‹‹ጸሎታችሁ እንዳትሰናከል ሚስቶቻችሁን አክብሩ›› (ጴጥ.፫፥፯)

ዲያቆን መልአኩ ይፍሩ

ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ቀዳሜ ፍጥረት አዳምን እና እናታችን ሔዋንን ከፈጠራቸው በኋላ ሕግ እንዳያፈርሱ አንዲት ትእዛዝ ብቻ እንዲያከብሩ ሰጥቷቸው የመጀመሪያውን አንድነት አድሎ በልዩ ቦታ በኤደን ገነት አኖራቸው። በኋላ ግን ሕግን ሲያፈርሱ ከዚያች ቅድስት ቦታ አስወጣቸው፤ አባታችን አዳም በእናታችን ሔዋንን ‹‹እንግዲህ ከገነት ያስወጣሽኝ አንቺ ነሽ›› ብሎ ተቆጥቷት ነበር። በዚህ ምክንያት ደንግጣ ከእርሱ ሸሽታ ስትሄድ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ አዳም መጥቶ፥ ‹‹ሔዋንን ሂድና አምጣት›› አለው። እርሱም መልሶ ‹‹በእርሷ ምክንያት ከገነት ወጥቼ ከአምላኬ ተጣልቼ ለምን ላምጣት›› ቢለው መልአኩ በመመለስ ‹‹በእርሷ ምክንያት ከገነት ብትወጣ ዳግመኛ ወደ ቦታህ የምትመለሰው በእርሷው እንደሆነ አታውቅምን?›› ብሎ አረጋጋውና ሂዶ እንዲታረቃት አደረገው። ከዚያም ጊዜ አንሥቶ በእርሷ ምክንያት ወደ ገነት እንደሚመለስ እንደሚድንም ሲያውቅ ቅድስት ሔዋንን ሕይወቴ እያለ ይጠራት ነበር። (መጽሐፈ አክሲማሮስ ዘዐርብ)

በትዳር ሕይወት ስንኖር ባል ራስ ነውና ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙና እንዲታዘዙ ሲያዛቸው፣ ለባሎች የሰጠው ትእዛዝ ደግሞ ከዚህ የጸና ትእዛዝ ነው። ይኸውም የገዛ ሕይወቱን አሳልፎ እስኪሰጥላት ድረስ ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንደወደዳት ባልም እንዲሁ ሚስቱን እንዲወዳት ጽኑዕ ትእዛዝን አዟል። ታዲያ ከመታዘዝና ከመገዛት ይልቅ ምን ያህል የሚጸና እንደሆነ ልናስተውለው ይገባል።

ትዳርን አግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠበት መሠረታዊው ዓላማ ጽድቅ እስከሆነ ድረስ ባል እና ሚስት አንዱ አንዱን ይዞ ለመጽደቅ መቻቻል ይኖርባቸዋል። በዚህ ርእሰ ጉዳይ የምናነሣው ግን ባሎችን ስለሆነ ባሎች ሚስቶቻቸውን ማክበር ይገባቸዋል። ማክበር የምንለው ከፍቅር ጋር የማይነጠል ጥብቅ ትእዛዝ ነው። በትርጓሜ መጻሕፍቶቻችን እና በቅዱሳን ታሪክም እንደሚነገረን ባልና ሚስት ሲከባበሩ ትዳሩ እግዚአብሔር የሚያድርበትና ቅዱስ ፍሬ የሚገኝበት፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚመራ ቤት ይሆናል።

በትዳር ውስጥ ምንም ዓይነት አለመግባባት ቢኖር ፈጥነው አለመግባባቱን መፍታት ይገባል። ምክንያቱም በመጽሐፍ እንደሚነገረን ሰው በልቡ ቂም እና ጠብን ይዞ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ከሆነ የጸሎቱ መዓዛ የተወደደ አይሆንለትም። የዚሁ የቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት ትርጓሜ እንደሚነግረንም ባልና ሚስት በጠብ ጸንተው የሚኖሩ ከሆነ በዚያ ምክንያት አንድ ጊዜ ከዳኛ አንድ ጊዜ ከሽማግሌ እያሉ ከእግዚአብሔር ሊገናኙ የሚገባበትን ውድ ጊዜያቸውን በከንቱ ያጠፋሉ። እንዲሁ ከእግዚአብሔር የሚገናኙባት ጸሎታቸውም ትታጎልባቸዋለች።

በመጽሐፍም ደግሞ ‹‹ጸሎቱ ለመስተቀይም ከመ ዘርዕ ዘወድቀ ማዕከለ አስዋክ፥ የቂመኛ ሰው ጸሎት በእሾህ መኻከል እንደወደቀ ዘርዕ ነው›› ይላል። ይኸውም ማለት አንድ ዘርዕ በእሾህ መኻከል ቢወድቅ በሚገ’ባ እንዳያድግ እሾሁ አንቆ እንደሚይዘው እንዲሁ ሁሉ በጠብ በክርክር የሚደረግም ጸሎት ቂም በቀሉ ጸሎቱ ወደ ላይ የሚያርግበትን ኃይል ነሥቶ አንቆ ከዚሁ ያስቀረዋል። ለዚያም ነው በሥርዓተ ቅዳሴያችን ዲያቆኑ በሥርዓተ ቅዳሴ ከበእንተ ቅድሳት በፊት ‹‹ይህ የአባቶቻችን የቅዱሳን ሐዋርያት ትእዛዝ ነው፤ ሰው በልቡናው ቂም እና በቀልን ቅንዓትና ጠብን በባልንጀራው ላይ ማንምን በማን ላይ ቢሆን አይያዝ›› የሚለው። በኋላ በእንተ ቅድሳት ብሎ የሚጸልይ ነውና ያን ስለብዙዎች የሚቀርበውን ምልጃ በእግዚአብሔር ፊት ውኩፍ እንዲሆን ሲባል ሰው ቂም ቅናት ምቀኝነት ጠብ የያዘውን ይህን ሁሉ እንዲጥል በአዋጅ ያዝዛል። (፩ጴጥሮስ መልእክት አንድምታ ትርጓሜ ፫፥፯)

ከጠብና ቅናት ባሻገር ሚስትን ማክበር ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተነገረን ሴት የተፈጠረችው ከወንድ ጎን ነው። ከጎኑ ብትፈጠርም እንኳን ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዚሁ የመልእክት ክፍሉ እንደሚያስረዳን ሴቶች ለባሎቻቸው ይገዙ ቢባልም እንኳ መንግሥተ እግዚአብሔርን በመውረስ ግን ከወንድ ያነሰ ዕድል ስላልሆነ መከበር ያለበት መሆኑ ነው። እንዲያውም የዚሁ መልእክት ትርጓሜ እንደሚነግረን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲናገር በሚደረግ የትሕርምት ተጋድሎ ሴቶች የሚበልጡበት ብዙ ጊዜ እንዳለ ነው። እንኪያስ ሚስቱን የሚያከብር ባል በሚስቱ ምክንያት ከእግዚአብሔር በጎ ዋጋን እንደሚያገኝ ያስተምረናል።

በአጠቃላይም ጸሎታችሁ እንዳይሰናከል ሚስቶቻችሁን አክብሩ ማለቱ በዋናነት ሚስት ትታዘዝ ስለተባለ መና’ቅ አለባት ማለት እንዳይደለ ማስተዋል ይገባል። ይልቁንስ ይውደዳት ተብሏልና እርሷን ለማስደሰትና በእርሷም እግዚአብሔርን ለማስደሰት መድከምና መትጋት እንደሚገባ ማስተዋል ይገባል። እግዚአብሔርም በፍጥረት ሥርዓት ሲፈጥራት ከራስ አጥንት ወይም ከጋርን አጥንት ያልፈጠራት፣ ከመኻከል ጎኑ የፈጠረበት ምክንያት እንዳትናቅም፣ እንዳትኩራራም፣ በትክክል ቦታዋን ይዛ አግዚአብሔርን ስታመሰግን እንድትኖር ነው።