ግስ

…ካለፈው የቀጠለ

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ሀ. የግስ አርእስት

የግስ አርስቶች አልፎ አልፎ በአንዳንድ ጉባኤ ቤቶች በተወሰነ መንገድ ልዩነት አላቸው። ልዩነታቸው ግን የቁጥር ሳይሆን ግሶችን የመለዋወጥ ሁኔታ ነው። በቁጥር ሁሉም ስምንት ያደርጓቸዋል። ይሁን እንጂ በዚህ ጽሑፍ አብዛኛዎቹ የሚከተሉትን እናቀርባለን። ለማሳያ ያህል ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው መጽሐፈ ግስ ወሰዋስው መርኆ መጻሕፍት በተባለ መጽሐፋቸው የግስ አርስቶች የምንላቸው ስምንት ናቸው ። እነርሱም ቀተለ፣ ቀደሰ፣ ተንበለ፣ ባረከ፣ ማኅረከ፣ ሴሰየ፣ ክህለ፣ ጦመረ ናቸው በማለት ይገልጹአቸዋል። (ያሬድ፣ገጽ ፬፻፳፭)

አልፎ አልፎ ለየት ያለ አጠቃቀም ያላቸውን ለማሳየት ያህል ገብረ፣ ዔለ እና ዖደ የግስ አርእስት የሚያደርጓቸው አሉ። ይሁን እንነጂ በእነዚህና ከላይ በተመለከትነው መካከል እጅግ የጎላ ልዩነት አለ አያስብልም። ምክንያቱም ገብረ በማኅረከ፣ ዔለ በሴሰየ፣ ዖደ፣ በጦመረ ቤት የሚረቡ ናቸው። በእርግጥ የተወሰነም ቢሆን ልዩነት የላቸውም ማለት ግን አይደለም። ምክንያቱም ገብረ ባለ ሦስት ፊደል ሲሆን ማኅረከ ግን ባለ አራት ፊደል ነው። ሴሰየ ባለ ሦስት ፊደል ሲሆን ኤለ ባለ ሁለት ፊደል ነው። ዖደም ባለ ሁለት ፊደል ሲሆን ጦመረ ግን ባለ ሦስት ፊደል ነው። ይህ እንዴት ይታረቃል ለሚል ሰው እንደኪዳነ ወልድ አረባብ ዖደ እና ኤለ አሁን ባሉበት ቅርጽ አይደለም የሚረቡት። በእርግጥ በእርባታ ጊዜ በሌሎችም ጉባኤ ቤቶች እንዲሁ የሚረቡት የጎረዱት ፊደል እንዳለ ተደርጎ በእርባታ ጊዜ ድምጹ ይወጣል። ለምሳሌ ዖደ የዐውድ ብሎ በቀዳማይ አንቀጹ የተዋጠው ወ በካላይ አንቀጹ ላይ ይወጣል። እንደነዚህ ዓይነቶችን ግሶች መምህር እንባቆም እርጉዝ ግሶች ብለው ገልጸዋቸዋል።

መምህር አስበ ድንግል ደግሞ በአከፋፈል ደረጃ ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ጋር የሚስማሙ ሲሆን ጠባያቸውንና ቅርጻቸውን ልንረዳውና አንዱን ከሌላው ልንለይበት በምንችል መንገድ እንደሚከተለው ያስረዱናል።
ተ.ቁ ግስ ትርጉም ቅርጽ የአነባበብ ስልት የፊደል ቁጥር
፩ ቀተለ ገደለ ሙሉ ግእዝ ላልቶ የሚነበብ ፫
፪ ቀደሰ አመሰገነ ሙሉ ግእዝ ጠብቆ የሚነበብ ፫
፫ ተንበለ ለመነ ፪ኛ ድምፅ ሳድስ ሌላው ግእዝ ላልቶ ሚነበብ ፬
፬ ባረከ ባረከ ፩ኛድምፅ ራብዕ ሌላው ግእዝ ላልቶ ሚነበብ ፫
፭ ማኅረከ ማረከ ፩ኛ ድምፅ ራብዕ፣፪ኛ ድምፅ ሳድስ፣ሌላው ግእዝ ላልቶ ሚነበብ ፬
፮ ሴሰየ መገበ ፩ኛድምፅ ኃምስ ሌላው ግእዝ ላልቶ ሚነበብ ፫
፯ ክህለ ቻለ ፩ኛና ፪ኛ ሳድስ የመጨረሻው ግእዝ ላልቶ ሚነበብ ፫
፰ ጦመረ ጻፈ ፩ኛድምፅ ሳብዕ ሌላው ግእዝ ላልቶ ሚነበብ ፫
ምንጭ አስበ ድንግል (ገጽ፴፯)
እነዚህ የግስ አርእስቶች ከላይ እንደተመለከትነው የሌላውን የግስ አረባብ የሚያመለክቱ ናቸው። በእነዚህ የግስ አርእስት የሚመደበው ግስ ሁሉ የእነርሱን የአረባብ ጠባይ እየተከተለ ይሄዳል።
ለምሳሌ፡- የአርስቶችን አረባብ ብቻ እንመልከት፡-
ቀዳማይ ትርጉም ካልዓይ ትርጉም ሣልሳይ ትርጉም ራብዓይ ትርጉም
ቀተለ ገደለ ይቀትል ይገድላል ይቅትል ይገል ዘንድ ይቅትል ይግደል
ቀደሰ አመሰገነ ይቄድስ ያመሰግናል ይቀድስ ያመሰግን ዘንድ ይቀድስ ያመስግን
ተንበለ ለመነ ይተነብል ይለምናል ይተንብል ይለምን ዘንድ ይተንብል ይለምን
ባረከ ባረከ ይባርክ ይባርካል ይባርክ ይባርክ ዘንድ ይባርክ ይባርክ
ማኅረከ ማረከ ይማኀርክ ይማርካል ይማኅርክ ይማርክ ዘንድ ይማኅርክ ይማርክ
ሴሰየ መገበ ይሴሲ ይመግባል ይሴሲ ይመግብ ዘንድ ይሴሲ ይመግብ
ክህለ ቻለ ይክህል ይችላል ይክህል ይችል ዘንድ ይክሀል ይቻል
ጦመረ ጻፈ ይጦምር ይጽፋል ይጦምር ይጽፍ ዘንድ ይጦምር ይጻፍ
አርእስቶቹ በዚህ መንገድ ሲረቡ በእነርሱ ቤት የሚረባው ግስም የእነርሱን የአረባብ ስልት ተከትሎ ይረባል ማለት ነው። ለምሳሌ፡- በቀደሰ፣ በቀተለና ሴሰየ የሚረቡ ግሶችን እንመልከት
ቀዳማይ ካልዓይ ሣልሳይ ብዓይ
ቀደሰ ይቄድስ ይቀድስ ይቀድስ
ወደሰ ይዌድስ ይወድስ ይወድስ
ቀተለ ይቀትል ይቅትል ይቅትል
ቀጸበ ይቀጽብ ይቅጽብ ይቅጽብ
ሴሰየ ይሴሲ ይሴሲ ይሴሲ
ሌለየ ይሌሊ ይሌሊ ይሌሊ

እነዚህ የግስ አርእስቶች በዐሥሩም መራሕያን ይረባሉ።
በዝርዝር በሚቀጥለው የምንመለስበት ሁኖ ግን በቀዳማይ አንቀጻቸው ብቻ የሚኖራቸውን አረባብ እንመልከት

ውእቱ አንተ ውእቶሙ አንትሙ ይእቲ አንቲ ውእቶን አንትን አነ ንሕነ
ቀተለ ቀተልከ ቀተሉ ቀተልክሙ ቀተለት ቀተልኪ ቀተላ ቀተልክን ቀተልኩ ቀተልነ
ቀደሰ ቀደስከ ቀደሱ ቀደስክሙ ቀደሰት ቀደስኪ ቀደሳ ቀደስክን ቀደስኩ ቀደስነ
ተንበለ ተንበልከ ተንበሉ ተንበልክሙ ተንበለት ተንበልኪ ተንበላ ተንበልክን ተንበልኩ ተንበልነ
ባረከ ባረከ ባረኩ ባረክሙ ባረከት ባረኪ ባረካ ባረክን ባረኩ ባረክነ
ማኅረከ ማኅረከ ማኅረኩ ማኅረክሙ ማኅረከት ማኅረኪ ማኅረካ ማኅረክን ማኅረኩ ማኅረክነ
ሴሰየ ሴሰይከ ሴሰዩ ሴሰይክሙ ሴሰሰየት ሴሰይኪ ሴሰያ ሴሰይክን ሴሰይኩ ሴሰይነ
ክህለ ክህልከ ክህሉ ክህልክሙ ክህለት ክህልኪ ክህላ ክህልክን ክህልኩ ክህልነ
ጦመረ ጦመርከ ጦመሩ ጦመርክሙ ጦመረት ጦመርኪ ጦመራ ጦመርክን ጦመርኩ ጦመርነ

ውድ አንባብያን በዚህ መንገድ ግስን በተመለከተ የሚኖረውን አረባብ፣ ሙያና እርሱን የተመለከተውን ሁሉ በተከታታይ በሰፊው የምንመለከት ይሆናል ለዛሬው የቤት ሥራ እንድትሠሩ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጽፈንላችሁ እንለያያለን። የሚከተሉትን ግሶች በቀዳማይ አንቀጻቸው በዐሥሩም መራሕያን አርቧቸው።
-ተከለ
-ቀመረ
-ደምሰሰ
-ማሰነ
-ባህነነ
-ዜነወ
-ጥዕመ