“ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ”

ታኅሣሥ  22/2004 ዓ.ም
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

በዛሬው ቀን ዓለም ለመዳን የቅድስት ድንግል ማርያምን ይሁንታን የፈለገበት ቀን ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከምንም በላይ የሰውን ነጻ ፈቃድ ስለሚያከብር መልአኩን ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲልከው ፈቃዱዋን ይጠይቃት ዘንድ ነበር፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት መሰላችሁ “እነሆ በደጅህ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል”(ራእ.3፡20) እንዳለው ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን በይዘቱ የቅድስት እናታችን  ይሁንታ በጣም የተለየ ነው፡፡ ስለዚህም የዓለም መዳን በእርሱዋ ይሁንታ ላይ ነውና እግዚአብሔር በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኩል የቅድስት ድንግል ማርያምን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ ለእርሱዋም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አንደበት እግዚአብሔር ቃል ለሰው ልጆች መዳን ከእርሱዋ ተፀንሶ ለመወለድ ፈቃዱ እንደሆነ፣ እርሱዋንም የዘለዓለም እናቱና የሰው ልጆችን ፍጹም የመውደዱ ምልክት ሊያደርጋት እንደወደደ አበሰራት፡፡ ቅድስት እናታችንም ፍጹም ትወደውና ታመልከው የነበረው እግዚአብሔር ከእርሱዋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን መፍቀዱን ስትሰማ በፍጹም ደስታ ተሞልታ ግሩም በሆነ ትሕትና “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” “እንደቃልህ ይደረግልኝ” በማለት ዓለምን እፎይ አሰኘቻት፡፡ እስከዛች ጊዜ ድረስ ዓለም በጭንቀት ተውጣ የእርሱዋን መልስ በጉጉት ትጠባበቅ ነበር፡፡

የቅድስት እናታችን የይሁንታ ቃል በተሰማ ጊዜ በሲኦል ያሉ ቅዱሳት ነፍሳት በደስታ ቦረቁ፡፡ በአካለ ሥጋ የነበሩ ነቢያትና ቅዱሳን እንደ እምቦሳ በደስታ ዘለሉ፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልም በደስታ ተውጦ ለመላእክት ጉባኤ “በቅድስት ድንግል ማርያም የይሁንታ ቃል ምክንያት ዓለም ዳነች” ብሎ የምስራች አላቸው፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል “… በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ” (ሕዝ.1፡26) ብሎ እንደገለጠው እግዚአብሔር አምላክ ለመላእክት በሰው ምሳሌ ተገልጦ ይታያቸው ነበር እንጂ እርሱን ገጽ በገጽ ለመመልከት አልበቁም ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ገብርኤል የፀንሰቱን ነገር ለመላእክት በነገራቸው ጊዜ ፈጣሪያቸው እግዚአብሔር ቃል ሰው በመሆን በአካል ሊያዩት እንደተቃረቡ ተረድተው ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቅ ታላቅ የሆነ የደስታ ዝማሬ ዘመሩ፡፡ በዚያን ጊዜ  ቅዱሳን መላእክት ደስታቸው ድርብ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ደስታቸው የሰው ልጆች መዳን ሲሆን ሁለተኛው ግን አምላካቸውን በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ ለማየት በመብቃታቸው ነበር፡፡ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ!!!