የጽጌ ጾም

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ እርሱን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብፅ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታችንን ያገኘው መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የሆኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡

በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ሆኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትሆን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጌታችንና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኃ ግንቦት ነው፤ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባና የፍሬ ወቅት በመሆኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ በዘመነ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በሰፊው ተገልጧል፡፡

የጽጌ ጾም በቤተክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ያሉት አርባ ቀናት ዘመነ ጽጌ (ወርኃ ጽጌ) እንደሚባሉ ይታወቃል። በነዚህም ቀናት በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነበቡ ምንባቦች፣ የሚዘመሩ መዝሙሮች፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚቆመው ማኅሌት፣ በጠቅላላው የሚነገረው ስብሐተ እግዚአብሔር ሁሉ ሰማይ በከዋከብት ምድር በጽጊያት አሸብርቀው የሚታዩ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው። በወርኃ ጽጌ ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት መነሻው ‹‹መልአኩ ሕፃኑና እናቱን ወደ ግብጽ ይዘሃቸው ሽሽ፤ ሕፃኑን ሊገድሉት ይሻሉና›› ሲል ለዮሴፍ በሕልሙ በነገረው መሰረት  ሕፃኑን እናቱን ድንግል ማርያምን ይዞ ዮሴፍ ወደ ግብፅ መሰደዱና እመቤታችንና ሕፃኑን ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስደት ከኖሩ በኋላ ወደ አገራቸው ወደ ናዝሬት የመመለሳቸው መታሰቢያ ነው። (ራእይ ፲፪፥፲፮)

በዐሥራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሡ አባት አባ ጽጌ ብርሃን ‹‹የሮማን ሽቱ የቀናንም አበባ የምትሆኝ ማርያም ሆይ ፥ በረሃብ በጾም አበባ የመሰለ የመልክሽ ደም ግባት እስኪ ጠወልግ ድረስ በስደትና በለቅሶ የደረሰብሽን ችግርና ድካም መከራሽንም ሁሉ እንደ እኅትሽ እንደ ሶሎሜ አብሬሽ ብቀበል ምኞቴ ነበር፤ በዚህም ፍጻሜ የሌለውን ደስታሽን እሳተፍ ነበር።›› ብለዋታል፡፡ እንዲሁም አባ አርከ ሥሉስ በስደቷ የደረሰባትን ኀዘን፣ ልቅሶና ሰቆቃ አስመልክተው በደረሱት ‹‹ሰቆቃወ ድንግል›› በሚለው ድርሰታቸው እንዲህ አሉ፦ ‹‹ፀሐይን የምትለብሽ የብርሃን ልጅ ቅድስት ድንግል ማርያም ከክፉ ከሄሮድስ ዘንድ ልጅሽን ባሸሽ ጊዜ የደረሱብሽን ችግሮች ጨረቃን የሚጫሙ እግሮችሽ በመንገድ ብዛትና በአሸዋ ግለት እንዳጎበጎቡ ሲሰማ ሰው ይቅርና ድንጋዩም ባለቀሰ ነበር።››

በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታትም ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን የሚተነትነው ቅዳሴ ማርያም ነው፤ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው፡፡

የማኅሌተ ጽጌና የጾመ ጽጌ አጀማመር የእመቤታችን የስደቷ መታሰቢያ ወር በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው በማኅሌት፣ በቅዳሴና በዝክር ነው። በወርኃ ጽጌ ባሉት ሳምንታት ከቅዳሜ ማታ እስከ እሑድ ጥዋት አበው ካህናት የሚያቀርቡት ዝማሬ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ፣ ከማኅሌተ ጽጌና ከሰቆቃወ ድንግል የተውጣጣና ሦስት ወገን ያለው ነው። ዝክሩም በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ እየተረሳ ቢመጣም፥ ዘወትር እሑድ የአንድ አካባቢው ሰዎች ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተሰባስበው በእመቤታችን ስም የሚዘክሩት ነው። ዐቅመ ደካሞች ድሆችና መንገደኞች ተጠርተው በእመቤታችን ስም እንዲበሉና እንዲጠጡ ይደረጋል። ይህም ትውፊት እመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ በመጣች ጊዜ ኢትዮጵያውያን እናቶችና አባቶች ያደረጉላትን መስተንግዶ ለማሰብ ነው።

የጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ዜና ገድል የጽጌን ጾም አስመልክቶ የሚከተለውን ይተርካል፦ ‹‹አባ ጽጌ ብርሃን የተባለው አባት እንደ መዝሙረ ዳዊት መቶ ኀምሳ አድርጎ ማኅሌተ ጽጌን ደረሰ። አባ ጽጌ ብርሃን ይህንን በደረሰበት ጊዜ የወረኢሉ ተወላጅና የደብረ ሐንታው አባ ገብረ ማርያም አማካሪው ነበር። ድርሰቱንም ሲደርስ ቤት እየመታና በአምስት ስንኝ እየከፋፈለ ነው። አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም ከመስከረም  ፳፮ ቀን እስከ ኅዳር ፭ ቀን ማኅሌተ ጽጌን ለመቆምና የጽጌን ጾም ለመጾም በየዓመቱ በደብረ ብሥራት እየመጡ ይሰነብቱና ቁስቋምን ውለው ወደየ በአታቸው ይመለሱ ነበር።›› ከአባታችን የገድል ክፍል ለመረዳት እንደሚቻለው አባ ጽጌ ብርሃንና አባ ገብረ ማርያም የጽጌን ማኅሌት መቆም ወቅቱንም በፈቃዳቸው መጾም የጀምሩበ ዘመን በዐሥራ አራተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ነው።

ከዚያ ወዲህ ግን ጥቂት በጥቂት እያለ አብያተ ክርስቲያናት በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ጀመሩ። ጥቂት መነኩሳትና አንዳንድ ምእመናን በፈቃዳቸው ወቅቱን መጾም ጀመሩ። በዘመናችን በወርኃ ጽጌ የጽጌን ማኅሌት መቆም ስለ ተለመደ ከማታው በሦስት ሰዓት ይደወላል። ሴት ወንዱ፥ ትንሹም ትልቁም ይሰባሰባል፤ ማኅሌተ ጽጌው እየተዜመ፤ አስፈላጊ የሆነው በጽናጽል በከበሮ እየተወረበና እየተሸበሸበ እስከ ጥዋቱ ፲፪ ሰዓት ድረስ ተቁሞ ይታደራል። የጽጌ ጾም የውዴታ (የፈቃድ) እንጂ የግዴታ አይደለም። የእመቤታችን ስደት በማሰብ ከትሩፋት ወገን የሚጾም ስለሆነ ምእመናን ሁሉ እንዲጾሙት አይገደዱም፤ የሚጾመው የማይጾመውን ለምን አልጾምክም ብሎ ሊፈርድበት ስለ ራሱም እየጾምኩ ነው ብሎ መናገር አይገባውም። የፈቃድ መሆኑንም የሚያሳየው ይኸው ነው፤ የማይጾመውም በልቡ ያመሰግናል፤ ስደቷን እያሰበ ማኅሌቷን እየዘመረ ያሳልፋል።

አምላካችን እግዚአብሔር የጽድቅ ፍሬን ሳናፈራ በሞት እንዳንወሰድ በቸርነቱ ይጠብቀን፤ አሜን፡፡