‹‹ጠፈር ይሁን፤ ውኃም ከውኃ ይለይ›› (ዘፍ.፩፥፮)

መምህር ቢትወደድ ወርቁ

ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

እግዚአብሔር በዕለተ ሰኑይ በቀዳሚት ሰዓት ሌሊት ‹‹ጠፈር ይሁን፤ ውኃም ከውኃ ይለይ›› ብሎ ቢያዘው ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ ሞልቶ የነበረውን ውኃ ከአራት ከፍሎ አንድን እጅ በመካከል ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ዘረጋው፡፡ (ዘፍ.፩፥፮) እንደ ቤተ መንግሥት አዳራሽ ወደ ላይ ጠበብ አድርጎ እንደ ብረት አጸናው፤ ይህ የምናየው ሰማይ ነው፤ ጠፈር ይባላል፡፡ ጠፈር ማለትም ሥዕለ ማይ (የውኃ ሥዕል) ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠፈርን መፍጠሩ ስለምንድነው? ቢሉ ረቡዕ የሚፈጥረውን ፀሐይን ሊያቀዘቅዝ ሰውም ይህን እያየ ሰማያዊ ርስት እንዳለው እንዲያውቅ ነው፡፡ እጅግም ነጭ ከሆነ ዓይን እየበዘበዘ እያንጸባረቀ ለሰው የደዌ ምክንያት ይሆን ነበርና፡፡ በድስት ያለ ውኃ በሚታጠብ ጊዜ የእሳት ማቃጠል ሲበዛበት እንደሚሰበር ጠፈርም የፀሐይ ማቃጠል ሲበዛበት እንደ ሸክላው በፈረሰ ነበርና እንዲያጸናው ሐኖስን በላይ አደረገለት፡፡ (መጸሐፈ ሥነ ፍጥረት ገጽ ፳-፳፫)

እግዚአብሔር ምድርን ከውኃ እንዴት ለያት? የሚለውን ሐሳብ ሊቃውንቱ ሲተረጉሙ ‹‹ዛሬ አይብ ከአጓት ተለይቶ እንደሚረጋ ውኃውን በውስጥ እንደ አጓት እያደር ተራራ፣ ኮረብታና ድንጋይ የምታስገኝ እስክትሆን ድረስ ምድርን አግዝፎና አወፍሮ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ በውኃ ላይ እንደ መርከብ ዘርግቶ አጸናት፤ ውኃንም ከእሳትና ከአየር አራርቆ አሰፈራት፡፡ የውኃን ቅጥር ከእሳት ቅጥር፣ የእሳትን ቅጥር ከነፋስ ቅጥር፣ የነፋስን ቅጥር ከበርባሮስ ቅጥር እርሱ ባወቀው ማኅተም አትሞ ገጥሞታል፡፡ የውኃና የምድር እምብርት ጉልላት ቀራንዮ ናት፡፡ በዚህች በቀራንዮ ቀድሞ አዳም ተፈጥሮባታል፤ በኋላም ጌታ መስቀሉን ተክሎ ድኅነተ ዓለምን ፈጽሞባታል፡፡ ምድርን ዙሪያዋን ከሰባት ከፍሎ የወዲያኛው አንድ እጅ ወዲያና ወዲህ ከንፈሩን ቀፍፎ መካከሉን አጎድጉዶ የወዲያውን አድማስ የወዲሁን ናጌብ አለው፡፡ ዙሪያውንም ተጠምጥሞ ቆሞ የነበረውን ውኃ በአድማስና በናጌብ መካከል አሰፈረው፤ ስሙንም ውቅያኖስ አለው፡፡ ውኃውን ከአራት ከፍሎ አንዱን ሐኖስ፣ አንዱን ጠፈር፣ አንዱን ውቅያኖስ አንዱን ለምድር ምንጣፍ አደረገው›› በማለት ያብራራሉ፡፡ (መጸሐፈ ሥነ ፍጥረት ገጽ ፳-፳፫)

ምድርን በውኃ ላይ አጸናት፤ ድኅነትም በውኃ በመጠመቅ ተፈጸመ

እግዚአብሔር ‹‹ምድርን በውኃ ላይ አጸናት›› ተብሎ በመጽሐፍ እንደተጻፈ ምድር እንኳን የጸናችው በውኃ ላይ ነው፡፡ (መዝ.፻፴፭፥፮) ከሰባ እስከ ሰባ አምስት ከመቶ የሚሆነው የምድራችን መዋቅርም ውኃ ነው፡፡ በምድር ካለ ፍጥረት ያለ ውኃ መኖር የሚችል ምንም ፍጥረት የለም፡፡ ‹‹ውኃ ሕይወት ነው!›› የሚያሰኘውም ይኽው እውነት ነው፡፡ ውኃ የተፈጠረው ለምሕረትና ለሰው ልጆች ሕይወት ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ከሰውነት ወጥቶ እግዚአብሔርን ባሳዘነው ጊዜ በውኃ ተቀጥቷል፡፡ ለዚህም በኖኅ ዘመን የተፈጸመውን ታሪክ አውስቶ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞችም ዓለም ላይ የጥፋት ውኃ ካወረደ›› በማለት አስተምሯል፡፡ (፪ጴጥ.፪፥፭) ይሁን እንጂ ሰው በኖኅ ዘመን የሆነውን እያሰበ ውኃ የተፈጠረው ‹‹ለመቅጫ›› ነው ወደሚል ድምዳሜ እንዳይደርስ በኋላ ዘመንም ማዳኑን የፈጸመለት በውኃ አማካኝነት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን አስመልክቶ ባስተማረበት የመጽሐፍ ክፍል ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል›› በማለት አስተምሮዋል፡፡ (፩ጴጥ.፫፥፳)

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም ይህን የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል ይዘው ‹‹አጥመቃ ለምድር እግዚአብሔር በማየ አይህ፤ እግዚአብሔር ምድርን በጥፋት ውኃ አጠመቃት››  በማለት ያስተምራሉ፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ ምዕራፍ ሦስት) ከቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት ውኃ የሥጋ ብቻ ሳይሆን የነፍስም ድኅነት መሠረት መሆኑን እንረዳለን፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን ስለምን በውኃ አደረገው? ለሚለው ጥያቄ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አያሌ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው ኃጢአታችንን በውኃ እንደሚያስወግድልን ትንቢት ስላናገረ ነው፡፡ ‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኩሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ›› እንዳለ፡፡ (ሕዝ.፴፮፥፳፭) ከሌላኛዋ የውኃ ክፍል ከባሕርና በባሕር ውስጥ ከተፈጠሩ ፍጥረታት ጋር በተያያዘም እግዚአብሔር ‹‹ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቃሳቃሾች ታስገኝ፤ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ፡፡ እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፥ ውኃ ያስገኘውን ተንቀሳቃሽ ሕያው ፍጥረትን ሁሉ በየወገኑ የሚበሩትንም አዕዋፍንም ሁሉ ፈጠረ›› ብሎ በተናገረ ጊዜ በልብ የሚሳቡ፣ በእግር የሚሽከረከሩ፣ በክንፍ የሚበሩ፣ በደመ ነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል፡፡ (ዘፍ.፩፥፳) ከውኃው (ከባሕሩ) በረው በረው የሄዱ አሉ፤ እዚያው የቀሩም አሉ፡፡ በረው የሄዱት የኢጥሙቃን ከዚያው የቀሩት ደግሞ የጥሙቃን ምሳሌዎች ናቸው፡፡

ጥምቀትን በውኃ ያደረገበት ምሥጢርንም ሊቃውንቱ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፤ ‹‹ውኃ በዙፋን ካለ ንጉሥ በዐደባባይ እስካለ ማናቸውም ሰው ለሁሉ ይገኛል፤ ጥምቀትም መሠራቱ ለሁሉ ነውና፡፡ ውኃ ከጽንፍ እስከ ከጽንፍ ይፈሳል፤ ጥምቀትም ከጽንፍ እስከ ከጽንፍ ላመነ ሁሉ ይደረጋል፡፡ ውኃ ከቆሻሻ ከጉድፍ ያነጻል፤ ጥምቀትም ከኃጢአት ያነጻል፡፡ ውኃ ለወሰደው ፍለጋ የለውም፤ (ውኃ የወሰደው አይገኝም፤ ቢገኝም አስከሬኑ ነው) በጥምቀትም የተሠረየ ኃጢአት በምንም በምን አይመረመርም፡፡ ውኃ መልክን እንደ መስታወት ያሳያል፤ ጥምቀትም መልክአ ነፍስን ያሳያልና፡፡ ውኃ ፍጥረትን ያለመልማል፤ ጥምቀትም ልምላሜ ነፍስን ያሰጣልና፡፡ በውኃ የተነከረ ልብስ ግዝፈት ይነሣል፤ ምእመናንም ተጠምቀው ገድል ትሩፋት እየጨመሩ ይሄዳሉና፡፡››

በብሉይ ኪዳን መልካም ፍሬን ያፈሩ መተጫጨቶች በውኃ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ርብቃ ለይስሐቅ፣ ሲፓራ ለሙሴ፣ ራሔልም ለያዕቆብ የታጩት በውኃ አማካኝነት ነው፡፡ (ዘፍ. ፳፬፥፲፫፣፲፫፣፳፱፥፩፣ዘፀ.፪፥፲፱) ክርስቶስ ሙሽራ በጥምቀት የወለዳት ቤተ ክርስቲያንም ሙሽሪት ናትና ይህን መንፈሳዊ መተጫጨት በውኃ አደረገው፡፡ ሸክላ ሠሪ ሠርታ ስትጨርስ ከነቃባት (ከተሰነጠቀባት) እንደገና ከስክሳ በውኃ ለውሳ ታድሰዋለች፤ (ትርጓሜ ወንጌል ገጽ ፸) መጽሐፍ ‹‹በልባችሁ መታደስ ተለወጡ›› በማለት እንደተናገረም የልቡና መታደስ የሚገኘው በጥምቀት በተገኘ ጸጋ ነውና፡፡ (ሮሜ ፲፪፥፪) ጌታችን በወንጌል ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም›› በማለት ማስተማሩም በውኃ ያገኘነው ጥምቀት የድኅነታችን መሠረት መሆኑን እንድናስተውል ያደርገናል፡፡ (ዮሐ.፫፥፭)

‹‹የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰደው›› (ራእ.፳፪፡፥፲፯)   

የውኃን ነገር ስናነሣ ሌላው ልናስታውሰው የሚገባው ጉዳይ በመጽሐፍ ‹‹የሕይወት ውኃ›› የተባለውን ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው ውኃ ካላገኘ ሊኖር እንደማይቻለው ሁሉ ቃለ እግዚአብሔርንም ካልተማረ በነፍሱም ሆነ በሥጋው ትርጉም ያለው ኑሮ ይኖር ዘንድ አይቻለውም፡፡ ሰው ምድራዊውን ውኃ ቢያጣ በሥጋው ብቻ ይጎዳል፤ የሕይወት ውኃ ቃለ እግዚአብሔርን ቢያጣ ግን በሥጋውም በነፍሱም ጥፋት ያገኘዋል፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጥሞ ደሴት ለተገለጠለት ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹የተጠማም ይምጣ፤ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰደው›› በማለት ቃለ እግዚአብሔርን ያለምንም ዋጋ እንዲያው በጸጋው እንድንማር ጋብዞናል፡፡ (ራእ.፳፪፡፥፲፯) ምድራዊውን ውኃ ለመቅዳት ወደ ወደ ጉድጓድ ወርዳ የነበረችው ሳምራዊትዋ ሴት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹በእውኑ አንተ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል›› ባለችው ጊዜ ጌታችን ‹‹ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ” አላት፡፡ (ዮሐ. ፬፡፥፲፬)

እግዚአብሔር ለሥጋችን ጥማት የሚያረካንን ውኃ እንደሰጠን ሁሉ የነፍሳችንንም ጥማት የሚያረካና ነፍሳችንን ወደ ዘለዓለማዊነት የሚያሻገግራትን የሕይወት ውኃ ሰጥቶናል፡፡ ያም የሕይወት ውኃ ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ አንደበት ‹‹እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፤ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ፤ ብሉም፤ ኑ! ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ›› በማለት በፍቅር ቃል ጋብዞናል፡፡ (ኢሳ.፶፭፥፩) የእግዚአብሔር ቃል ነውና እውነት ነው፡፡ እስካሁን ከፈቃዱ ርቀን ቅዱስ ቃሉን ከመስማት ጆሮአችንን የመለስን ማናችንም ብንሆን እንደደረቅንና እንደጠወለግን ልናውቅ ይገባናል፡፡

‹‹ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ ዋጋው አይጠፋበትም›› (ማቴ.፲፥፵-፵፪)

አምላካችን እግዚአብሔር ‹‹ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም›› በማለት በዚህም መንገድ መንግሥተ ሰማይን መውረሻ አድርጎታል፡፡ (ማቴ.፲፥፵-፵፪) እንደ ፈቃዱ የተመላለሱትን እርሱን ያስደሰቱትን ወዳጆቹን በማሰብ በስማቸው ቀዝቃዛ ውኃን ለሌሎች የሚያጠጣ ዋጋው በሰማያት እንደማይጠፋበት ጌታችን በእውነት አስተማረን፡፡  እግዚአብሔር ያለ ምክንያት የፈጠረው አንድም ፍጥረት የለም፡፡ ኃጢአት በበዛበት፣ ስስት በነገሠበት፣ ክሕደትና ጥርጥር በገነነበት ዓለም ነውና የምንኖረው እግዚአብሔርን ከሚያሳዝን ነፍስንም ሥጋንም ከሚጎዳ ተግባር ለመራቅ ልቡና መሻቱ ካለን ውኃን ባሰብን ቁጥር እግዚአብሔርንና በውኃ አማካኝነት ለእኛ ያደረገውን ነገር በማሰብ ወደ እርሱ ፊታችንን ማዞር እንችላለን፡፡

ይቆየን!