ግዝረተ ክርስቶስ

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱና የመጀመሪው ሲሆን ይህም ግዝረተ ክርስቶስ ይባላል። በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው “ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ግዘረት ቤት ወሰደችው፤ ገራዡ ምላጩን ይዞ ቀረበ፤ ነገር ግን ምላጩ እጁ ላይ ሳላ ውኃ ሆኖ ፈሰሰ። ጌታችንም በተአምራት የተገረዘ ሆኖ ተገኘ፡፡” (ሉቃ.፩፥፳፩)

ጌታችን ደሙ የሚፈሰው ሥጋውም የሚቆረሰው አንዴ በዕለተ ዓርብ ብቻ ስለሆነ ይህ ሆኗል። ጌታችን የሰውን ሥርዓት ሁሉ ጠብቋል። እራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።” (ማቴ.፭፥፲፯) “አምላክ ነኝና ዕለቱን ተፀንሼ ዕለቱን ልወለድ” አላለም። ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ቆይቶ ተወለደ እንጂ፤ እንደ ሕፃናትም አለቀሰ፤ ደግሞም በጥር ፮ ተገረዘ።

አምላካችን ከበዓሉ ረድኤት ያሳትፈን፤ አሜን!