ገብር ኄር (ለሕፃናት)

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ የተወደዳችሁ ሕፃናት? መልካም! እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን፣ ለወደፊትም የሚጠብቀን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ይመስገን! ልጆች! ስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ አለው፡፡ ‹ገብር ኄር› ማለት ‹በጎ፣ ታማኝ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ጸጋን (ተሰጥዎን) በአግባቡ ስለ መጠቀም እና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያስተምር ቃለ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ይነገራል፡፡ በተጨማሪም ስለ ‹ገብር ሐካይ› ጠባይ የሚያስረዳ ትምህርት ይቀርባል፡፡ ‹ገብር ሐካይ› ማለት ‹ሰነፍ አገልጋይ› ማለት ነው፡፡ የእነዚህን ሰዎች ታሪክም በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፭ ከቍጥር ፲፬ ጀምሮ እንደ ተጻፈው አንድ ሰው አገልጋዮቹን ጠራና ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት፤ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ ልጆች! ‹መክሊት› – ብር፣ ዶላር፣ እንደሚባለው ያለ የገንዘብ ዓይነት ነው፡፡

አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ነግዶ፣ ሌላ አምስት መክሊት አትርፎ ዐሥር አድርጎ ለጌታው አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ጎበዝ እና ታማኝ አገልጋይ! በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም አትርፎ አራት አድርጎ አቀረበ፡፡ እርሱንም ጌታው፡- ‹‹አንተ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ እርሱ ግን መክሊቱን ቀብሮ አቆየና ጌታው እንዲያስረክብ በጠየቀው ጊዜ፡- ‹‹እነሆ መክሊትህ!›› ብሎ ምንም ሳያተርፍበት መለሰለት፡፡ ጌታውም፡- ‹‹ይህን ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እጅ እግሩን አስራችሁ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ሥፍራ ውሰዱት! መክሊቱን ቀሙና ለባለ ዐሥሩ ጨምሩለት!›› ብሎ አዘዘ፡፡ ‹ገብር ሐካይ› የተባለው ይህ መክሊቱን የቀበረው አገልጋይ ነው፡፡

ልጆች! ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠንን ጸጋ በአግባቡ ከተጠቀምን ትልቅ ዋጋ እንደምናገኝ፤ ጸጋችንን በአግባቡ ካልተጠቀምን ደግሞ ቅጣት እንደምንቀበል ከዚህ ታሪክ እንማራለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለእናንተም ስታድጉ በመንፈሳዊው ሕይወታችሁ የጵጵስና፣ የቅስና፣ የዲቁና፣ የሰባኪነት፣ የዘማሪነት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ጸጋዎችን እንደየአቅማችሁ ይሰጣችኋል፡፡ በዓለማዊው ሕይወታችሁ ደግሞ የፓይለትነት፣ የመሐንዲስነት፣ የዶክተርነት፣ የመምህርነት፣ የመንግሥት ሠራተኛነት፣ ወዘተ. ሌላም ዓይነት የሥራ ጸጋ ያድላችኋል፡፡

መንፈሳዊውን ወይም ዓለማዊውን ትምህርታችሁን በርትታችሁ በመማር ካጠናቀቃችሁ በኋላ ከእናንተ ብዙ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ልጆች! በምድር ሕይወታችሁ እንዲባረክ፤ በሰማይም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንድትወርሱ እንደ ገብር ኄር የተሰጣችሁን ጸጋ በመጠቀም ቤተሰባችሁን፣ አገራችሁንና ቤተ ክርስቲያናችሁን በቅንነት ማገልገል አለባችሁ፡፡ በጣም ጥሩ ልጆች! ለዛሬው በዚህ ይበቃናል፤ በሌላ ዝግጅት እስከምንገናኝ ድረስ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይኹን! ሳምንቱ መልካም የትምህርት ጊዜ ይኹንላችሁ!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡