ግብጻዊቷ ቅድስት ሣራ

መጋቢት ፲፬፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ባለጸጋ ከሆኑ ግብጻዊ ወላጆቿ የተወለደቸው ቅድስት ሣራ በምንኩንስና ሕይወት የኖረች ተጋዳይ እንደነበረች ገድሏ ይናገራል፡፡ የመጋቢት ፲፭ (ዐሥራ አምስት) ቀን መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚገልጸው ከልጅነት ጀምሮ በምንኩስና ሕይወት ቅንዓት ኖራለች፡፡ ወላጆቿ ክርስቲያናች ስለነበሩና ቅዱሳት መጽሐፍትን ማንበብና መጻፍ ስላስተማሯት በተለይም የመነኰሳትን ገድል ማንበብ ታዘወትር ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ከላይኛው ግብጽ ወደ ሚገኝ ገዳም በመሄድ ለረጅም ዓመታት ደናግልን ስታገለግል ኖሯለች፡፡

ከዚህም በኋላ የምንኩስናን ልብስ በመልበስ ጠላት ዲያብሎስን ለ፲፫ (ዐሥራ ሦስት) ዓመታት ተዋግታዋለች፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀንም በኩራታና በትዕቢት ሊጥላት ወደ እርሷ ቀረበና እንዲህ አላት፤ “ሣራ ሆይ ሰይጣንን ድል አድርገሽዋልና ደስ ይበልሽ፤” ቅድስት ሣራ ግን በሐሰተኛው ጠላት ሳትታለልና ሳትሸነፍ እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “እኔ ደካማ ነኝ፤ ከክብር ባለቤት ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ድል አድርጌ ላባረው አልችልም፤” ስለዚህም ሰይጣን ከአጠገባ በኖ ጠፋ፡፡

ግብጻዊቷ መነኩሴ በገዳማዊ ሕይወት አብረዋት ሲያገልግሉ ለነበሩ ደናግል እንዲህ እያለች ታስተምራቸውና ትመክራቸው ነበር፡፡ “ከቀን ብዛት ጠላት እንዳያስተኝ እኔ እንደምሞት አስቀድሜ ሳላስብ እግሬን ከአንዱ መወጣጫ ደረጃ ወደ ሁለተኛዋ አውጥቼ አላኖራትም፡፡ ዳግመኛም ለሰው ርኅራኄ ማድረግ በተሻለው ነበር፤ ይህንንም በሚያደርግ ጊዜ የኋላ ኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ ይኖራል፡፡”

ቅድስት ሣራ በዜና አረጋውያን መነኮሳት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፉ ሌሎች ብዙ ቃሎችንም ተናግራለች፡፡ ለ ፷ (ስድሳ) ዓመታትም በባሕሩ ዳርቻ በሚገኘው ዋሻ ውስጥ ጽኑ ተጋድሎን ስትጋደል ኖረች፤ ማንም ግን ያያት አልነበረም፡፡ ፹ (ሰማንያ) ዓመት በሆናት ጊዜም በመጋቢት  ፲፭ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፋለች፡፡

በረከቷ ይደርብን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መጋቢት