ሁለት አገልጋዮች በድንገተኛ የመኪና አደጋ ሕይወታቸው ዐለፈ
በካሣሁን ለምለሙ
የነቀምቴ ማእከል አገልጋይ የነበሩት ዲ/ን መልካሙ ረጋሳ እና ዲ/ን ሽፈራው ከበደ በገተማ ወረዳ ለአገልግሎት ሲፋጠኑ መስከረም ፳ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ሕይወታቸው ዐለፈ፡፡
ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ረጋሳ የነቀምቴ ማእከል ጸሐፊ የነበረ ሲሆን በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም ከእናቱ ከወ/ሮ አሙሴ ተፈራ እና ከአባቱ አቶ ረጋሳ ተወለደ፡፡፡ ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ገና በልጅነቱ የብዙ ሙያዎች ባለቤት የነበረና የተለያዩ ጽሑፎችን፣ መንፈሳዊ ግጥሞችን እንዲሁም ዋሽትና ሌሎች መንፈሳዊ የዜማ መሣሪያዎችን ጭምር መጫወት የሚችል ነበረ፡፡ወንጌልን እየተዘዋወረ ከማስተማሩ በተጨማሪ በርካታ የመዝሙር ካሴቶችን አውጥቶ ለአገልግሎት አውሏል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮም ከቤተ ክርስቲያን ያልተለየና ዘወትር ቤተ ክርስቲያንን በዲቁናና በዝማሬ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
በ፳፻፭ ዓ.ም 12ኛ ክፍልን ካጠናቀቀ በኋላ መንፈሳዊ ሥዕላትን ይሥል ነበር፡፡ በአፋን ኦሮሞ የመዝሙር ካሴቶችን አበርክቷል፡፡ ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ በትሕትና የሚታወቅና ያለ አባት ያሳደጉትን እናቱንና አያቱን በቻለው መጠን የሚረዳ ሲሆን በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ሕፃናትን ዘወትር ነገረ ሃይማኖት የሚያስተምርና የዕድሜ እኩዮቹን የሚመክር በመሆኑ ለሁሉም ምሳሌ የሆነ ወጣት አገልጋይ ነበር፡፡
ዘማሪ ዲ/ን መልካሙ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወደ ገተማ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአገልጋይ ወንድሙ ከዲ/ን ሽፈራው ከበደ ጋር እየሔዱ ሳለ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በደረሰባቸው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በተወለደ በ፳፬ ዓመቱ ሕይወቱ ዐልፏል፡፡
ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ጽዋ ማኅበራት የተሐድሶ መናፍቃንን ጥፋት በተመለከተ ሥልጠና ለመስጠት እንዲሁም የገተማ ወረዳ ማእከል አባላትን ለመቃኘት እየሔዱ በነበረበት ወቅት አደጋው እንደደረሰባቸው የነቀምቴ ማእከል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
ሌላኛው ድንገተኛ የመኪና አደጋ ደረሰበት ዘማሪ ዲ/ን ሽፈራው ከበደ ኢትቻ ሲሆን ከአባቱ ከአቶ ከበደ ኢትቻ እና ከእናቱ ከወ/ሮ እየሩስ አለቃ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም በምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ሶምቦ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ተወለደ፡፡
ከ፩-፲ኛ ክፍል በኪረሙ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን ኤልፓ ኮሌጅ ጂማ ድስትሪክት የኮሌጅ ትምርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቅቋል፡፡ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም በኪረሙ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዲቁናን ተቀብሎ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ባቦ ጋምቤላ ወረዳ፣ ህዳሴ ቴሌኮም ጋምቤላ፣ ነጆ ህዳሴ ተሌኮም እንዲሁም በነቀምቴ ከተማ ህዳሴ ቴሌኮም ውስጥ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተጨማሪ ሀገሩን አገልግሏል፡፡
በኪረሙ ቅድስት ሥላሴ ሰንበት ትምህርት ቤት አባል እና ሥራ አስፈጻሚ የነበረ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳንም ከመደበኛ አባልነት ጀምሮ እስከ ሥራ አስፋጻሚነት አገልግሏል፡፡ በነጆ ወረዳ ማእከል ሒሳብና ንብረት ክፍል ሓላፊ እንዲሁም በነቀምቴ ማእከል ደግሞ የሰው ኃይል ልማት እና አስተዳደር በመሆን ሠርቷል፡፡
ዲ/ን ሽፈራው ከበደ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በተመለከተ ለምእመናንና ለአገልጋዮች በደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሥልጠና ይሰጥ እንደነበር ተገልጧል፡፡በሕይወቱ ትሑት፣ ታዛዥ እና በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የሚወደድና በአገልግሎቱም አርአያ የሆነ ወጣት አገልጋይ ነበረ፡፡ ዲ/ን ሽፈራው ከበደ ባለ ትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበረ፡፡
ለአገልግሎት እየሔደ እያለ መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም በደረሰበት ድንገተኛ የመኪና አደጋ በተወለደ በ፳፯ ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ዝግጅት ክፍሉም ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን መጽናናትን እየተመኘን እግዚአብሔር አምላክ የሟቾቹን ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያኖር እንጸልያለን፡፡
ምንጭ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ኛዓመት ቁ፪/ቅጽ ፳፮ ቁጥር ፫፻፺፭ ከጥቅምት፩-፲፭ ቀን፳፻፲ወ፩ ዓ.ም