የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፯

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፯ ቀን ፳፻፲ .

፩.፰ ፍቺ የሚፈቀድባቸው መንገዶች

በክፍል ስድስት ዝግጅታችን እንደ ጠቀስነው ጋብቻ፣ ፈተና ቢበረታበትም መነጣጠል፣ መለያየት የማይስማማው ጥምረት ነው፡፡ ስለዚህም ‹‹ከዛሬ ጀምሮ በቃኝ›› ተብሎ የሚቋረጥ የኮንትራት ኑሮ አይደለም፡፡ ኾኖም ለጥንዶቹ ሰላማዊ ኑሮ፣ ለሕይወቱ ክብርና ለተጣመሩበት ሥጋ ወደሙ ቅድስና እንቅፋት የሚያመጡና በውይይት ወይም በእርቅ የማይስተካከሉ ችግሮች ከተከሠቱ መፋታት ይፈቀዳል፡፡ ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረትም ይቻላል፡፡ ፍቺ መፈጸምና ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረት ከሚቻልባቸው መንገዶች መካከል ዋና ዋናዎቹም የሚከተሉት ናቸው፤

ሀ. ዝሙት

መፋታት ከሚፈቀድባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው ዝሙት ነው፡፡ ዝሙት፣ ያገቡትንም ያላገቡትንም የሚፈታተን የኀጢአት ዓይነት ነውና ስለዚህ ኀጢአት መጠነኛ ትምህርት ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡

ወደ ትምህርቱ ስንገባ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ሩካቤ ሥጋ (አመንዝራ) ‹ዝሙት› ይባላል፡፡ ይህም በትዳር ላይ ሌላ ሴት (ወንድ) መደረብ ወይም መሰራረቅ (ከሌላ መሔድ) ነው፡፡ ሴሰኝነት ደግሞ ከፍተኛ የዝሙት ስሜትን ያመለክታል፡፡ ዝሙት፣ አመንዝራ፣ ሴሰኝነት ዂሉም ካልጠግብ ባይነትና ራስን ካለመግዛት የሚመጡ የኀጢአት ዘሮች ናቸው፡፡ የዝሙት መንፈስ የስስት ውጤትም ነው፤ ይኸውም ያለኝ ይበቃኛል አለማለትና ዐዲስ ነገርን ያውም የራስ ያልኾነን ነገር መመኘት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን “የባልጀራህን ሚስት አትመኝ፡፡ የባልንጀራህንም ቤት እርሻዉንም ሎሌዉንም ገረዱንም በሬዉንም አህያዉንም፣ ከባልንጀራህ ገንዘብ ዂሉ ማናቸውንም አትመኝ፤” በማለት መፈጸም ይቅርና መመኘት እንኳን እንደማይገባን አዝዞናል (ዘፀ. ፪፥፲፯፤ ዘዳ. ፭፥፳፩)፡፡ ዝሙት ማለት እንግዲህ የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፍ ከሚስት (ከባል) ውጪ በመሴሰን ሰውነትን ማቆሸሽ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቃል የሚናገረው ዐቂበ ርእስን (ራስን መጠበቅ) ገንዘብ ስለ ማድረግና በንጽሕና ስለ መጽናት ቢኾንም ቃሉን በተግባር የሚፈጽሙት ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ዝሙትን ልማድ አድርገን የምንኖር ኀጥኣን በርካቶች ነን፡፡ ከዚህ ክፉ ልማድ የምንረዳውም ሰይጣን ወደ ምድር ከለቀቀብን የወረርሽኝ በሽታዎች መካከል ዝሙት ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዝ ነው፡፡ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች እንደምንሰማው አንድ ለአንድ መወሰንና ከጋብቻ በፊት ራስን መጠበቅ እንደ ኋላ ቀርነት የተቈጠረ ይመስላል፡፡ “ጓደኛ” በሚል ሰበብ አንድ ወንድ የብዙ ሴቶች ባል፤ አንዲት ሴት የብዙ ወንዶች ሚስት የሚኾኑበት አጋጣሚ ተለምዷል፡፡ በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ግብረ ዝሙት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ በስካር፣ በስሜታዊነት ወይም በግዴለሽነት ተገፋፍተን ካገኘነው ዂሉ ጋር በዝሙት የምንድቅ ወነኖች ቤት ይቍጠረን፡፡ ይህ ዂሉ ከዘማዊነታችን የመነጨ ውጤት ነው፡፡

ከጣልያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ በአገራችን እንደ ተስፋፋ የሚነገርለት የሴተኛ አዳሪነት ልማድ ባለ ትዳሮችን ጨምሮ የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት እየበከለ ይገኛል፡፡ በየመገናኛ ብዙኃኑ እንደምንሰማው ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ወጣት እኅቶቻችን ገንዘብ ለማግኘት በሚል ሰበብ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ለሥነ ልቡናዊ ችግርና ለልዩ ልዩ በሽታ የሚጋለጡ እኅቶቻችን ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም ፅንስ ለማስወረድ በሚያደርጉት ጥረት የሚሞቱም ብዙዎች ናቸው፡፡ ከማያውቁት ወንድ የሚወልዱ እናቶችና አባታቸውን የማያውቁ ልጆችም እንዳሉም ለመገመት አያዳግትም፡፡ ይኼ ደግሞ በእናቶችም በልጆችም የሚያስከትለው የሥነ ልቡና ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር አገር በምትባለው በኢትዮጵያ የምንኖር ክርስቲያኖች ሳይቀር የዚህ ኀጢአት ሰለባዎች መኾናችን እጅግ ያሳፍራል፤ ያሳዝናልም፡፡

በዝሙት መተዳደር ከሚያስገኘው ገንዘብና ከመብትነቱ ይልቅ ነጻነትን የሚቀማና ማንነትን የሚያሳጣ ተግባር መኾኑን በማስተዋል ይህን ድርጊት የሚከለክል ሕግ በአገራችን መንግሥት ሊወጣም ይገባል፡፡ መብት ማለት ለሰዎች የሚጠቅም ምርጫ እንጂ እየተጎዱ እንዲኖሩ መፍቀድ ማለት አይደለምና፡፡ በመኾኑም የዝሙት ተግባር ከመብትና ከገቢ ምንጭነት በተለየ መንገድ ቢታይ መልካም ነው፡፡ ወገኖቻችን በእንጀራ ምክንያት ራሳቸውንም ሌሎችንም ወደ ጥፋት እየወሰዱ ነውና፡፡

ጋብቻ የመሠረትን ትዳራችንን ወደ ኋላ በመተው፣ ያላገባንም ራሳችንን በመጣል ከማናውቃቸው ሴቶች ጋር ሰውነታችንን ማሳደፍ በምድርም በሰማይም ያስጠይቀናልና ላለፈው በደላችን ንስሐ ገብተን ለወደፊቱ ራሳችንን እንጠብቅ መልእክታችን ነው፡፡ በሕግ ያልተወሰንን ወጣቶችም የራሳችን አጋር እስኪትመጣልን ድረስ ፈቃደ ሥጋችንን ልንቈጣጠር ይገባል፡፡ “ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮው የጐደለ ነው እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ምሳ. ፮፥፴፪)፣ የዝሙት ኀጢአት ሰይጣናዊ ደዌ ነውና በዝሙት ኀጢአት የምንኖር ዂሉ የሰይጣንን አሽክላ ሰባብረን በራሳችን ጊዜ ከገባንበት እስራት ነጻ እንውጣ፡፡ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሔደንም እንፈወስ፡፡

ወደ ቀደመ ርእሳችን እንመለስና ባልና ሚስት በሕይወተ ሥጋ እያሉ ሊፋቱ የሚችሉት በአመንዝራ (በዝሙት) ምክንያት ነው፡፡ የፍትወት ፆር ከመበርታቱ የተነሣ ከትዳር አጋር አልፎ ወደ ሌላ የሚሔድ ካለ ስለ አንደኛው ደኅንነትና ስለ ጋብቻ ክቡርነት፣ እንደዚሁም ስለ ሥጋ ወደሙ ቅድስና ሲባል መፋታት ይፈቀዳል፡፡ አምላካችን “ኢትዘሙ፤ አታመንዝር” በማለት እንዳስተማረን ዝሙት መሥራት ኃጢአት ነው (ዘፀ. ፳፥፲፬)፡፡ ቢቻል ከኀጢአት ተለይቶ ለመኖርና በጽድቅ ሥራ ለመትጋት መሽቀዳደም ተገቢ ነው፤ ኾኖም ኀጢአት እየሠሩ አብሮ ከመኖር ተለያይቶ በጽድቅ መኖር ይገባልና ከመዘሞት መፋታት ይሻላልና፡፡ ደግሞም በአንድነት ወደ ገሃነመ እሳት ከመጣል ይልቅ ተለያይቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ይመረጣል፡፡ “… ሁለት ዓይና ኾነህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትገባ ይልቅ አንድ ዐይና ኾነህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃልና” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፭፥፳፱-፴)፡፡

ይህ ሲባል ግን የሐሰት ወሬ በመስማትና በይኾናል (በጥርጥር) ብቻ ለመፋታት መወሰን ተገቢ አይደለም፡፡ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም በዝሙት እየወደቁ ከኾነና በንስሐ መመለስ ካልቻሉ ፍቺ ይፈጸማል፡፡ በጋብቻ ወቅትም ይኹን ከጋብቻ በፊት ወይም በኋላ መዘሞት (መሴሰን) አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ ስለዚህም መፋታት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ዝሙት እንዲኾን ተደንግጓል፡፡ ይህም ዝሙት ቊርባንን ከማፍረሱም ባለፈ ከጋብቻ ውጪ ልጅ መውለድን፣ እንደዚሁም በጥንዶቹም፣ በልጆቻቸውም ላይ ሞትን ያመጣልና የሰውን ልጅ ከጥፋት ለመታደግ ነው፡፡

ከዚህ ላይ ልብ ማለት የሚገባን ቁም ነገር ቢኖር ወንድም ኾነ ሴት በዝሙት ምክንያት የተፈቱትን ማግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ “ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ዂሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ዂሉ ያመነዝራል” እንዳለ ጌታችን (ማቴ. ፭፥፴፩)፡፡ ማግባት የሚቻለው ንስሐ ግበተው፣ ከዝሙት ርቀው፣ ራሳቸውን ጠብቀው፣ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ተወስነው ከሚኖሩት ወገን ነው፡፡ ዂሉም ምእመናን በዚህ ክርስቲያናዊ ግብር መኖር መንፈሳዊ ግዴታችን ነውና፡፡ “ኢይደልዎ ለመኑሂ ከመ ያውስብ ብእሲተ ኅድግተ እምዝሙት በጕጕዓ አላ ይጽናሕ እስከ ትኔስሕ፤ ስትሰስን ተገኝታ የተፈታችዉን ሴት ለማንም ፈጥኖ ማግባት አይገባውም፡፡ በንስሐ እስክትመለስ ድረስ ይጠብቅ እንጂ” እንዲል ፍትሐ ነገሥት፡፡

ይቆየን