው ትምህርታቸውን ጨርሰው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ አሉ፡፡ ሀገር ቤትም በቀዳሽነት፣ በድቁናና በመምህርነት በተለያየ ሙያ ያስተማርኳቸው በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ ክፍላተ ሀገር በአገልግሎት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ዛሬም ድረስ ተማሪዎቼ የነበሩ ከትምህርት ባሻገር  ምክር፣ ንስሓ  ያስፈልገናል ባሉ ጊዜ ይጠሩኛል፤ የሚፈልጉትን ምክርና እገዛ፣ ጸሎት አድርጌ አጽናንቼቸው ተስፋ እንዳይቆርጡ የተቻለኝን አባታዊ ምክር እሰጣቸዋለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ትዳር መሥርተዋል? ከመሠረቱ ስለ ቤተሰብዎ ቢነግሩን፡፡

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ፡- ትዳር የመሠረትኩት ወደ ሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት ማሠልጠኛ ከመምጣቴ በፊት በገጠር እያለሁ ነው፡፡ የአምስት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ቤተሰቤን በገጠር ትቼ ነበር አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ ያ በጊዜው በጣም ያስጨንቀኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርቴን ጨርሼ ወደ አገልግሎት ስገባ ከገጠር ቤተሰቤን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ልጆቼን አስተማርኩ፡፡

በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ልጄ በሲቪል ምህንድስና በማስተርስ ዲግሪ ተመርቆ በሥራ ላይ ይገኛል፣ ሁለተኛውም ልጄ በመካኒካል ኢንጅነሪንግ እንዲሁም ሦስተኛዋ ተመርቃ በሥራ ላይ ስትሆን ሁለቶቹ ገና የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ናቸው፡፡ ልጆቼ በዚህ ደረጃ ነው ያሉት በዚህ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊውን ትምህርት ስላላስተማርኳቸው አሁን ይቆጨኛል፡፡ አራት ዓመት ተለይቻቸው ስቆይ ከጎናቸው ሆኜ ፊደል ማስቆጠር አልቻልኩም፡፡ እዚያው ባለው በአካባቢው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገብተው ነው የተማሩት፡፡ እዚህ ለማስተማር አልተመቻልኝም፡፡ እኔ የምኖረው ሽሮ ሜዳ ነው የማገለግለው ደግሞ ጎላ ሚካኤል ነበር፡፡ በቦታ ርቀትና በሥራ ምክንያት እጀምርላቸውና ይቀራል፡፡  እነርሱም ወደ ዘመናዊው ትምህርት አዘነበሉ፡፡ ዛሬ ድረስ ይጸጽተኛል፡፡ ነገር ግን ልጆቼን የሃይማኖት ትምህርት ባላስተምራቸውም በሥነ ምግባር ኮትኩቼ ነው ያሳደግኳቸው፣ በእምነታቸው ጠንካሮች ናቸው፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፡- ርስዎ መሠረትዎ የአብነት ትምህርት ነውና በአሁኑ ወቅት የአብነት ትምህርት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ይላሉን? ለሀገር ያበረከተውን ፋይዳስ እንዴት ይገልጹታል?

መጋቤ ምሥጢር  ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ፡-  ቀድሞ በአብነት ትምህርት ቤት ያላለፈ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም መሪዎቻችንም ይሁኑ በተለያዩ ሙያዎች ሀገራቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ ባለሙያዎች፣ አማካሪዎችም ከቤተ ክርስቲያን የተገኙ የአብነት ትምህርት ቤት ውጤቶች ነበሩ፡፡ ይህንን ማንም የሚክደው አይደለም፡፡ ደራስያን፣ የቲያትር ባለሙያዎች፣ ገጣሚዎቻችን ሁሉም ቢሆኑ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያለፉ ነበሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ በገዳማቱ፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉባኤ ዘርግታ፤ ከፊደል እስከ መልእክተ ዮሐንስ፣ ከመልእክተ ዮሐንስ እስከ ንባብ፣ ከንባብ እስከ ዳዊት፣ ከዳዊት መልሳ እንደገና ንባቡን ከአጠናከረች በኋላ ድጓ፣ የቃል ትምህርት፣ ውዳሴ ማርያም፣ መስተጋብዕ፣ …ወዘተ የቅዱስ ያሬድ ሙያዎችን በሙሉ አስተምራ፣ ወደ  ቅኔ ቤት በመላክ የምሥጢር ባለቤት የሆነውን የግእዝ ቋንቋ በማስተማር፣ ዛሬ እየደበዘዘ ቢመጣም ቤተ ክርስቲያንና ሊቃውንቱ ለትውልድ ለማስተላለፍ ብዙ ደክመዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን መምህራን በየመልኩ አሏት፡፡ ለአብነት ያህል ዳዊት የሚያስደግሙ፣ የዜማውን ሙያ ከጾመ ድጓ እስከ ድጓ ፤ ከምዕራፍ እስከ ዝማሬ መዋሥዕት ዜማ ድረስ አጠናክረው የያዙ ሊቃውንት አሉ፡፡ ቅኔ መዝለቅ የፈለገውን በቅኔ ሙያ እንዲዘልቅ እያደረገች፣ ብሉያትን፣ ሐዲሳትን፣ መጽሕፍተ መነኮሳትን፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን በየጉባኤ ቤቱ ታላላቅ በሆኑት እንደ ጎንደር፣ ሞጣ፣ መርጡለ ማርያም ፣ ቦሩ ሜዳ ፣ ደብረ ሊባኖስ … ሌሎችም ቦታዎች አብነት ትምህርት ቤቶች አራቱም ጉባኤያት ይሰጥባቸዋል፡፡ እዚህ አዲስ አበባ እንኳን  በአታ ለማርያምን ማንሣት ይቻላል፡፡ በየመልኩ፣ በየዘርፉ እንደ ቅደም ተከተሉ አስቀምጣ፣ የማስተማር ሥነ ዘዴውንም በአግባቡ የምታውቅና የምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ አሁን ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን እንደ ቀድሞው ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ ወንበሮች እያታጠፉ፣ ሊቃውንቱ እየተሰደዱ በመሆናቸው ቤተክርስቲያን  በዚህ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ሰው መሠረቱን መልቀቅ የለበትም፣ አብነት ትምህርት ቤቶቻችንን ቸል እያልናቸው የመጣን ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን ከጥንት ጀምሮ መሠረታችንን አንለቅም ብለው የሚፍጨረጨሩ መምህራንና ጉባኤ ቤቶች ያሉ ቢሆኑም እገዛ ካልተደረገላቸው  ግን ያሰጋሉ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሕፃናቱ ሲያድጉ (ከፍ ሲሉ) የሚሰጠውን ለይታ ቅደም ተከተል አስቀምጣ ስታስተምር የኖረች፣ ለሀገር፣ ለታሪክ፣ ለሃይማኖት፣ ለሥነ ምግባር መሠረት ሆና ኖራለች፡፡ የእኛ ስለሆነች አይደለም የምናወድሳት እውነቱን ነው የምንናገረው፡፡ ዘመናዊው ትምህርት ቤት መጥቶ ቢጋፋትም ቤተ ክርስቲያን ግን ይህንን ሁሉ ሙያ አስተምራ ትውልድን አንጻ፣ ታሪክን ጠብቃ እዚህ ያደረሰች ናትና የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን ውለታ መዘንጋት የለበትም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ቋንቋ የሆነው ግእዝ የማኅበረሰቡም መነጋገሪያ ቋንቋ ነበር፡፡ አማርኛ እየገነነ ሲመጣ ያንን ቋንቋ እንዳይጠፋ ጠብቃ እስከ አሁን ድረስ ይዛ የተጓዘች፣ ለትውልድ ያቆየች ይህችው ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ የግእዝ ቋንቋ መቆየት ደግሞ የሀገር መቆየት ነው፡፡ የተጻፉ ታሪኮች፣ ጥበቦች፣ ሥነ ምግባር፣ ሃይማኖታዊ ቀኖናዎች ሁሉ ከዚያ ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡ ሌላው ሥዕል፣ ቀለም ቀምማ፣ ብራና ፍቃ፣ መጻሕፍትን ጽፋ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የተጫወተችው ሚና እንዲሁ በቀላሉ አውርተን የምንተዋቸው አይደሉም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዘመን አቆጣጠር የሆነው ባሕረ ሐሳብን ያፈለቀች፣ የራሷ ፊደልና ቁጥር የቀረጸች ይህንንም ለዓለም ያበረከተች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የእነዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ከሌሎች ዓለማት የተለየ ውብ ማንነት እንዲኖረን ያደረገች፣ በሀገር በቀል ዕውቀት እንድንኮራ ያደረገችን ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያበረከተችውን በቀላሉ ገልጸን የምንዘልቀው አይደለም፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የማኅበራዊ ሕይወት ተሳትፎዎ ምን ይመስላል?  

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀፀላ ፈንቴ፡-  በእውነት በማኅበራዊ  ሕይወት መሳተፍ በጣም ከምወዳቸው ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡ ለሰው በጎ ማድረግ፣ ለተቸገረ በቶሎ መድረስ ነው፡፡ ምንአልባትም ብዙ ሰዎች በጎ ማድረግን የሚያስቡት በገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ሰው ሀሳብም ሊቸገር ስለሚችል በሐሳብ መርዳት፣ አብሮ ችግርን መጋራት መፍትሔ መፈለግ በጎ ማድረግ ነው፡፡

ወጣቶች፣ ትልልቅ ወንድሞች፣ ሊያማክሩኝ ሲመጡ ያለኝን ሳልሰስት፣ ሳይደክመኝ ነው የማማክረው፡፡ መንፈሳዊ ሕወታቸው እንዳይዳከም፣ ትዳር የሚገቡት ወደ ትዳር እንዲገቡ በማስተማር በመምከር እረዳለሁ፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤትም ላይ ወጣቶችን በመደገፍ እንደ አባትነቴ በኃላፊነት አግዛቸዋለሁ፡፡ በተለይ ወጣቶችን፤ ምክንያቱም ሃይማኖትና ሀገር ወጣት ሲረከበው ነው ሀገርነቱም እምነቱም ሊቀጥል የሚችለው የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡ እና እንደዚህ ባለው  ማሕበራዊ ሕይወት ሁሉ  እሳተፋለሁ፡፡ በተጨማሪ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያስፈልጋቸው፣ በገጠር ያሉ አብተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣ ልብሰ ተክህኖ ሲያጡ ግለሰቦችን፣ ማኅበራትን በማስተባበር የአቅሜን እንዲረዱ እጥራለሁ፡፡

ባለኝ ማኅበራዊ ሕይወት በእምነት ከማይመስሉኝ ሰዎች  ጋር እንኳን ተግባብቼ፣ የእነርሱን ሳልነካ፣ የኔንም ሳላስነካ  በፍቅር ነው የምኖረው፡፡ እኔ በምኖርበት አካባቢ ብዙ ፕሮቴስታንት፣ ሙስሊሞች  አሉ፡፡ ሰው ቢጣላ ሸምጋይ አድርገውኝ ነው በፍቅር የምንኖረው፡፡ ቢቻል ሰው ሁሉ ከሰው ጋር በፍቅር፣ በሰላም መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም እምነት ማለት፣ እግዚአብሔር ማለት ፍቅር  ስለሆነ፡፡ እንደ ቅንነት በዓለም ላይ እምወደው ነገር የለም፡፡ ቅን መሆንና፣ በቅንነት ማድረግ፤ ከሰው ጋር ተፋቅሮ መኖር ነው ለማኅበራዊ ኑሮ የሚስፈልገው፡፡ ሌላው በስብከተ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ ከመደበኛ ሥራዬ ውጭ የሚሰጡኝን አገልግሎቶች በቅንነት ነው ማገለግለው፡፡ ሀገሬን፣ ቤተ ክርስቲያኔን ሕዝቤን በሙያዬ የማገልገል ግዴታ አለብኝ፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፡- በመጨረሻም በሚያስተላልፉት መልእክት ቆይታችንን ብናጠናቅቅ?

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ፡- መልካም ሥራ ሠርቶ ማለፍ በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ የሚያስመሰግን ነው፡፡  ጥላቻ ማንም ደካማ ሰው የሚሠራው ሥራ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከሰው፣ ነገርን ከነገር ወሬ በማቀበል ብቻ በአንዲት ቀን ሀገር ለብልቦ መዋል ይችላል፡፡ ሰውን ወደ መልካም ሥራ ለማስገባት ግን ብዙ ጥረት ብዙ ዕውቀትንና ቅንነትን  የሚጠይቅ፣ ብዙ ጊዜም የሚፈልግ በመሆኑ እነዚህ  በውስጣችን ስለመኖራቸው  ራሳችንን ቀድመን ብናይ ፣ ማስተካከል ያለብንን ነገር ብናስተካክል መልካም ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ከክፉ ሥራዎችን ጋር ባንተባበር፡፡ መጀመሪያ ራሳችንን የምንሠራውን ሥራ  ብንፈትሸው፣ የምናስበውን ብንመረምረው፣ ውሎአችንን ብንገመግም፣ አዳራችንን ብናጤን፤ ከሰው ጋር እንዴት መኖር እንደሚገባን  ያንጊዜ  ይገባናል፡፡ እኔ ለሀገሬ፣ ለእምነቴ ምን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ማለት አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ከመልካም ነገር ጋር ተባበሩ፣ ክፉ ሥራን ተጸየፉ ይለናል፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ “ራስን መግዛት” ይላል  አቅጣጫችንን መቆጣጠር ብንችል ፤ በኛ ምክንያት ብዙዎች ባይሞቱ የነፍስ ተጠያቂዎች ባንሆን ዛሬ ሰው ባያየንም እግዚአብሔር ያየናል፡፡ የፈጠረውን ፍጥረት ያያልና እንደነ ቃየል እንዳንጠፋ፡፡  ክፉው ነገር ከውስጣችን  መንገድ እያጠናን እየመረመርን ለሀገር ለቤተ ክርስቲያን ስንል ብንተባበር መልካም ነው፡፡ ካልሆነልን ደግሞ ከክፉ አድራጊዎችና አድራጎት ጋር ባንተባበር፡፡ መልካም የሆነው ነገር ይጠቅመናል፣ ለሀገርም አብረን ለምንኖርም ለታሪክም ጠቃሚ ነው፡፡ መጥፎ ድርጊታችን በታሪክ ያስወቅሰናል ለትውልድ ይቆያል፡፡ ስለዚህ ባለንና እግዚአብሔር በሰጠን ዕድሜአችን መልካም ነገር ሠርተን፣ ለሚመጣው ትውልድ አርአያ መሆን ይገባናል እላለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- እግዚአብሔር ይስጥልን አባታችን፡፡

መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ፡፡