ጥንተ ሆሣዕና

መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የዓለም መድኃኒት አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንባባና ልብስ ተነጥፎለት በአህያ ውርንጭላዋ ተጭኖ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት ‹‹ጥንተ ሆሣዕና›› በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይዘከራል፡፡ ሆሣዕና ማለት ‹‹አሁን አድን›› ማለት ነው፤ (ማሕቶተ ዘመን ገጽ ፻፷)

አስቀድሞ በቅዱስ መጽሐፍ በነቢዩ ዘካርያስ ‹‹ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሏት›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። (ዘካ.፱፥፱)

ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው ጌታችን ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረበ ጊዜ ሕዝቡ ተናወጠ። ሰዎች ሁሉ እርሱ በሚያልፍበት መንገድ ልብሳቸውን፣ የዘንባባ፣ የወይራና የዛፍ ቅርንጫፎች በማንጠፍ ለክብር ጌታ ምስጋናን፣ ውዳሴን አቀረቡለት። በመቅደስም ሳለ ሕፃናቱ ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም!›› እያሉ በታላቅ ድምጽ እየጮኹ አመሰገኑት። ‹‹ሆሣዕና … ሆሣዕና… ሆሣዕና በአርያም! በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ብሩክ ነው!›› እያሉ በአናታቸው ጀርባና እቅፍ ያሉ ሕፃናትና የቢታንያ ድንጋዮች ሁሉ ሳይቀሩ በታላቅ ደስታና ሐሴት ሆነው መድኃኒት፣ አዳኝና ቤዛ ለሆነው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ድምፅ በንጹሕ አንደበት ዘመሩለት፤ አመሰገኑት። ምድርምና ሞላዋ፣ ውቅያኖሶች፣ ባሕሮችና ተራሮች፣ ሰማይ፣ ሰማየ ሰማያት፣ ከሰማይም በላይ ያለ ሰማይ፣ የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ በዚህ ልዩ የሕፃናት የምስጋና ጥዑም ዜማ ተሞሉ፣ በደስታም እንደ እንቦሳ ዘለሉ።

በዚህ ልዩ ሰማያዊ ቅኔ የሰማይ ሠራዊት፡- መላእክት፣ ሊቃናት፣ አጋእዝትና መናብርት ሁሉ በአንድነት በሐሴትና በደስታ ታደሙ። በዚህ ታላቅ የምስጋና፣ የፍቅር ዜማ ምድርም በሐሴትና በደስታ ተናወጠች። የፍቅር አምላክ፣ የሰማይና የምድር ሁሉ ፈጣሪ ዝቅ ብሎ፣ የዋህና ትሑትም ሆኖ በአህያ ውርንጫ ላይ ሆኖ መጥቷልና።

ሆሣዕና ጌታችን ከዚህ ቀን በኋላ ለሚያደርገው ገቢረ ተአምራት እና የሚቀበለው መከራ የሞት ጽዋ በመሆኑ ይህ ምስጋና የጌታንን የሞት ዕለት መቅረብ የሚያበስር ዐዋጅ ነበር፡፡ በዕለተ ሆሣዕና ሕፃናት፣ የተከተሉት ሕዝቡ ሁሉ በደስታ ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሕዝበ እስራኤል በበደልና ኃጢአት ለኢየሩሳሌም ከተማ የመጥፋትና የመፍረስ ምክንያት እንደሚሆን ዐውቆና ጊዜውንም አሻግሮ አይቶ አለቀሰላት፤ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ብታውቂ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሠውሯል፡፡›› (ሉቃ.፲፱፥፵፪)

ስለዚህም በዚህ ቀን አምላካችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዋህና ትሑት በመሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን እንዳሳየ እንዲሁም ሰላምን እንዳበሠረ ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ ለሰው ልጆች ሰላምን የምንሻና ፍቅርን በተግባር የምንገልጽበት መልካም የምስጋናና የውዳሴ ዕለት ነው፡፡

ሆሣዕና በአርያም!!!