ሀብዎሙ ዘይበልዑ/ክፍል ሁለት/
የሚበሉትን ስጡአቸው /ማቴ. 14፣16 /
ሀ/ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ፣ ቸርነትና መግቦት
ለ/ በመታዘዝ የሚገኘውን ታላቅ በረከት
ሐ/ ለጋስነትን
መ/ የችግር ተካፋይ መሆንን
ሠ/ ያለውን ማካፈልን
ረ/ የሥራ ድርሻን ማወቅ
የተራበውን ሕዝብ እንዲመግቡ ከጌታ የታዘዙት ደቀ መዛሙርቱ /ሐዋርያት/ ዓለምን በምግበ ሥጋ በምግበ ነፍስ እንዲጎበኙት ታዘዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እንዲጠብቁት እንዲከባከቡት ቢታመም በተሰጣቸው ሥልጣን እንዲፈውሱት ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል፡፡ መታዘዝንም አስተምሮአቸዋል፡፡
ዓለም ይህን አውቆ ወደ መጋቢዎቹ ወደ ጠባቂዎቹ ቀርቦ ምግበ ሥጋውን ምግበ ነፍሱን ሊመገብ ይገባዋል፡፡ ከሚደርስበት መከራም ሊጠበቅና ሊፈወስ ይችል ዘንድ ወደ ጠባቂዎቹ ካህናት /ሐዋርያት/ በመቅረብ ጠባቂዎቹን አውቆ ከሌላው ሊሸሽ ግድ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ከመታዘዝ አንዱ ነውና፡፡
አበው ነቢያትና ሐዋርያት ለእውነት በመታዘዛቸው ጥቂቱን በማበርከት፣ መራራውን በማጣፈጥ፣ አስገራሚ ተአምራት በማድረግ፣ በጸሎታቸው የሕዝቡን ችግር አስወግደዋል፡፡
1. ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ ለስራፕታዋ መበለት ትንሿን ዱቄት በማበርከት
2. ነቢየ እግዚአብሔር ኤልሳዕ ልጆቿ በዕዳ የተያዙባትን ሴት ጥቂቱን ዘይት በማብዛት፣ መካን ለነበረችው የሱነማይቱ ሴት ልጅ በመስጠት የአባትነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ነቢያቱም ሆነ ሐዋርያቱ በመጀመሪያ ታዛዦች ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡
የሚታዘዝ ይባረካል የማይታዘዝ ደግሞ ይረገማል፡፡ ሰው ለእግዚአብሔር ቢታዘዝ በረከትን ይቀበላል መርገሙ ከእርሱ ይርቃል፡፡
«እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና» ኢሳ. 1፣19፣ ዘዳ. 11፣27፡፡
ምግባራትን ሁሉ መታዘዝ ይቀድማቸዋል በክርስትናው ዓለም መታዘዝ ማለት፤
– ለእግዚአብሔርና ለሕጉ
– ለወላጅና ለቤተሰብ
– ለአካባቢና ለጎረቤት
– እግዚአብሔር ለሾማቸው ካህናት
– በዕድሜ ለገፉ አባቶችና እናቶች
እንደ አስፈላጊነቱ መታዘዝ ይገባል፡፡ ሐዋርያት በቅንነት በመታዘዛቸው በሥራቸው ፍሬ አፍርተዋል፡፡ የሐዋ. 10፣33፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ጌታችን ተከተሉኝ ሲላቸው ተከተሉት፡፡ ለሕዝቡ የሚበሉትን ስጡአቸው ሲላቸው ያላቸውን ያለንፍገት በማቅረብ ሰጡ፡፡
ከእግዚአብሔር የመጣውን ትእዛዝ ሳንጠራጠር ሳንሟገት ጠቃሚ መሆኑን አውቀን በጽኑ እምነት ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡
ሰማዕታት በእሳት፣ በስለት፣ በሰንሰለት በጅራፍ፣ በመገረፍ፣ በመስቀል በመሰቀል ይህንና ይህን በመሳሰለው መከራ ተፈትነው በሃይማኖታቸው ጸንተው ፈተናውን ድል አድርገው የተቀበሉትን ቃል ኪዳን ሳይጠራጠሩ መቀበል መታዘዝ ነው፡፡
ለጋስ ማለት ያልቅብኛል ይጎልብኛል ሳይል ሳይሳሳ በንፍገት ሳይሆን በቸርነት የሚሰጥ፤ ዘመድ ወገን ሳይል የሰው ወገን የሆነውን ሁሉ የሚረዳ፤ ለተራበው የሚያበላ፣ ለተጠማው የሚያጠጣ፣ ለተራቆተው የሚያለብስ ደግ ቸር የሆነ ሁሉ ለጋስ ይባላል፡፡
በዘመነ አበው በለጋስነት ከታወቁት አባቶች ታላቁን አብርሃምን ብንመለከት በየዕለቱ እንግዳ ይቀበል ነበር፡፡ በዚህ ግብሩም ታላቅ የበረከት አባት እንደሆነ ተነግሮለታል፡፡ ዘፍ. 12፣2፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም «የወንድማማቾች መዋደድ ይኑር እንግዶችን መቀበል አትርሱ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን በእንግድነት ተቀብለዋል» ዕብ.13፣1-2 በማለት በቸርነት በለጋስነት የተገኘውን ረድኤት በረከት አሳይቷል፡፡
እግዚአብሔር በሀብት በዕውቀት በመግቦት የጎበኛቸው ሁሉ ለጋሶች፣ ሳይነፍጉ ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ታማኝነታቸውን የሚሰጡ እንዲሆኑ ይህ ርእሰ ትምህርት ይናገራል፡፡ የሐዋርያት ለጋስነት ከብዙ ነገር ላይ ተነሥቶ ሳይሆን በትንሹ ላይ በመለገስ ለበረከት መብቃትን ያሳያል፡፡
በዚች ምድር ላይ የተፈጠረ ፍጥረት ሁሉ በተለይም የሰው ልጅ ችግሩ ይለያይ እንጂ ችግር የማይደርስበት የለም፡፡
አንዱ የገንዘብ ችግር ባይኖርበት የጤና ችግር ይኖርበታል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብና ጤንነት ተሟልተውለት በትዳር የሚቸገር፣ ትዳር ተሟልቶለት በልጅ እጦት የሚቸገር ሊኖር ይችላል፡፡ በዚህ በኩል የሚመጣውን ችግር መወጣት ያዳግተዋል፡፡ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከት ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሁሉንም እንደየችግሩ ልንረዳና ልንረዳዳ፣ በችግሩ ልንጋራ፣ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ወደ ሰርግ ቤት ከመሔድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት መሔድ ይሻላል ያለው፤ የተቸገሩትን መርዳት ያዘኑትን ማጽናናት ማረጋጋትን ሲያስረዳን ነው፡፡
የሐዋርያት ጥያቄ የጌታችንም መልስ በችግርና በችግረኞች ላይ የተደረገ ውይይትና መፍትሔም የታየበት ነበር፡፡ የመፍትሔው አካላት ለመሆን ፈቃደኞች እንሁን፡፡
ሐዋርያው «በአሁኑ ዘመን ባለጠጎች የሆኑትን መልካም እንዲያደርጉ በበጎ ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው» 1ጢሞ. 6፣17-19 ይላል፡፡ መርዳት የሚችሉ አካላት በመርዳታቸው የችግር ተካፋዮች መሆናቸውን ማመን ያስፈልጋል፡፡
ከትንሽ እስከ ትልቅ ከአገልጋይ እስከ ተገልጋይ ከመጋቢ እስከ ተመጋቢ ያለው የሥራ ድርሻውን ማወቅ በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ የሥራን ድርሻ ሳያውቁ መንቀሳቀስ ፍምን በእጅ ጨብጦ አልቃጠልም እንደማለት ነው፡፡ ጆሮ የዓይንን እግር የእጅን ሥራ ሊሠራ እንደማይችል ሁሉ የሥራ ድርሻውን የማያውቅ እንዲሁ ነው፡፡
ዳታንና አቤሮን በሊቀ ነቢያት ሙሴና በሊቀ ካህናት አሮን የሥራ ድርሻ ውስጥ በመግባት ክህነታዊ ሥራ እንሠራለን ብለው አደጋ ላይ ወድቀዋል፤ በእሳት ተበልተዋል፤ ምድር ተከፍታ ውጣቸዋለች፡፡
ንጉሡ ግዝያንም በማን አለብኝነት ተነሣሥቶ በሥጋዊ ሥልጣኑ ተመክቶ ክህነታዊ ሥራ እሠራለሁ በማለቱ በለምጽ ተመትቶ ሞቷል፡፡
የሐዋርያት ድርሻ የሕዝቡን ችግር ወደ ፈጣሪያቸው ማቅረብ፣ የታዘዙትን በቅንነት መፈጸም፣ ያላቸውን ይዘው መቅረብ ነበር፡፡ የጌታችን ድርሻ ለሐዋርያት መመሪያ መስጠት፣ የቀረበውን ማበርከት፣ የተቸገረው ሕዝብ ከችግሩ እንዲላቀቅ ሐዋርያት ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ችግር ፈች አሠራር ለባለ ድርሻዎች ሁሉ አርአያነት አለው፡፡
በአጠቃላይ በየትኛውም የሥራና የአገልግሎት ድርሻ ሆነን ሕዝብን እንደምናገለግል በቅድሚያ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ «የሚያስተምር ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር» ሮሜ. 12፣7-8 ተብሎ ተጽፏል፡፡
«ሀብዎሙ ዘይበልዑ፤ የሚበሉትን ስጡአቸው» የተባሉ እነማን ናቸው? ለምን ተባሉ? መመሪያውንስ እንዴት ተወጡት? አሁን ከእኛ ምን ይጠበቃል? እንወያይበት፡፡
የሚመግብ ሆነ የሚመገብ ድርሻውን አውቆ ይሥራ፡፡ እንደተሰጠው ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢውም ተመጋቢውም ራሱን አሳልፎ ለፈጣሪው ይስጥ፡፡ መጋቢም ተመጋቢም የምግባቸው ዐውደ ማዕድ፤ ሲሳዮሙ ለቅዱሳን፤ የተባለ እግዚአብሔር መሆኑን አምኖ መቀበል ብስለት ነው፡፡
የምንመገበውንና የሚመግቡንን ያዘዘልንና የሰጠን እግዚአብሔር ይመስገን አሜን፡፡