ያልተጻፈን ከማንበብ፣ የሌለን ታሪክ ከመጥቀስ መቆጠብ ያስፈልጋል

በጥፋት የታወሩ፣ በወንጀል የተጨማለቁ፣ በሐሰት ታሪክ የታጀሉ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን በጥፋተኝነት ሲወቅሷት፣ በቅኝ ገዥነት ሲያሳጧት ይደመጣሉ፡ እነዚህ ወገኖች ከእነሱ የተለየ አመለካከት ያላቸውን አካላት በመተቸት አንድም ተባባሪያቸው ለማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተሳስታችኋል ብለው እንዳይተቿቸው በር በመዝጋት የሚጠቀሙበት ስልት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ በክርስቲያኖች እና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተሰለፉ የጥፋት ኃይሎች ተከራክረው ለማሳመን የአመክንዮ ችግር እንዳለባቸው እንዳይታወቅባቸው ከሚጠቀሙበት ስልት አንዱ የሰዎችን ስሜት የሚኮረኩር ንግግር በማድረግ ሳያመዛዝኑ በጅምላ ተከታዮቻቸው እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

ዓላማቸው የሰዎችን ዕውቀት ማበልጸግ ሳይሆን ስሜታቸውን ሊቀሰቅስና በግብታዊነት ተነሣስተው በጥላቻ ጥፋትን እንዲፈጽሙ፣ ራሳቸውንም፣ የራሳቸውንም፣ ወገናቸውንም በመጥላት እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ሞቶ የሰነበተውን በክት የሚበሉ አሕዛብ ሳይቀር በጾም በጸሎት ተወስነው፣ በተጋድሎ ጸንተው የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በቃል ተከራክረው፣ በአሳብ ልቀው መርታት ሳይቻላቸው ሲቀር ስለ ክርስትና የሩቅ ግንዛቤ ያላቸው አካላት ወደ ክርስትና እንዳይቀርቡ ያደርጓቸው የነበረው ክርስቲያኖች የሰው ሥጋ የሚበሉ በማስመሰል ነበር፡፡ ለዚህም የሚጠቅሱት ‹‹ሥጋዬን የበላ፣ ደሜንም የጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› የሚለውን አምላካዊ ትምህርት ነበር፡፡ ይህን የሚያደርጉት አሕዛብ፣ መናፍቃንና የዘመኑ ፈላስፎች ስለ ክርስቶስ ያላቸውን አመለካከት በመቃረም የኑፋቄ አሳቦችን ያስተላልፉ ነበር፡፡

በዘመናችንም የሚደረገው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያንን ወራሪ፣ ክርስቲያኖቸን ሰብአዊነት የማይሰማቸው አድርገው የሚያቀርቡ ወገኖች ስለ ክርስትና እና ስለ ሀገራቸው ታሪክ በደንብ የሚያውቁትን ምሁራን እንዳይናገሩ በማስፈራራት ወይም በጥቅም በመደለል ዕውቀት የሌላቸውን ለእነሱ ዓላማ እንዲመቹ አድርገው ያዘጋጇቸዋል፡፡ ከእነዚህ ወገኖች አብዛኛዎቹ ሕዝብን ለማገልገል፣ ሀገርን ለመምራት ሥልጣን ሲሰጣቸው ሥልጣናቸውን የሰውን ልጅ ሁሉ ያለ አድሎ ለማገልገል ከመጠቀም ይልቅ በተንሸዋረረ የታሪክ ትርክት በእምነት የሚመስሏቸውን በመደገፍና የጥፋት ተልእኮ በማስታጠቅ ቤተ ክርስቲያንን እና ክርስቲያኖችን እንዲያጠቁ ያደርጋሉ፡፡ የሚገርመው ደግሞ በእንደዚህ ያለ አመራራቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውጭ መንግሥታት እንደሚተቿቸው አለማወቃቸው ነው፡፡ ለራሳቸው ታሪክ ያልሆኑ፣ አባቶቻቸውን ያላከበሩና፣ በቀደምቶቻቸው በአርበኝነት የሚሸማቀቁ መሆናቸውን የሚረዱት ምዕራባውያንም በድቃቂ ሳንቲም፣ በእላቂ ጨርቅ እያማለሉ ታሪካቸው የሚጠፋበትን፣ ማንነታቸው የሚዘነጋበትን፣ ክርስትና ከሀገራችን የሚወድምበትን እኩይ ተግባር ሲያስፈጽሟቸው ይኖራሉ፡፡ በዚህ ራሳቸውን ጠልተው ሌሎችን ለመምሰል በሚያደርጉት ማስመሰል ከሁለት የወጣ ሆነው እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል እንጂ የሚያስገኝላቸው ትርፍ አይኖርም፡፡

መረዳት የሚገባው ግን ቤተ ክርስቲያንን ማንም ምሁር፣ ፖለቲከኛ፣ ባለ ሥልጣን በጥፋተኝነት ሊወቅሳት፣ በዘረኝነትና በቅኝ ገዥነት ሊከሳት የሚችልበት ታሪካዊ መሠረቶች፣ ሞራላዊ ብቃት የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ራሱ በወንጀልና በዘረኝነት የተበከለ አካል ኵላዊት፣ ቅድስት፣ አሐቲ እና ሐዋርያዊት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን የመጠየቅ ችሎታ እንደሌለው መረዳት ይኖርበታል፡፡ ሌላውን ለመተቸት የተሻሉ ሆነው መገኘትን ይጠይቃልና፡፡ ሌላውን ለመጠየቅ ከመነሣት አስቀድሞ የቤተ ክርስቲያንን ባሕርያት እና የክርስቲያኖችን ሃይማኖትና ምግባር በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የሀገሩን ታሪክ ማወቅና ከዚያ በኋላ መደገፍም መቃወምም የወግ ነው፡፡ እንደ መናፍቅ በተቆነጸለ ጥቅስና በውሸት ትርክት ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት መሞከር በራሱ ላይ እባብ መጠምጠም መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በመያዝ መከራ እየተቀበለች ወንጌልን በአሕዛብ መካከል የምትሰብከውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ወራሪ ብሎ በድፍረት መናገር ከጥላቻና ከአላዋቂነት ያለፈ መልእክት የለውም፡፡

ሰው መልካም የሆነ ነገር መሥራት ሲሳነው፣ ሀገር የሚያበለጽግ አሳብ ማመንጨት አእምሮው ሲነጥፍበት አጀንዳ የሚያገኘው ቤተ ክርስቲያንን በመተቸት ይመስለዋል፡፡ በእርግጥ ከምድራዊ ገዢዎችና ሥጋዊ አመለካከት ካላቸው አካላት ቤተ ክርስቲያን ምስጋና ለማግኘት ትፈልጋለች ተብሎ ባይታሰብም በምርምር እያሳበቡ እውነትን ለመቅበር መሞከር የጥፋት ጥፋት ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቀው የሚሰማት እስከምታገኝ ማንነቷን መግለጥ ነው፡፡ በብዙ ተጋድሎ ከዘመናችን የደረሰችውም መሥራቿ ዘለዓለማዊ አምላክ በመሆኑ የእግዚአብሔርን መሠረት የሰው ልጅ ማጥፋት ስለማይቻለው ነው፡፡ ‹‹ሒዱ አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ›› የተባለውን ማሰብ ዛሬም እግዚአብሔር አብሮን እንዳለ ያስገነዝበናል፡፡

በዘመናችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ከግራኝ አሕመድ የጥፋት ዘመን ባልተናነሰ ጥፋት እየተፈጸመባት የመጣው አንድም የሐሰት ትርክት ሲጋቱ የኖሩ አካላት ሒሳብ ማወራረጃ ጊዜያችን አሁን ነው በማለት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ትዕግሥታችንን እንደ ፍርሃት፣ እንደ አላዋቂነት፣ እንደ የዋህነትና ለራሳችን እንደማናውቅ አድርገው በማሰብ ነው፡፡ በመንግሥት መዋቅር ተሰግስገው ቤተ ክርስቲያን የምትወድምበትን፣ ቅርሶቿ የሚጠፉበትን ተግባር ቢፈጽሙም ክርስቲያኖችን የሚጠብቅ አምላክ ስለማይተኛ በየዘመናቱ የቤተ ክርስቲያን ጠበቆችን ያስነሣል፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀውን ተጋድሎ በመፈጸም ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃሉ፣ ምእመናንን አጽናንተው በሃይማኖት ጸንተው እንዲቆሙ ያደርጋሉ፡፡ ራሳቸውንም ቤተ ክርስቲያናቸውንም እንዲጠብቁ ያደርጋሉ፡፡

በአንድ ወቅት የግብፅ አክራሪ የእስልምና እምነት ተከታዮች በክርስቲያኖች ላይ መጠነ ሰፊ ጥፋት ጀምረው ነበር፡፡ ከፈጸሙት ብዙ ጥፋት አንዱ አንድን ቄስ ገድለው ሚስቱን መድፈራቸው የሚጠቀስ ሲሆን ይህን ዘግናኝ ድርጊት የተመለከቱት የግብፅ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በክርስቲያኖች ላይ እንዲህ ዓይነት ጥፋት ሲፈጸም ቆሞ ከሚያይ መንግሥት ጋር አብሬ አልሠራም፡፡ ገዳም ገብቼ ለሀገር ሰላም እጸልያለሁ ብለው ወደ አባ ቢሾይ ገዳም ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ የግብፅ መንግሥት በውጭ ሚዲያዎች ተብጠለጠለ፣ ዲፕሎማሲው ወደቀ፡፡ የደረሰበትን ውድቀት የተረዳው የግብፅ መንግሥትም አባ ቢሾይ ገዳም ድረስ ሔዶ ፓትርያርኩን ለምኖ ወደ መንበረ ፕትርክናቸው መለሳቸው፡፡ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን በሚችለው ሁሉ ጥበቃ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ ለክርስቲያኖች ከለላ መስጠት ጀመረ፡፡

ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመታት በፊት የሙስሊም ወንድማማቾች የግብፅን መንግሥት መቆጣጠር ተከትሎ አክራሪ እስራሞች አብያተ ክርስቲያኖችን ለማቃጠል ሆን ብለው በተነሡ ጊዜ በመጀመሪያ እኛን ገድላችሁ ቤተ ክርስቲያንን ታቃጥላላችሁ እንጂ ጥፋታችሁን ቆመን አናይም ብለው እጅ ለእጅ እየተያያዙ አብያተ ክርስቲያኖችን የታደጉት ሙስሊሞች ናቸው፡፡ ይህ ታሪክ በእኛም ሀገር ሲፈጸም የኖረ ነው፡፡ ያልተጻፈ ድርሳን እየተነበበ፣ የሌለ ታሪክም እየተጠቀሰ ክርስቲያኖችን ከዋሉበት ላለማሳደር፣ ካደሩበትም ላለማዋል የሚፈጸመው እኩይ ድርጊት ከአሁኑ ካልተገታ ወደ ባሰ ብጥብጥ ያሸጋግረን ካልሆነ በቀር ሰላም እንደማያመጣ ተገንዝቦ ቤተ ክርስቲያንን እና ክርስቲያኖችን ዓላማ ከማድረግ መታቀብ አስተዋይነት ነው፡፡ ለሀገር የሚጠቅመውም ተከባብረን የምንኖርበትን አስተዳደር በመመሥረት እንጂ አንዱ አጥፊ ሌላው ጠፊ ሲሆን እያየን ቆሞ በማየት አይደለም፡፡

የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ‹‹ማንም ቤተ ክርስቲያንን በጥፋተኝነት ሊወቅሳት አይችልም፡፡ በየትኛውም ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ናት፡፡ ክርስቲያኑ ንጉሥ ሙስሊም ወገኖቻችንን ተቀብሎ እንዳስተናገደ የሙስሊም መጻሕፍት ጭምር የመሰከሩት እውነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ተከባብረን እየኖርን ያለነው፡፡ አንዳንድ አላዋቂዎች ቤተ ክርስቲያን ስለ ሀገር ምን አገባት ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ አላዋቂነት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሀገር ይገዳታል፣ ቤተ ክርስትያን ስለ ኢትዮጵያ ትጨነቃለች፣ ቤተ ክርስቲያን እኔን ብቻ ይድላኝ አትልም›› በማለት በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት መንግሥት እንዲያስቆም በሰላማዊ ሰልፍ ለመጠየቅ የባሕር ዳር ሕዝብ በወጣ ጊዜ ተናግረዋል፡፡ አባታችን እንዲህ ብለው የተናገሩት ራሳቸውን ሰጭ እና ነሽ አድርገው የሚቆጥሩ አካላት በመኖራቸው ነው፡፡ ‹‹ቤተ ክርስትያን ስለ ሀገር ምን አገባት›› የሚሉ አካላት እነሱ መብት ሲያገኙ ቤተ ክርስቲያንን ሊከለክላት የሚችል አለመኖሩን መረዳት ይገባቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ታቦት ተሸክማ፣ መስቀልን ተመርኩዛ፣ ምሕላ እያደረገች፣ ሱባኤ እየገባች ባቆየቻት ሀገር እየኖሩ ቤተ ክርስቲያንን አያገባትም ማለት አቅምን አለማወቅ፣ ታሪክን አለመመርመር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ሠራዊቱ፣ ስለ ገዢዎቹ፣ ስለ ወንዝ ውኃ፣ መሬት የዘሩባትን አብቅላ ከረኀብ፣ ከስደት እንድንድን ወደ ፈጣሪዋ የምትማልደው ቤተ ክርስቲያን መሆኗን መዘንጋት ነው፡፡ በሌላ በኩል የድንግል ማርያም የአሥራት ሀገር፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የግብዝና መቅደስ መሆኗን አለመረዳት ያመጣው የአላዋቂ ንግግር ወይም የአዋቂ አጥፊ ተልእኮ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንን ስለ ሀገር ያማያገባት፣ ስለ ሕዝቦቿ የማይገዳት አድርገው የሚያቀርቡ አካላት እስከ አሁን በለመዱት ክርስቲያኖቹን የማሸማቀቅ ስልታቸው ስለ ሰማያዊ መንግሥት የምትሰብክ ቤተ ክርስቲያንን ስለ ምድራዊ መንግሥት ምን አገባት ለማለት ይሞክራሉ፡፡ ይህም አላዋቂነት ነው፡፡ ሰማያዊ መንግሥት የሚወረሰው በምድር በሚሠራ በጎ ምግባር መሆኑን መረዳት የተሣናቸው፣ የዛሬን እንጂ ሩቅ ማሰብ የማይችሉ ናቸው፡፡ በጎ ሥራ የሚባለው ደግሞ ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ በጸሎት መጠየቅ፣ በአሳብ መደገፍ፣ የተሳሳተውን ማስተካከል፣ እውነቱ እንዲገለጥ ማድረግን ያጠቃልላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስን ይዛ አድዋ ድረስ የዘመተችው፣ ጦርነቱ ሲጀመርም ጸሎት አድርጋ የቁም ፍታት አድርጋ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጊያ የላከቻቸው ለሀገር ስለሚገዳት ነው፡፡ በዘመኑ ያን ባታደርግ ዛሬ ያለው ታሪካችን በተለወጠ ነበር፡፡

ሰማዕተ ጽድቅ ዐርበኛ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ መጀመሪያ እስከ ማይጨው ንጉሡን ተከትለው የዘመቱት በኋላም ከነደጅ አዝማች አበራ ካሳ ጋር ደብረ ሊባኖስ አካባቢ ሆነው ዐርበኞችን ሲያበረቱ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ስለ ሀገር ስለሚገዳት መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ ለጥፋት የተሰለፉ አካላት በአንድ በኩል ስለ ሀገር እደማያገባት ተናግረው በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን አግላይ፣ ለሆነ አካባቢ የምታደላ፣ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሊያምንባት የሚገባ አስመስለው የዋሃንን ያሳስታሉ፡፡ ይህ ክርስቲያኖችን ማዘናጊያ እንጂ ትክክል አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ኵላዊነት ያልተረዱ መናፍቃን ጀምረውት ፖለቲከኞች ቆንፅለው የወሰዱት አሳብ ነው፡፡ መታረም ያለበት ግን ቤተ ክርስቲያንን አግላይ አድርጎ መረዳቱ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጥፋት ኃይሎች በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሱት ባለው ጥቃት ‹‹ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመኖቿን ለማጥፋትና ለመግደል ቢያደቡም ሞት ግን ክርስቲያኖችን አስደንግጦ አያውቅምና ይህ ከቶ አያስፈራንም እኛ የማንንም መብት አለመንካት የዘወትር ተግባራችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራ ሀገራችን ናት፤ የእኔ ብቻ የምትባል አይደለችም›› ያሉት ቤተ ክርስቲያን ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለሚያሳድዷት ሁሉ የምትጸልይ ኃዳጊተ በቀል መሆኗን ያሳያል፡፡ ርግብ እንቁላሏን እየሰበሩባት፣ ቤቷን አፍርሰው እያባረሯት ቦታዋን ለቃ እንደማትርቅ ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ናት፡፡ ሊያቃጥላት የመጣውን፣ ልጆቿን ሊያጠፋ የተሰለፈውን በፍቅር ስባ ልብ እንዲገዛ ታደርገዋለች፡፡ ከዚህ ከብፁዕ አቡነ አብርሃም ንግግር ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትምህርት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመስቀል በፊት ሠርቶ ያጠናቀቀውን የአሥራ አምስት አብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባስረከበበት ወቅት እንዲህ በማለት ተናግረዋል፡- ‹‹ወጣት የአሥሩ ማኅበራት ኮሚቴዎች ወጥታችሁ ወርዳችሁ የቤተ ክርስቲያን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጥ ስላደረጋችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተችው ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳይ ከፍተኛ ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለሳችሁ መልካም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን ጠይቃ አታውቅም፡፡ ሳልጠቅስ የማላልፈው ጉዳይ ታላቁ የባሕረ ጥምቀታችን ማክበሪያ እየተቆራረሰ ከማለቁ በፊት የባለቤትነታችን ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጠን ነው፡፡ እንዲሁም መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመሥራት ለከተማዋ ነዋሪዎች ሲያስተላልፉ ወደተሻለ ቤት ሲገቡ ስናይ በእጅጉ ደስ ይለናል፡፡ ነገር ግን እስከ አሁን ያልታሰበበት ጉዳያችን የአምልኮት ቦታ ነው›› ብለዋል፡፡

እዚህ ላይ የማንንም መብት አለመንካት የዘወትር ተግባራችን ነው የሚለው የብፁዕነታቸው ንግግርና ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን አትጠይቅም የሚለው የቅዱስነታቸው መልእክት የቤተ ክርስቲያንን ባሕርይ የሚገልጥ የክርስቲያኖችን ሥነ ምግባር ላላወቁት የሚያስገነዝብ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች እንኳን የሌላውን ሊጠይቁ የራሳቸውን ሰጥተው የሚኖሩ፣ ስለ ክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጥ ያላቸውን ገንዘብ በመስጠት አልረካ ብለው ራሳቸውን ሰጥተው ፍቅራቸውን የሚገልጡ ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ለዚህ የክርስቲያኖች ምግባርና ለዓለም ድኅነት ለምትጸልየው ቤተ ክርስቲያን ያለ ግብራቸው ግብር፣ ያለ ስማቸው ስም እየሰጡ ለማጥፋት መሞከሩ ነው፡፡

ከቤተ ክርስቲያ ጋር መታገል ለመላላጥ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነ ኔሮን፣ እነ ዳኬዮስ፣ እነ ዲዮቅልጥያኖስ፣ እነ መክስምያኖስና ሌሎችም አፅራረ ክርስቲያኖች ታግለው አልጧላትም፡፡ በተሳለ ሰይፍ ላይ በግብዝነት ቁመው ተቆርጠው እንደ ወደቁ መረዳት ይገባል፡፡ ላቆመችው የራሷ ምስል ፍቅር ይዟት አምላኳን ያስካዳት ንግሥት አውዶክስያና ባለቤቷ ንጉሥ አርቃዴዎስ ጻድቁን ፓትርያርክ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ባጋዙት (በወኅኒ ቤት ባሰሩት) ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ትዘጋ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዓለሙ ሁሉ ስለ ጠላህ ለእውነት መቆምህን ትተህ ዓለሙን ምሰል ብለው ሐዋርያዊው አትናቴዎስን በመከሩት ጊዜ ‹‹እኔም ዓለሙን አልፈልገውም›› ብሎ መንበረ ፕትርክናውን ለቆ ገዳም በገባ ጊዜ ትዘጋ ነበር፡፡ በሀገራችንም በዝሙት እሳት አብደው የአባቶቻቸውን ሚስቶች ባገቡት በንጉሡ ዓምደ ጽዮን እና በሰይፈ አርዕድ ዘመን ሁሉን ለክርስቶስ የሰጡ እነ አቡነ ፊሊጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ አቡነ አኖሬዎስ፣ አቡነ አሮን መንክራዊና ሌሎችም ለምን ተቃወማችሁ ተብለው በተጋዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ትዘጋ ነበር፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡

አምላክ ከቤተ ክርስቲያን እንደማይለይ ከቀደምቶቹም ከራሱ ሕይወትም ያረጋገጠው ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ጊዜ ትዋጋለች፤ ተሸንፋ ግን አታውቅም፣ ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ፤ ቀስቱንም ጨረሰ፤ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም›› ያለውን ትምህርት ደጋግሞ መመርመር ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በባሕር ላይ የምትቀዝፍ መርከብ ናት፡፡ የፈራ እየንተጠባጠበ ይቀራል እንጂ እሷ በአውሎና በወጀብ ውስጥ መንገድ ባለው አምላክ እየተመራች ዜጎቿን ለመንግሥተ ሰማያት ታበቃለች፡፡ እኛ ስለ ቤተ ክርስቲያን የምንናገረው ራሳችን ፈርተን ከመርከቧ እንዳንወጣ እንጂ እሷ ትሰምጣለች ብለን አይደለም፡፡

ይህን ጽሑፍ የምናጠቃልለው በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሔድ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ የሚያስተባብረው ኮሚቴ መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም በሰጠው መግለጫ ሲሆን ‹‹ርእዮተ ዓለም መር ከሆኑ የስሕተት ትርክቶች የተነሣ በሃይማኖታዊ ማንነታቸው ምክንያት ብቻ ለልዩ ልዩ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች ተዳርገው ከቀያቸው የተፈናቀሉ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለሉ፣ ከኃላፊነት ቦታቸው እና ከሥራ መደባቸው የተባረሩ፣ ዛሬም በዚህ ጫና ውስጥ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ተገቢውን ፍትሕ እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትክክለኛ ማንነት እና ሀገራዊ ውለታ በአግባቡ የማይገልጡ እና መሠረት የለሽ ትርክቶች እንዲታረሙ›› በጥብቅ በማሳሰብ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ተልእኮዋ ሁልጊዜ እውነትን በመያዝ የተጣመመው እንዲቃና የተበላሸው እንዲስተካከል ያለመታከት መሥራት መሆኑን በማስተዋል ሊረዱት እንደሚገባ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም ልናስገነዝብ እንወዳለን፡፡

ምንጭስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከመስከረም ፲፮፴ቀን ፳፻፲፪ .ም.