ሁለቱ የቤተ ክርስቲያን አዕማዶች
ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም
ቅዱስ ጴጥሮስ
የዮና ልጅ ስምዖን የተባለው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተወለደው በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተ ሳይዳ ነው፡፡ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋርም ዓሣ ያሠግር ነበር፡፡ በዚህን ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ» በማለት ቅዱስ ጴጥሮስን ከወንድሙ ጋር ጠራው፡፡ (ማቴ.፬፥፲፰፣ ፩ኛቆሮ.፩፥፲፯፣ሐዋ.፳፪፥፫) በዚህ ጥሪ መሠረትም መተዳደሪያው የነበረውን መረቡንና ታንኳውን እንዲሁም አባቱን ትቶ ጌታውን ተከተለ፤ ዕድሜው ፶፭ ዓመት ነበር፡፡ (ዜና ሐዋርያት ገጽ ፫-፲፭)
በዕብራይስጥ ጴጥሮስ ‹ዐለት› ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም» በማለት ተናግሯል። (ማቴ.፲፮፥፲፰) ጌታም ይህን ክብር ለሐዋርያው የሰጠው ጴጥሮስ የእርሱን ወልድ እግዚአብሔር መሆን ስለመሠከረ ነው፡፡
ጴጥሮስ ጌታ ዐለት እንደሆነ ቢመሠክርለትም አስቀድሞ ግን እናቱ ባወጣችለት ስም ‹ስምዖን› ተብሎ የሚጠራ አሳ አስጋሪ ሰው እንደነበር ታሪኩ ይገልጻል፡፡ ጌታችን ከመረጠው በኋላ የአምላኩን ትእዛዝ በመጠበቅ ሲያገለግል ኖሯል፡፡ ቃሉንም (ወንጌልን) ማወቅም ብቻም ሳይሆን በገቢረ ተአምሩ ተመልክቷል፡፡ ይህንም በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ተጽፎ እናገኘዋለን፤ «ደቀ መዛሙርቱ በታንኳው ገብተው ወደ ባሕር ማዶ ቀድመውት ይሄዱ ዘንድ ግድ አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ሕዝቡን አሰናብቶ ሊጸልይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር፡፡ ታንኳው ግን እነሆ፥ በባሕሩን መካከል ነበር፤ ከማዕበል የተነሣ ይታወክ ነበር፤ ነፋስ ከፊቱ ነበርና፡፡ ከሌሊቱም በአራተኛዪቱ ክፍለ ሰዓት ጌታችን ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ እነርሱም፣ «ምትሐት ነው!» ብለውም ደገነገጡ፤ ከፍርሃትም የተነሣ ጮኹ፡፡ ወዲያውም ኢየሱስም፥ «አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ አትፍሩ» አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ «አቤቱ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ» አለው። እርሱም «ና» አለው። ጴጥሮስም ከታንኳው ወርዶ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው እየተራመደ ላይ ሄደ። ነገር ግን ነፋሱ በርትቶ ባየ ጊዜ ፈራ፤ ሊስጥምም ጀምረ፥ ያንጊዜም «አቤቱ፥ አድነኝ!» ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ጌታችን ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና «አንተ እምነት የጐደለህ ለምን ተጠራጠርህ?» አለው። ወደ ታንኳው በወጣ ጊዜ ወዲያው ነፋሱ ፀጥ አለ። በታንኳው ውስጥ የነበሩት ሁሉ «በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ» እያሉ ሰገዱለት። ባሕሩንም ተሻግረው ወደ ጌንሴሬጥ ምድር ደረሱ። ወደ አውራጃዋዎቻቸውም ሁሉ ላኩ፤ በሽተኞችንም ሁሉ አመጡለት፡፡ የልብሱንም ዘርፍ ይዳስሱ ዘንድ ለመኑት፤ የዳሰሱትም ሁሉ ይድኑ ነበር።» (ማቴ.፲፬፥፳፪-፴፮) በማቴዎስ ወንጌል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጴጥሮስን አማት ማዳኑን የተቀሰበት ምዕራፍ በመኖሩም ቅዱስ ጴጥሮስ ባለትዳር እንደነበር እንረዳለን፡፡ (ማቴ.፰፥፲፬-፲፭)
ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስ በደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮቱን ሲገልጥ፣ በኢያኤሮስ ቤት ልጁን ሲፈውስ እና በጌቴሴማኒ ጸሎት ሲያደርግ ከሐዋርያቱ ቅዱስ ዮሐንስና ቅዱስ ያዕቆብ ጋር አብሮ አልተለየም፡፡ ሆኖም ግን ጴጥሮስ ጌታችን ክዶ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል። ይህንንም ጌታችን እራሱ አስቀድሞ ዐውቆ እንዲህ ብሎታል፤ «ነፍስህን ስለ እኔ አሳልፈህ ትሰጣለህን? እውነት እውነት እልሃለሁ ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡» (ዮሐ.፲፫፥፴፰) ጌታችን ለሰዎች ሁሉ ድኅነት ሲል በመስቀል ይሰቀል ዘንድ በአይሁድ ተይዞ መከራ ሲቀበል እርሱን የሚያውቁትን ደግሞ እየለዩ በተመሳሳይ መልኩ ሊያሰቃዩአቸው በሞከሩ ጊዜ ጴጥሮስ ለጌታው ከመመሥከር ይልቅ ክዶታል፡፡ በሚክድበት ጊዜም ዶሮ ስትጮህ ሰምቶ ጌታችን የነገረውን ቃል በማስታወስ መሪር ልቅሶን አለቀሰ፤ ይህም እንደ ንስሓ ተቆጠረለት፡፡ (ማር.፲፬፥፷፰-፸፪)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶና ሞትን ድል ነሥቶ በሦስተኛው ቀን ሲነሣ ለደቀ መዝሙሩ በተገለጠበት ጊዜ ጴጥሮስን «ትወደኛለህን?» ብሎ ጠይቆታል፤ ይህን ጥያቄ የጠየቀው ደጋግሞ ሦስት ጊዜ ነበር፤ እርሱም በመጨረሻ «አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እኔም እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ» ብሎ መልሶለታል። ጌታችንም ግልገሎቹን እንዲያሠማራ፣ ጠቦቶቹን እንዲጠብቅ፣ በጐቹን እንዲያሠማራ አደራ አለው። (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)
ጌታችን ካረገ በኋላም በአይሁድ ሸንጐ ድውይ ፈወስክ ተብሎ በተከሰሰ ጊዜ በድፍረት ስለ መድኃኔዓለም ክርስቶስ መሥክሯል፤ ወደ ፍልስጥኤም፣ ሶርያ፣ ጳንጦን፣ ገላትያ፣ ቀጰዶቅያ፣ ቢታንያ እና ሮሜም ሀገርም በመጋዝ አሕዛብን አስተማረ፤ ድውያንን ፈወሰ፤ (ሐዋ ፭፥፲፭)
ለአንድ ዓመት ያህልም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ካስተማረ በኋላ ዝናው በሮማ ባለሥልጣናት ዘንድ ተሰማ ደረሰ። የኔሮን ባለሥልጣናት የሆኑት የአልቢኖስና የአግሪጳ ሚስቶች ክርስትናን በመቀበላቸው ኔሮን ንጉሠ ሮማ ቀንቶ አሳዳጊ መምህሩን ሁለቱንም ሚስቶቹን አግታሺያንና ፓፒያን በርግጫ ገደላቸው። የሮማን ከተማ ደግሞ በእሳት አቃጠላት። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከሮማ ወደ ኦፒየም ጎዳና ተጓዘ፤ በዚያም ጌታችን በሽማግሌ አምሳል ተገለጠለት፤ ሆኖም ግን ጴጥሮስ ጌታ እንደሆነ ዐውቆ በፊቱ ተደፋና «ጌታዬ ወዴት እየተጓዝክ ነው?» አለና ጠየቀው። «ዳግም በሮም ልሰቀል» አለው። ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲሰማ እጅግ አዝኖ ወደ ሮማ ተመለሰ። ሲፈልጉት ወደ ነበሩት የኔሮን ወታደሮች ሄዶ «እነሆኝ ስቀሉኝ» አላቸው፤ ቅዱስ ጴጥሮስንም ይዘው ካሠሩት በኋላ ሊቅሉት የመስቀያውን እንጨት ሲያቀርቡ «እኔ እንደ ጌታዬ ልሰቀል አይገባኝም» በማለት ቁልቁል እንዲሰቅሉት ለመናቸው። እነርሱም ቁልቁል ሰቀሉት ይህም የሆነው ሐምሌ ፭ ቀን ፷፯ ዓ.ም. ነበር፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ
በኪልቂያ አውራጃ ጠርሴስ ከተማ የተወለደው ቅዱስ ጳውሎስ ከፈሪሳውያን ወገን ነው፡፡ የዘር ሐረጉ ከነገደ ብንያም እርሱም ሮማዊ እንደሆነ ራሱ ተናግሯል፡፡ በልጅነቱ አስተዋይ እንደነበር በቅዱሳት መጻሕፍት ይገልጻል፡፡ አስተዳደጉም የአይሁድ ሥርዓት ነበር፡፡ የመምህር ገማልያል ተማሪም ስለነበር የሕግ ትምህርት ተምሯል፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ጥበብና እድም አብሮ እንደተማረና ጳውሎስ ድንኳን መስፋት ተምሮ እንደነበር ታሪኩ ምስክር ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ይኖር የነበረው የሕግና ፍልስፍና ትምህርት ቤቶች በብዛት ይገኝባት በነበረችው የጤርሰስ ከተማ ነው፡፡
ጳውሎስ ሐዋርያ ከመሆኑ በፊት አስቀድሞ ሳውል ተብሎ የሚጠራ ክርስቲያኖችንም እያሳደደ የሚገድል ሰው ነበር፡፡ ለዚህም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማስረጃ ያደረጉት የእርሱ ለአባቶቹ ሕግ ቀናተኛ መሆኑ የክርስትናን ትምህርት እንዲቃወም ማድረጉን ነው፡፡ ‹‹ሳውል ግን አብያተ ቤተ ክርስቲያናትን ይቃወም ነበር፤ የሰውንም ቤት ሁሉ ይበረብር ነበር፤ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጎተተ ወደ ወኅኒ ቤት ያስገባቸው ነበር፡፡›› (የሐዋ.፰፥፫)
በዚህ ብቻም አላበቃም፤ የቀድሞ ሳውል የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርትን ለመግደል በመዛት ወደ እነርሱ ሄዶ ለሊቀ ካህናቱ የሥልጣን ደብዳቤ እንደለመናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሷል፡፡ ይህም ምንአልባት በመንገድ የሚያገኘው ሰው የሚኖር ከሆነ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደማስቆ ያሉ ምኵራቦች እንዲፈቅዱለት ለማድረግ ነው፡፡ በደማስቆ ከተማ ሲደርስም በድንገት መብረቅ ከሰማይ ብልጭ ሲልበት መሬት ላይ ወደቀ፤ ወዲያውም ‹‹ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?›› የሚል ድምጽ ሰማ፤ ሳውልም ‹‹አቤቱ፥ አንተ ማነህ›› አለው፤ እርሱም አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፤ በሾላ ብረት ላይ ብትቆም ለአንተ ይብስብሃል›› አለው፤ እርሱም እየፈራና እየተንቀጠቀጠ ‹‹አቤቱ፥ ምን እንዳደርግ ትሻለህ?›› አለው፤ ጌታም፥ ‹‹ተነሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚያም ልታደርግ የሚገባህን ይነግሩሃል›› አለው፡፡ ሳውልም ከምድር ተነሥቶ በሚቆምበት ጊዜ ማየት ተሳነው፤ ዓይኖቹ ቢገለጡም የሚያየው ነገር ግን አልነበረም፡፡ ለሦስት ቀናት ያህል ሳይበላና ሳይጠጣ ከቆየ በኋላም ጌታ በራእይ ለደቀ መዝሙሩ ሐናንያ ተገልጦ ባዘዘው መሠረት እጁን ጭኖ ዓይኖቹን ፈወሰለት፤ ስለመመረጡ ነገርም አስረዳው፡፡ ‹‹በአሕዛብና በነገሥታት፥ በእስራኤል ልጆችም ፊት ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ አድርጌዋለሁና፡፡›› እንዲል፤ (የሐዋ.፱፥፬-፲፭)
ሳውልም ተጠመቀ፤ ከበላና ከጠጣ በኋላ ስለበረታ ወደ በደማስቆ ከደቀ መዝሙርቱ ጋር ሰንብቶ ምኵራቦቹ በመግባት ሰብኳል፡፡ ደማስቆም ከተመለሰ በኋላ አሕዛብን በማሳመን አጥምቋቸዋል፡፡ በዚህም ጊዜ በዚያ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ሊገድሉት በማሰባቸው ክርስቲያኖቹ እርሱን ለመደበቅ ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱት፡፡
እርሱም ማስተማሩን ሳያቋርጥ በአንጾኪያ ኤፌሶን ቆሮንቶስ ሮም ከተሞች እየተዘዋወረ የእግዚአብሔርን ቃል ሰብኳል፡፡ በተአምራት ሙት አስነሥቷል፤ ድውይ ፈውሷል፡፡ ትምህርቱንም የሚያደርገው የነበረው ሰው በተሰበሰበበት በምኵራብ፣ በዐደባባይ፣ በገባያ፣ በትያትር ቦታ፣ በደስታና በኀዘን ወቅት ነው፡፡ ጳውሎስ ተብሎ የተሰየመውም በቆጵሮስ ከተማዎች ባደገረው ጎዞ እንደነበር በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጷል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ በቃል ካስተማራቸው ትምህርቶችም ይልቅ በመልክእት መልክ በጽሑፍ ያስቀመጣቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበው ለትውልድ ትውልድ ተላልፈዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የተለያዩ የመከራን ተቀብሏል፡፡ ስለዚህም ሲገልጽ «በሁሉ መከራ ስንቀበል አንጨነቅም፤ እንናቃለን፤ አንዋረድም፤ እንሰደዳለን አንጣልም፤ እንጨነቃለን አንጠፋም» በማለት ነው፡፡ (፪ኛቆሮ. ፬፥፰-፲፩)
በ፷፭ ዓ.ም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በኒቆጵልዮን ከተማ ሲያስተምር በነበረበት ወቅት ንጉሥ ኔሮን ይዞ ወደ ወኅኒ አስገብቶ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየው፤ በ፸፬ ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን በሰይፍ ተቆረጦ ሐምሌ ፭ ቀን ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡
ቅዱሳኑ ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ለዓለም የሰበኩ፣ ብዙዎችን በክርስትና ጥምቀትና በገቢረ ተአምራት ያዳኑ የቤተ ክርስቲያን አዕማዶች ናቸው፡፡
አማላጅነታቸውና ተራዳኢነታቸው አይለየን፤ አሜን!
ምንጭ፡- ፹፩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ ፭፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቁጥር ፩