የጅማ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች እስር እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ታወቀ

በካሣሁን ለምለሙ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጅማ ሀገረ ስብከት የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የተላለፍወን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን በማድረግ አግባብ ያልሆነ እስርና እንግልት በምእመናንና በአባቶች ላይ እየተፈጸመ መሆኑን በማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል አስታወቀ፡፡

እንደማእከሉ ገለጣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት የተላለፈውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፀጥታ ኃይሉ በጅማና አካባቢው የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንን ነጥሎ ለማጥቃት አመቺ የሆነ ሁኔታ ፈጥሮለታል፡፡

አንዳንድ የጅማ የፀጥታ ኃይሎች መንግሥትና የጤና ሚኒስቴር ከሚሰጡት መመሪያ ውጭ በሆነ መልኩ ካህናት፣ ዲያቆናት እንዲሁም አስተዳዳሪዎችን ያስሩና ገንዘብ ጭምር ይቀጡ እንደነበር ማእከሉ አስታውቆ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስትም የአንድን እምነት ተቋም ምእመናን ብቻ ለይቶ ማጥቃት እንደማይገባ  አስገንዝቧል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ምልዐተ ጉባኤ የወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን በየገዳማቱና አድባራቱ በማውረድ ላይ የነበሩትን የጅማ የየሞና የኮንታ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም መምህር ተስፋ ሚካኤል አሰፋ ‹‹አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጥሰሃል›› በሚል ሽፋን በጅማ የፀጥታ ኃይሎች ታስረው እንደተፈቱ ማእከሉ አስታውቋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ተግባራዊ ካደረጉ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የጅማ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሲሆን በቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ንግሥ ባዕል ወቅት ምእመናን ርቀታቸውን ጠብቀው በሚጸለዩበት ወቅት ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችዋል›› በሚል የአካባቢው የፀጥታ ኃይል የደብሩን አስተዳዳሪ መልአከ ሣህል ቆሞስ አባ ገብረ ኢየሱስን አስሮ እንደፈታቸው ያረጋገጠው ማእከሉ በወቅቱ ማእከሉን ሲደግፉ በነበሩ ምእመናንም ላይ መጠነኛ ድብደባና ወከባ እንደተፈጸመ ገልጧል፡፡

እስካሁን የታሰሩት ምእመናንና አባቶች ከእስር የሚፈቱት የሀገረ ስብከቱ፤ የመምሪያ ኃላፊዎችና አስተዳዳሪዎች በየጊዜው ለፀጥታ ኃይሉ በሚያቀርቡት አቤቱታ እንደሆነ ማእከሉ አስታውቋል፡፡

የጅማ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ፈድሉ መሐመድ በበኩላቸው በጅማና አካባቢው በሚገኙ አብያተክርስቲያንም ሆነ ምእመናን ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት የሕግ ጥሰትና ሃይማኖታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ ገልጠዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ለመግታት የተጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያላከበረ ግለሰብም ሆነ ተቋም ግን በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

የጅማ ሀገረስብከት ሥራ አስኪያጅም ሆነ ሌሎች ምእመናን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል የሚል ጥርጣሬ በፀጥታ ኃይሉ በኩል በመኖሩ ለተጨማሪ ምርመራ ታሥረው እንደተለቀቁ የጠቀሱት ኢንስፔክተር ፈድሉ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር የደረሰችበትን ስምምነት የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ እኛ ዘንድ ባለመኖሩ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጭ የሆነ እንቅስቃሴ የሚያደረጉ አባቶችንም ሆነ ምእመናን በሕግ ተጠያቂ አድርገናል›› ብለዋል፡፡

ኢንስፔክተር ፈድሉ አያይዘውም ‹‹አንዳንድ የጅማ የፀጥታ ኃይሎች ለሚከተሉት ሃይማኖት በመወገንና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሽፋን በማድረግ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች  ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ የተባለው ፈጽሞ የተሳሳተ ሀሳብ እንደሆነ ገልጠው በአንጻሩ የፀጥታ ኃይሉ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ብቻ የተከተለ የፀጥታ ሥራ እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ኢንስፔክተር ፈድሉ ከሕገ መንግሥቱ ያፈነገጠ ድርጊት በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ ተፈጽሞ እንደማያውቅ ጠቅሰው ‹‹ሁልጊዜም ቢሆን ሥራዎችን የምንሠራው ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመመካከር ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ከኦርቶዶክሳውያን አባቶች ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላቸውና በሃይማኖት ተቋማት መካከል አድሏዊ የሆነ ፀጥታ የማስከበር ሥራ እየሠሩ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡