Tserha Tsion Sebakian wongel

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ሰባኪያነ ወንጌልን አስመረቀ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር በ14ኛው ዙር ለ3 ወራት ያሰለጠናቸውን 47 ሰባኪያነ ወንጌልን ሚያዚያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡ በማኅበሩ የተመሠረተው የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የስብከተ ወንጌልTserha Tsion Sebakian wongel ማሰልጠኛ ተቋም በ12 የትምህርት ዓይነቶች ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከ16 ሀገረ ስብከቶች በተለይም ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተውጣጥተው የተመረጡና እያንዳንዳቸው ከሁለት እስከ ሦስት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሰባኪያነ ወንጌልን ቡራዩ አካባቢ በሚገኘው በተቋሙ ግቢ ውስጥ በደመቀ መንፈሳዊ መርሐ ግብር አስመርቋል፡፡ ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል መነኮሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ያካተተ ሲሆን ‹‹ለቤተ ክርስቲያናችን እጣን፣ ጧፍና ንዋያተ ቅድሳት ብቻ ሳይሆን ሰውም እንስጥ›› የሚል መመሪያ ይዞ በመነሣት በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ማናዬ አባተ የማኅበሩ መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንዲሁም ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ‹‹ማኅበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት ለሌሎች አርአያ የሚሆንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደጋፊ አገኘች የምንልበት ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡ ለተመራቂ ደቀBitsu Abune Epiphanios መዛሙርትም “ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር እናንተን በወንጌሉ ቃል እንዳስታጠቃችሁ በሔዳችሁበትና በደረሳችሁበት ስፍራ ሁሉ የጠፉትን ወገኖቻችን የተበተኑትን አንድ በማድረግ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውለታ ለትመልሱ ይገባል” በማለት አደራቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱን ካስተማሩ አባቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ ባስተላለፉት መልእክት “ግራኝ መሐመድ እንደተሸነፈ ልክ እንደዛሬው ማኅበረ ቅዱሳንና ማኅበረ ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ ኖረው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አፍሪካን ታጠምቅ ነበር፡፡” በማለት የማኅበሩን ጥረት አበረታተዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት ልጆቻቸው ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ በማድረግ ረገድ በየሰንበት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በዕለቱ በመድረክ ላይ ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል፡፡ ተመራቂ ደቀ መዛሙርትም አስር በሚደርሱ ቋንቋዎች ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የተማሩትን ትምህርት በተግባር ላይ እያዋሉ ስለመሆናቸው ምስክር ይሆን ዘንድ በአንድ ተመራቂ ደቀ መዝሙር ትምህርተ ወንጌል ተሰጠቷል፡፡

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ከሰንበት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡና በአንድነት በመኖር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፊት ጽኑ አላማ ባላቸው ምእመናን የካቲት 23 ቀን 1980 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ቀደም ሲል ከፍትህ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ የመለከት መጽሔትን በማሣተምና በማሰራጨት፤ በአካባቢው ለሚገኙ ረዳት ለሌላቸው አረጋውያንና ወላጅ አልባ ለሆኑ ሕፃናት የዕለት ምግብ በመስጠት፤ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስና የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ በማድረግ ፤አቅም ለሌላቸው በማኅበሩ ዘመናዊ ት/ቤት በአነስተኛ ክፍያ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር ባለ ሁለት ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ በማጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሔደውን የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠናን በአንደኛው ፎቅ ላይ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ አስር የማደሪያ ክፍሎች ሲኖሩት በአንድ ዓመት በ2 ዙር እስከ 120 ደቀ መዛሙርትን ማሰልጠን ያስችላል፡፡ የመጸዳጃ ቤት፣ የገላ መታጠቢያ፣ የምግብ ማብሰያና በአንድ ጊዜ ከ500 ሰው በላይ ማስተናገድ የሚያስችል አዳራሽ የያዘ ነው፡፡ ስልጣገኞቹ ሙሉ የሕክምና ወጪ፤ የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ በቀን 3 ጊዜያት የሚመገቡት ምግብ በማኅበሩ ይሸፈናል፡፡ ሕንፃው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የሰባኪነ ወንጌል ማሰልጠኛ ተቋም በዓመት በ3 ዙር የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠና ለመስጠት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ማኅበሩ እስከ አሁን ድረስ በ14 ዙር ሥልጠናዎች 612 ሰባኪያነ ወንጌል ማሰልጠኑን መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው አቶ ማናዬ አባተ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ ሠልጣናቹ የዘመናዊ ትምህርት ተማሪ ከሆኑ 10ኛ ክፍልና ከዚያ በላይ፣ የአብነት ተማሪ ከሆኑ በዘመናዊው ትምህርት ስድስተኛ ክፍልና ከዚያ በላይ የሆኑትን ከየሀገረ ስብከቱ የሚመረጡበት መስፈርት ሲሆን በተጨማሪም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የወሰኑና የአካባቢውን ቋንቋ መስማትና መናገር የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡

ከደቡብ ኦሞ ጂንካ ሀገረ ስብከት አንቀጸ ብጹአን አቡነ ተክለ ሃይማሃት ቤተ ክርስቲያን የመጡት አባ ኃ/ሚካኤል በድሉ ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ “አካባቢያችን በመናፍቃን የተከበበ ነው፡፡ ምዕመናንም ሆኑ ካህናት ብዙ እውቀት የለንም፡፡ መናፍቃንን የምናሸንፍበት ትምህርት አጥተን ብዙዎች ተወስደውብናል፡፡ በሥልጠናው በነፃ የተቀበልነውን እውቀት በነፃ ለወገኖቻችን እናስተምራለን” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከምዕመናን መካከል ከጉጂ ቦረናና ሊበን ሀገረ ስብከት ሜጋ ቅዱስ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ተሰማ ርቀት ሳይገድባቸው እዚህ ድረስ የመጡት ከሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን ተመርጠው ለሰልጠናው የመጡትን ተመራቂ ደቀ መዛሙርትን ለመቀበል እንደሆነና አካባቢያቸውን አስመልክተው ባደረጉት ገለፃ “ያለንበት አካባቢ እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ ኬንያ ድንበር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ የአገልጋዮች እጥረት ያለበትና ቦታውም አመቺ ያልሆነ ነው፡፡ የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ደርሶልን ከጭንቅ እየገላገለን ነው፡፡ ወደፊትም ትብብራችሁ እንዳይለየን” በማለት ተማጽነዋል፡፡

ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ከብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እጅ የምስክር ወረቀትና መጽሐፍ ቅዱስ ተቀብለዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ የደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምክሐ ደናግል ማርያም ሰንበት ትምህርት ቤት በስጦታ የተገኘ ስለመሆኑ ከሓላፊዎቹ የተገለጸ ሲሆን  ደቀ መዛሙርቱን ለማፍራት በተደረገ ጥረት ውስጥ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሥልጠናውን ለሰጡ አካላት ማኅበሩ ምስጋናውን በእግዚአብሔር ስም አቅርቧል፡፡