ክተ ብርሃኑ ተሾመ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ!

የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ዶክተር ብርሃኑ ተሾመ ከአባታችው ከአቶ ተሾመ አየለ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አበራሽ ዲባባ መስከረም ፲፰ ቀን በ፲፱፻፸፪ ዓ.ም. በአርሲ ዞን በጎለልቻ ወረዳ አሞልቾ (ሰፈረ ገነት) ተወልደው ዕድያቸው ለትምህርት ሲደርሱም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቻውን በአሞልቾ ወረዳና ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በጊንር ከተማ በከፍተኛ ውጤት አጠናቋል፡፡ በልጅነታቸው ከተማሩበት ደሎ ሰብሮ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆነው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይሳተፉ ነበር። ከዚያም ወደ ጊንር ለትምህርት በመጣ ጊዜ በጊኒር ጽጌ ተዋሕዶ ሰንበት ትምህርት ቤት በትጋት ያገልግሉ ነበር። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ እንደተሸጋገሩም ማኅበረ ቅዱሳን ባአዘጋጀው የአራት ኪሎ ግቢ ጉባኤ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመማር በመንፈሳዊ ሕይወት አሳልዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ፋኩልቲ (፬ ኪሎ) በመማር በስታትስቲክስ የትምህርት ዘርፍ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል። በዩኒቨርሲቲውም ስታትስቲክስ የትምህርት ክፍል መምህርነት ሌክቸረርነት ለሦስት ዓመታት ሠርቷል።

ከዚህም በኋላ በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም  በቤልጅየም ሀገር የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ስለተጠው  በአፕላይድ ስታትስቲክስ የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ድግሪ፣ እንዲሁም በ፳፻ ዓ.ም በባዮስታትስቲክስ የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ድግሪያቸውን ከሃሰልት ዩኒቨርሲቲ በጥሩ ውጤት  ተመርቀዋል። በዚያዉ በቤልጅየም ሀገር ሃሰልት ዩኒቨርሲቲ ባገኙት የሦስተኛ ድግሪ ትምህርት ዕድል በ፳፻ ዓ.ም የዶክትሬት ድግሪቸውን በባዮስታትስቲክስ አግኝቷል።

ዶክተር ብርሃኑ የዶክትሬት ድግሪያቸውን እንደጨረሰ እንግሊዝ ሀገር ባገኘው የድኅረ ምረቃ ሥራ ዕድል ለንደን በሚገኘው የንጽሕና ትሮፒካል ሕክምና ለሁለት ዓመታት ሠርተዋል። ከዚያም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካካበተው ጂ ኤስ ኬ ከተባለው የመድኃኒት አምራች ኩባንያ በሙያው ሠርቷል።

በ፳፻፯ ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስታትስቲክስ ትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፈሰር ደረጃ ለሦስት ዓመታት በማስተማር እና በተመራማሪነት ሠርቷል። ከማስተማር እና ምርምር ሥራ በተጨማሪ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የስታትስቲክስ ማኅበር ፕሬዝዳንት በመሆን ለትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተለይ በአውሮፓ ለትምህርት በቆዩበት ወቅት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን የቤልጅየም ግንኙነት ጣቢያ ሰባሳቢ፣ በዩኬ ንዑስ ማዕከል የክፍል ኃላፊ እንዲሁም ከ፳፻፯ እስከ ፳፻፰ ዓ.ም የአውሮፓ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ በመሆን በከፍተኛ ብቃት እና ቅንነት አገልግለዋል። በቤልጅየም የብራስልስ ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ዋና ጸሐፊ በመሆንም ለአጥቢያው መጠናከር የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡

በ፳፻፲፩ ዓ.ም ወደ ደቡብ አፍሪካ በመሄድ ኬፕታውን በሚገኘው በስተለንባሽ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ባዮስታትስቲሺያን ደረጃ ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ከ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ኅልፈተ ሞታቸው ድረስ በተባባሪ ፕሮፈሰርነት እየሠሩ ነበር።

ዶክተር ብርሃኑ በባዮስታትስቲክስ ሙያ ባላቸው ዕውቀት በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ ሀገር  ካሉ ከፍተኛ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን በርካታ የምርምር ሥራዎችን ለዓለም አበርክተዋል። በሕፃናት ጤና አጠባበቅ፣ በኤች አይ ቪ፣ በሳንባ፣ በስኳር፣ በካንሰር እና በሌሎች በሽታዎች ዙሪያ ከሠላሳ በላይ የምርምር ውጤቶችን በታወቁ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችንን እና ማኅበረ ቅዱሳንን በትጋት ሲያገለገሉ የኖሩ እንዲሁም ለብዙ ወንድሞች እና እኅቶች አርአያነት ነበረው አገልግሎት ሲያገለግሉ የኖሩት ዶክተር ብርሃኑ  ተግባቢ፣ ፈገግታ የማይለያቸው፣ ሁሉንም ለመርዳት የሚጥሩ ቅን ሰው ነበሩ።

ዶክተር ብርሃኑ ተሾመ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ፵፩ ዓመቱ ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በደብረ ምጥማቃት ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡ የወንድማችን ዶክተር ብርሃኑ ተሾመን (የብርሃነ ገብርኤል)  ነፍስ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን እንዲያድልልንና ለቤተሰቦታቸው መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን፤ አሜን፡፡