ድንቅ ቀን /ለሕፃናት/

መጋቢት 28/2004 ዓ.ም.

በልያ አበበ


ልጆች የዕረፍት ጊዜያችሁ ወይም የጨዋታ ሰዓት ሲደርስ በጣም ትደሰታላችሁ አይደል? እኔና ዘመዶቼ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ሰዎችን በማገልገል እነርሱንና ዕቃዎቻቸው ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ስንለፋ እና ስንደክም የምንኖር ቢሆንም በዓመቱ ውስጥ ግን ልክ እንደሰዎች እጅግ ተደስተንባቸው የምናሳለፋቸው በዓላት አሉ፡፡

 

Hosaena

 

አንደኛው በዓል የሁላችን ፈጣሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው ለዚያ ቀን እርሱ ቤተልሔም በሚገኝ የዘመዶቻችን ቤት /በሰዎች አጠራር በረት/ ውስጥ ሲወለድ አንደኛ በትሕትና በእንስሳት ቤት ለመወለድ በመምረጡ ሁለተኛ እጅግ ብርዳማ በነበረው የልደቱ ዕለት የእኛ ዘመዶች የሰው ልጆች እንኳን ያላደረጉትን በትንፋሻቸው እንዲሞቀው ስላደረጉ በጣም ደስተኞች ነን፡፡

ስሜ ደስተኛዋ አህይት ነው፡፡ አሁን የምነግራችሁ በሕይወቴ እጅግ የተደሰትኩበትና እኔና ዘመዶቼ እስካሁን የምንወደውን ሌላኛውን ቀን ነው፡፡ ቀደም ብዬ የነገርኳችሁን የቤተልሔሙን ልደት የነገረችኝ አንደኛዋ አክስቴ አህያ ናት፡፡ ሁል ጊዜም ያንን ታሪክ እንደ አክስቴ እኔም በቤተልሔም በረት ውስጥ በነበርኩ እል ነበር፡፡

 

ያ ቤተልሔም በሚኖሩ ዘመዶቻችን ቤት የተወለደው የዓለም ሁሉ ፈጣሪ እኛ እንኖርበት በነበረው ሀገር ለ30 ዓመት ከኖረ በኋላ የሀገራችን ሰዎች ሁሉ ማስተማር ጀመረ፡፡

 

እኔና እናቴ የምንኖረው ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ከሚባለው ቦታ ጥቂት እንደተሔደ በምትገኘው ትንሽ መንደር ነበር፡፡ የእኛ ባለቤት የሆነው ሰው ፈጣሪያችን በትንሽዬዋ የእንስሳት ቤት ሲወለድ የተደረጉትን ነገሮች ማለቴ የእረኞችና የመላእክትን ዝማሬ የሦስቱ ነገሥታት ስጦታን ማምጣት ሰምቶ ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ቦታ ሁሉ እየሔደ ይማር እጅግም ይወደው ነበር፡፡

 

ታዲያ አንድ ቀን ምን ሆነ መሰላችሁ፡፡ እናቴ ባለቤታችን አንድ ሁል ጊዜው ለብርቱ ሥራ ሊፈልገን ስለሚችል ብላ በጠዋት ቀሰቀሰችኝ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ሌላ ቀን ስትቀሰቅሰኝ ተኝቼ ማርፈድ የሚያምረኝ ቢሆንም የዚያን ቀን ወዲያውኑ ነበር የተነሣሁት፡፡ ፊቴን ከታጠብኩ እና ሰውነቴ ላይ ያለውን አቧራ ካራገፍኩ በኋላ ከእናቴ ጋር ሆነን ለዛ ቀን ያደረሰንን እና ጣፋጯን የጠዋት ፀሐይ እንድንሞቅ ላደረገው ፈጣሪያችን ጮክ ብለን እየጮህን ምስጋና አቀረብን፡፡

 

አሳዳሪያችን ከበረታችን አውጥቶ የቤቱ በር ላይ ባለ የእንጨት ምሰሶ ላይ አሰረንና ወደ ሌሎች ሥራዎች ተሰማራ፡፡ አሳዳሪያችን እንዲህ የሚያደርገው እርሱ ወደገበያ የማይወጣ እኛንም የሚያሥረን ሥራ ከሌለው ነው፡፡ እኔም እናቴም ቀኑን በሙሉ በማናውቀው ምክንያት ደስ ሲለን ዋለ፡፡

 

የሆነ ሰዓት ላይ ከሩቅ ሁለት ሰዎች ወደ እኛ መንደር ሲመጡ አየናቸው፡፡ ሰዎቹ እየቀረቡ መጡና እኛ ጋር ሲደርሱ አጎንብሰው የታሠርንበትን ገመድ ፈቱልን፡፡ ሰዎቹ ለጌታችን ፈጣሪያችን እንደሚፈልገን ነገሩን፡፡ እኛም በደስታ አብረናቸው ሔድን፡፡

 

ፈጣሪያችን ወደነበረበት ስንደርስ ምን እንደተደረገ ልንገራችሁ? ፈጣሪያችን በእኔ ላይ ልብስ ተነጥፎለት ተቀመጠና ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ጀመርን፡፡ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ በመንገድ የምናገኛቸው ሰዎች በሙሉ ሆሣዕና በአርያም እያሉ እየዘመሩ ልብሶቻቸውና የዘንባባ ዝንጣፊ በምናልፍበት መንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ ትንንሽ ሕፃናትም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ ዘመሩ፡፡ ትልልቆቹ መምህራን ግን ልጆቹን ተቆጥተው ዝም በሉ አሏአቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ተአምራዊ ነገር ተከሰተ፡፡ በመንገድ ላይ የነበሩ ድንጋዮች ሁሉ ልክ እንደ ሰው መዘመርና ፈጣሪያችንን ማመስገን ጀመሩ፡፡

 

ልጆች በዚያን ቀን ፈጣሪዬን በጀርባዬ ተሸክሜ 16 ምዕራፍ ያክል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወሰድኩት ታዲያ ይህንን ቀን እኛ አህዮችና ሌሎችም እንስሳት በታላቅ ደስታ እናከብረዋለን፡፡ ሆሣዕና ሕፃናት ፈጣሪያችንን ያመሰገኑበት ቀን ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ አክብሩት እሺ ልጆች፡፡