የግሥ ዝርዝር በመራሕያን

መምህር በትረማርያም አበባው
ኅዳር ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፈው ትምህርታችን ዐሥሩ መራሕያን አይተን ነበር፡፡ በዚያም መሠረት ለሰጠናችሁ መልመጃ ምላሽና ግሦችን በመራሕያን እንዴት መዘርዘር እንደምችል በዚህ ሳምንት ትምህርታችን አዘጋጅተን አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ይሁንላችሁ!

የመልመጃ ጥያቄዎች
፩) በሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች ያሉትን መራሕያን አገልግሎታቸውን ለዩ!
ሀ) ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም
መልስ፡- መራሕያን- ውእቱ
አገልግሎት- የዓረፍተ ነገሩ ማሰሪያ ወይም ግሥ ነው፤
ትርጉም፡- ዓለም ሳይፈጠር ንጉሥ ነበር፤

ለ) አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም
መልስ፡-መራሕያን- አንቲ እና ውእቱ
አገልግሎት- አንቲ በዓረፍተ ነገር ውስጥ ተውላጠ ስም (የስም ምትክ)ነው፤ የቅድስት ድንግል ማርያምን ስም ተክቷል፡፡
ውእቱ-የዓረፍተ ነገሩ ማሰሪያ ወይም ግሥ ነው፡፡
ትርጉም፡- የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ፤

ሐ) አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት
መልስ፡-መራሕያን- አነ እና ውእቱ
አገልግሎት- አነ- በዓረፍተ ነገር ውስጥ ተውላጠ ስም (የስም ምትክ) ነው፤ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስም ተክቷል፡፡
ውእቱ-የዓረፍተ ነገሩ ማሰሪያ ወይም ግሥ ነው፡፡
ትርጉም፡-ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ፤

መ) ውእቱ ሚካኤል ያፈቅረነ
መልስ፡-መራሕያን-ውእቱ
አገልግሎት-በዓረፍተ ነገር ውስጥ የስም አጋዥ ሆኗል፡፡
ትርጉም፡-እርሱ ሚካኤል ይወደናል፡፡

፪) የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ አማርኛ ተርጉሙ
ሀ) ኪያየ አፍቅሩ
መልስ፡-እኔን ውደዱ

ለ) ኪያክሙ ተወክፈ
መልስ፡-እናንተን ተቀበለ

ሐ) ለሊነ ንመውት
መልስ፡-እኛ እንሞታለን

መ) ኪያሃ ናፈቅር
መልስ፡-እርሷን እንወዳለን

፫) የሚከተሉትን ዓረፍተ ነገሮች ወደ ግእዝ ተርጉሙ
ሀ) የእኛ ወንዝ
መልስ፡-ፈለገ ዚአነ
ለ) የአንቺ ትሕትና
መልስ፡-ትሕትና ዚአኪ

ውድ አንባብያን! የመልመጃ ጥያቄዎቹን በትክክል መልሳችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ግሦች በመራሕያን እንዴት እንደሚዘረዘሩ እንመለከታለን፡፡
አንድ ግሥ ወይም ማሰሪያ አንቀጽ በአሥሩ መራሕያን ሲዘረዘር እንደሚከተለው ነው።

አንደኛ አካሄድ
፩) በውእቱ ጊዜ ምንም የሚጨመር ነገር የለም። ምሳሌ አእመረ ብሎ ዐወቀ ይላል።
፪) በውእቶሙ ጊዜ መድረሻ ፊደሉን ወደ ካዕብ መለወጥ ነው። ይኽውም አእመሩ ብሎ ዐወቁ ይላል።
፫) በይእቲ ጊዜ መድረሻ ፊደሉ ላይ “ት” ፊደልን መጨመር ነው። ይኽውም አእመረት ብሎ አወቀች ይላል።
፬) በውእቶን ጊዜ መድረሻ ፊደሉን ወደ ራብዕ መለወጥ ነው። አእመራ ብሎ አወቁ ይላል።
፭) በአንተ ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ሳድስ ለውጦ “ከ” ፊደልን መጨመር ነው። አእመርከ ብሎ አወቅህ ይላል።
፮) በአንትሙ ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ወደ ሳድስ ለውጦ “ክሙ” ፊደልን መጨመር ነው። አእመርክሙ ብሎ አወቃችሁ ይላል።
፯) በአንቲ ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ወደ ሳድስ ቀይሮ “ኪ” ፊደልን መጨመር ነው። አእመርኪ ብሎ አወቅሽ ይላል።
፰) በአንትን ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ወደ ሳድስ ቀይሮ “ክን” ፊደልን መጨመር ነው። አእመርክን ብሎ አወቃችሁ ይላል።
፱) በአነ ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ወደ ሳድስ ቀይሮ “ኩ” ፊደልን መጨመር ነው።አእመርኩ ብሎ አወቅሁ ይላል።
፲) በንሕነ ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ወደ ሳድስ ቀይሮ “ነ” ፊደልን መጨመር ነው።አእመርነ ብሎ አወቅን ይላል።

አብዛኛው ግሥ ይህንን መስሎ ይዘረዘራል። አስተውል በሁለተኛ መደቦችና በአንደኛ መደቦች ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ወደ ሳድስ ቀይሮ ባእድ ቀለማትን “ከ፣ ክሙ፣ ኪ፣ ክን፣ ነ፣ ኩ”ን ይጨምራል። በላይኛው አካሄድ አንድ ምሳሌ እንመልከትና የተለየ አካሄድ ያላቸውን ግሦች እንመለከታለን።
መራሒ……..ግእዝ……አማርኛ
፩) አነ ………..አፍቀርኩ……ወደድኩ
፪) ንሕነ………አፍቀርነ…….ወደድን
፫) አንተ……….አፍቀርከ…….ወደድክ
፬) አንትሙ…..አፍቀርክሙ……ወደዳችሁ
፭) አንቲ………አፍቀርኪ…….ወደድሽ
፮) አንትን……አፍቀርክን…….ወደዳችሁ
፯) ውእቱ……አፍቀረ……ወደደ
፰) ውእቶሙ….አፍቀሩ…..ወደዱ
፱) ይእቲ……….አፍቀረት…..ወደደች
፲) ውእቶን…… አፍቀራ….ወደዱ

አስተውሉ! በግእዝ ቋንቋ ወንዶችን ወደዳችሁ ስንልና ሴቶችን ወደዳችሁ ስንል የተለያየ ነው። ወንዶችን ወደዳችሁ ስንል አፍቀርክሙ እንላለን። ሴቶችን ወደዳችሁ ስንል ደግሞ አፍቀርክን እንላለን። ወንዶች ወደዱ ስንል አፍቀሩ እንላለን። ሴቶችን ወደዱ ለማለት አፍቀራ እንላለን። ሴት እና ወንድ ተቀላቅለው ካሉ ደግሞ በወንድ አንቀጽ አፍቅርክሙ፣ አፍቅሩ እንላለን ማለት ነው። ሁለት ፊደል ሆነው በ”ሀ” እና በ”አ” የሚጨርሱ ግሦችም ይህንኑ መስለው ይዘረዘራሉ።

ምሳሌ ፩፦ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ ኖኅኩ ረዘምኩ
፪) ንሕነ ኖኅነ ረዘምን
፫) አንተ ኖኅከ ረዘምክ
፬) አንትሙ ኖኅክሙ ረዘማችሁ
፭) አንቲ ኖኅኪ ረዘምሽ
፮) አንትን ኖኅክን ረዘማችሁ
፯) ውእቱ ኖኀ ረዘመ
፰) ውእቶሙ ኖኁ ረዘሙ
፱) ይእቲ ኖኀት ረዘመች
፲) ውእቶን ኖኃ ረዘሙ
በ”አ” ሲጨርሱ ደግሞ እንደሚከተለው ነው።

ምሳሌ ፪፦ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ ሦዕኩ ሠዋሁ
፪) ንሕነ ሦዕነ ሠዋን
፫) አንተ ሦዕከ ሠዋህ
፬) አንትሙ ሦዕክሙ ሠዋችሁ
፭) አንቲ ሦዕኪ ሠዋሽ
፮) አንትን ሦዕክን ሠዋችሁ
፯) ውእቱ ሦዐ ሠዋ
፰) ውእቶሙ ሦዑ ሠዉ
፱) ይእቲ ሦዐት ሠዋች
፲) ውእቶን ሦዓ ሠዉ

አስተውል! በሁለት ፊደል ጨርሰው መድረሻቸው “አ፣ዐ” ወይም “ሀ፣ ኀ፣ ሐ” የሆኑ ግሦች የሚዘረዘሩት በዚህ መልኩ ነው። ሦስትና ከዚያ በላይ ፊደል ያላቸው በሀ እና በአ የሚጨርሱ ግሦች ግን የተለየ አካሄድ ስላላቸው አካሄድ አምስት ላይ ተመልከት።

ሁለተኛ አካሄድ
በ “ነ” የሚጨርስ ግሥ ልክ እንደመጀመሪያው አካሄድ የሚዘረዘር ሲሆን በንሕነ ብቻ የተለየ አካሄድ አለው። ይኽውም “ነ”ን ይጎርድና “ጠብቆ” እንዲነበብ ያደርገዋል።
መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ ወጠንኩ ጀመርኩ
፪) ንሕነ ወጠ[ነ] ጀመርን
፫) አንተ ወጠንከ ጀመርክ
፬) አንትሙ ወጠንክሙ ጀመራችሁ
፭) አንቲ ወጠንኪ ጀመርሽ
፮) አንትን ወጠንክን ጀመራችሁ
፯) ውእቱ ወጠነ ጀመረ
፰) ውእቶሙ ወጠኑ ጀመሩ
፱) ይእቲ ወጠነት ጀመረች
፲) ውእቶን ወጠና ጀመሩ

አስተውሉ! ውእቱ ወጠነ ሲል እና ንሕነ ወጠነ ሲል በጽሑፍ ተመሳሳይ ቢሆኑም በንባብ ይለያያሉ። ንሕነ ወጠነ ሲል [ነ] ጠብቆ ይነበባል። ውእቱ ወጠነ ሲል ግን ላልቶ ይነበባል።

ሦስተኛ አካሄድ
የገብረ ቤቶች በአሥሩ መራሕያን ሲዘረዘሩ በአንደኛ መደቦች ማለትም በአነ እና በንሕነ እና በሁለተኛ መደቦች ማለትም በአንተ፣ በአንትሙ፣ በአንቲ፣ እና በአንትን ጊዜ ቅድመ መድረሻቸውን ወደ ግእዝ ለውጠው ይዘረዘራሉ። የገብረ ቤት የሚባሉት ሦስት ፊደል ያላቸው ግሦች ሆነው መነሻቸው ግእዝ መካከለኛው ሳድስ መጨረሻው ግእዝ የሆኑ ግሦች ናቸው። ለምሳሌ ሠምረ የሚለው ግሥ የገብረ ቤት ይባላል። ምክንያቱም መጀመሪያ ሦስት ፊደል ያለው ሲሆን በመቀጠል “ሠ” ግእዝ ነው። “ም” ሳድስ ነው። “ረ” ግእዝ ነው። ስለዚህ የገብረ ቤቶች እንደሚከተለው ይዘረዘራሉ።

መራሒ………ግእዝ……አማርኛ
፩) አነ ገበርኩ ሠራሁ
፪) ንሕነ ገበርነ ሠራን
፫) አንተ ገበርከ ሠራህ
፬) አንትሙ ገበርክሙ ሠራችሁ
፭) አንቲ ገበርኪ ሠራሽ
፮) አንትን ገበርክን ሠራችሁ
፯) ውእቱ ገብረ ሠራ
፰) ውእቶሙ ገብሩ ሠሩ
፱) ይእቲ ገብረት ሠራች
፲) ውእቶን ገብራ ሠሩ

አራተኛ አካሄድ
በ”ቀ፣ ከ፣ ገ” የሚጨርሱ ግሦች በአሥሩ መራሕያን ሲዘረዘሩ በአንደኛ መደብ በአነ ብቻ እና በሁለተኛ መደቦች በአንተ፣ በአንትሙ፣ በአንቲ፣ በአንትን ጊዜ “ከ” ጎርደው ጠብቀው ይነበባሉ። ለምሳሌ ሰበከ አስተማረ ይል የነበረው ሰበከ አስተማርክ ይላል እንጂ ሰበክከ አይልም። አስተማርክ ሲል ያለው “ሰበከ” ከ ጠብቆ ይነበባል።በምሳሌ እንመልከት።

ምሳሌ ፩፦ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ ሰበ[ኩ] አስተማርኩ
፪) ንሕነ ሰበክነ አስተማርን
፫) አንተ ሰበ[ከ] አስተማርክ
፬) አንትሙ ሰበ[ክ]ሙ አስተማራችሁ
፭) አንቲ ሰበ[ኪ] አስተማርሽ
፮) አንትን ሰበ[ክ]ን አስተማራችሁ
፯) ውእቱ ሰበከ አስተማረ
፰) ውእቶሙ ሰበኩ አስተማሩ
፱) ይእቲ ሰበከት አስተማረች
፲) ውእቶን ሰበካ አስተማሩ

በዚህ ምልክት [ ] የተቀመጡ ቃላት ጠብቀው እንደሚነበቡ ለማመልከት ነው።አስተውል በጽሑፍ ደረጃ ውእቱ ሰበከ ሲልና አንተ ሰበከ ሲል ተመሳሳይ ቢሆንም በንባብ ግን ይለያያል። አንተ ሰበከ ከሚለው “ሰበከ” ሲል “ከ” ይጠብቃል። አነ ሰበኩ በሚለውና ውእቶሙ ሰበኩ በሚለው መካከልን በጽሑፍ ተመሳሳይነት ቢኖርም በንባብ አነ ሰበኩ ከሚለው “ኩ” ይጠብቃል። በዚያኛው ላልቶ ይነበባል ማለት ነው። ቀጥለን የምናያቸው የቀ እና የገ ግሦችም ይህንኑ ይመስላሉ። የአነ እና የአንተ ሲጠብቅ የውእቱ እና የውእቶሙ ላልቶ ይነበባል።

ምሳሌ ፪፦ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ አጥመ[ቁ] አጠመቅሁ
፪) ንሕነ አጥመቅነ አጠመቅን
፫) አንተ አጥመ[ቀ] አጠመቅህ
፬) አንትሙ አጥመ[ቅ]ሙ አጠመቃችሁ
፭) አንቲ አጥመ[ቂ] አጠመቅሽ
፮) አንትን አጥመ[ቅ]ን አጠመቃችሁ
፯) ውእቱ አጥመቀ አጠመቀ
፰) ውእቶሙ አጥመቁ አጠመቁ
፱) ይእቲ አጥመቀት አጠመቀች
፲) ውእቶን አጥመቃ አጠመቁ
የ”ገ”ን በምሳሌ እንይና ወደቀጣዩ አካሄድ እንሂድ

ምሳሌ ፫፦ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ ኀደ[ጉ] ተውኩ
፪) ንሕነ ኀደግነ ተውን
፫) አንተ ኀደ[ገ] ተውክ
፬) አንትሙ ኀደ[ግ]ሙ ተዋችሁ
፭) አንቲ ኀደ[ጊ] ተውሽ
፮) አንትን ኀደ[ግ]ን ተዋችሁ
፯) ውእቱ ኀደገ ተወ
፰) ውእቶሙ ኀደጉ ተዉ
፱) ይእቲ ኀደገት ተወች
፲) ውእቶን ኀደጋ ተዉ

አምስተኛ አካሄድ
ሦስት ፊደልና ከዚያ በላይ የሆነ በ”ሀ፣ኀ፣ሐ” ወይም በ”አ፣ዐ” የሚጨርስ ግሥ ሲዘረዝር በአንደኛ መደቦችና በሁለተኛ መደቦች ጊዜ ቅድመ መድረሻውን ራብዕ አድርጎ ይዘረዘራል።

ምሳሌ ፩፦ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ መጻእኩ መጣሁ
፪) ንሕነ መጻእነ መጣን
፫) አንተ መጻእከ መጣህ
፬) አንትሙ መጻእክሙ መጣችሁ
፭) አንቲ መጻእኪ መጣሽ
፮) አንትን መጻእክን መጣችሁ
፯) ውእቱ መጽአ መጣ
፰) ውእቶሙ መጽኡ መጡ
፱) ይእቲ መጽአት መጣች
፲) ውእቶን መጽኣ መጡ

ምሳሌ፦፪ መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ መራሕኩ መራሑ
፪) ንሕነ መራሕነ መራን
፫) አንተ መራሕከ መራሕ
፬) አንትሙ መራሕክሙ መራችሁ
፭) አንቲ መራሕኪ መራሽ
፮) አንትን መራሕክን መራችሁ
፯) ውእቱ መርሐ መራ
፰) ውእቶሙ መርሑ መሩ
፱) ይእቲ መርሐት መራች
፲) ውእቶን መርሓ መሩ

ስድስተኛ አካሄድ
የክህለ ቤት ሆነው መድረሻ ቀለማቸው “የ” የሆኑ ግሦች ሲዘረዘሩ በአንደኛና በሁለተኛ መደቦች “የ”ን ይጎርዱና ቅድመ መድረሻቸውን ወደ ሣልስ ቀይረው ይዘረዘራሉ። የክህለ ቤት የሚባሉት መነሻቸው ሳድስ መካከላቸው ሳድስ መጨረሻቸው ግእዝ የሆኑ ሦስት ፊደል ያላቸው ቃላት ናቸው።

መራሒ ግእዝ አማርኛ
፩) አነ ርኢኩ አየሁ
፪) ንሕነ ርኢነ አየን
፫) አንተ ርኢከ አየህ
፬) አንትሙ ርኢክሙ አያችሁ
፭) አንቲ ርኢኪ አየሽ
፮) አንትን ርኢክን አያችሁ
፯) ውእቱ ርእየ አየ
፰) ውእቶሙ ርእዩ አዩ
፱) ይእቲ ርእየት አየች
፲) ውእቶን ርእያ አዩ

በግሥ ዝርዝር በመራሕያን ጊዜ የአንትን ዝርዝር ሥርዓተ ንባቡ ተጣይ ነው። የይእቲ ዝርዝር ሥርዓተ ንባቡ ሰያፍ ነው። የሌሎች ሥርዓተ ንባባቸው ተነሽ ነው።

መልመጃ
የሚከተሉትን ግሦች በዐሥሩ መራሕያን ዘርዝር
፩) ኮነ……ሆነ
፪) ሎሀ….ጻፈ
፫) ሰገደ….ሰገደ
፬) ጥዕየ….ዳነ
፭) ለቅሐ…..አበደረ
፮) ሐገገ……ሕግ ሠራ
፯) ሠምረ…..ወደደ

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!