የዕለተ ሠሉስ ፍጥረታት

መምህር ሃይማኖት አስክብር

                                   ታኅሣሥ ፬ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ዕለተ ማክሰኞ የፍጥረት ሦስተኛ የምስጋና ሁለተኛ ቀን ነች፤ በባሕረ ሐሳብ ቀመር ደግሞ ዕለተ ቀመር ትባላለች፤ በፀሐይ አቆጣጠር ሰባተኛ ቀን ትባላለች፡፡ ዛሬ ግን የምናነሣው በዕለተ ፍጥረት ስለተከናወነባት ክንዋኔ ነው፡፡

እግዚአብሔር ፍጥረትን መፍጠር ከጀመረ በሦስተኛው ቀን በዕለተ ማክሰኞ እንዲህ ብሎ ምድርን አዘዛት፤ ‹‹ምድር በየዘሩ፣ በየወገኑና በየመልኩ ዘር የሚሰጥ ቡቃያን፣ በምድርም ላይ በየወገኑ ዘሩ በውስጡ የሚያገኘውንና ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ ታብቅል፡፡››(ዘፍ ፩-፲፩) ይህንን እግዚአብሔር በተናገረ ጊዜ ታዛዧ ምድር ሦስት ሥነ ፍጥረትን በጣት የሚለቀሙ አትክልት፣ በማጭድ የሚታጨዱ ሰብልና በምሳር የሚቆረጡ ዕጽዋትን አስገኝታለች፡፡ እነዚህም ድንቅ ፍጥረታት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከምድር ተገኝተዋል፤  ለሰው ልጅም አገልግሎት ይውላሉ፤ ለመድኃኒትነት፣ ለምግብነት፣ ለአንክሮተ እግዚአብሔር ይጠቀምባቸዋል፡፡

በዚህ ዕለት የተገኙት እነዚህ ፍጥረታት ለሰው ልጅ ጥቅም ብቻ ሳይሆን የምድርም ጌጥና ውበት ናቸው፡፡ ዕርቃኗን የነበረች ምድር በእጽዋት፣ በአዝርእት፣ በአትክልት እነዚህ ሥነ ፍጥረት አሸብርቃ፣ ደምቃና ተውባ ታይታለች፤ ይህች ገራህይተ ሠሉስ የፈጣሪዋን ቃል ሰምታ ትእዛዙንም ፈጽማለች፤ ‹‹ወርእየ እግዚአብሔር ከመ ሠናይ፤ እግዚአብሔርም የፈጠረው ፍጥረት መልካም እንደሆነ አየ፡፡›› (ዘፍ ፩-፲፪)

በእግዚአብሔር ቃል የሚሆነው መልካም ነውና እኛም ሥራችንን ቃሉን እየሰማን ፈቃደ እግዚአብሔርን ብንሠራ እንደምን ይወደድ ይሆን? በእግዚአብሔር ዘንድም መልካም ይሆናል እንጂ የሚጠላ አይሆንም፡፡ ገራህይተ ሠሉስ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ስትጀምር የምድር ጌጥ የሆኑ ፍጥረታትን አስገኘች፤ እኛም የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ስንጀምር እንደ ገራህይተ ሠሉስ ሕይወታችን በእግዚአብሔር ቃል ያጌጣል፤ ሥራችንም በእግዚአብሔር ስም የተወደደ ይሆናል፡፡ የተራቆተችው ምድር የእግዚአብሔርን ቃል ስትሰማ ለመለመች፤ ተዋበች፤ የሰው ልጅም ቃለ እግዚአብሔርን ሲሰማ ነፍሱ በመንፈሳዊ ልምላሜ ትዋባለች፡፡ ሰው ዕርቃኑን የሚሆነው ከእግዚአብሔር ቃል ሲርቅ ነውና የእግዚአብሔር ቃል የሕይወታችን የፀጋ ልብስ ነው፡፡

በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜ ደግሞ ገራህይተ ሠሉስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ ገበሬ ሳይጥር ሳይግርባት የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ለሰው ልጅ ለመድኃኒትነት፣ ለምግብነት እንዲሁም ለምድር ጌጥ የሚሆኑ ፍጥረታትን አስገኝታለች፤ ከአማናዊት ገራህይት እመቤታችንም ያለ ዘርዓ ብዕሲ ቃል ወልደ እግዚአብሔርን አስገኝታለች፡፡ ይኸውም ለሰው ልጅ ጊዜያዊ ምግብ ያይደለ ዘለዓለማዊ ምግብ ጊዜያዊ መድኃኒት ያይደለ ዘለዓለማዊ መድኅኒተ ሥጋ ወነፍስ ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በድርሰቱ ላይ እመቤታችንን መስሎ ሲያመሰግናት ‹‹አንቲ ውእቱ ገራህይት ዘኢተዘርእ ውስቴታ ዘር…፤ በውስጧ ዘር ሳይዘራባት ለምልማ አብባ የተገኘች ገራህተ ሠሉስ ነበረች፡፡ ድንግል አንቺም ያለ ዘርዓ ብዕሲ የአብ አካላዊ ቃል ይዘሽ የተገኘሽልን አማናዊት ገራህተ ሠሉስ ነሽ›› ብሎ አመስግኗታል፡፡ ይህች ገራህተ ሠሉስ ለሥጋውያን ምግብ መድኃኒት አስገኝታለች፤ እንዲሁም ዕርቃኗን የነበረችውን ምድርን አስውባለች፡፡

በገራህይተ ሠሉስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ለመንፈሳዊያን ምግብ መድኃኒት እንዲሁም የሕይወታችን ጌጥ የሆነውን ንጉሥ ክርስቶስን አስገኝታለች፤ ዕርቃኗን የነበረችውን መሬት የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት እንድትዋብ አድርጋለች፤ እመቤታችን የሰው ልጅ በኃጢአት ተራቁቶ የነበረውን የፀጋ የድኅነት ልብስን እንዲለብስ ሆኗል፡፡ እንደ ምድር ዕርቃኑን የነበረው አዳም እመቤታችን የእግዚአብሔርን ቃል ክርስቶስን የሚገርም የፀጋ ልብስ እንዲጎናፀፍ አደገረ፤ ስለዚህም ገራህይተ ሠሉስ የምድር ጌጥ እንደሆነች አማናዊት ገራህይት እመቤታችንም በምድር ለምንኖረው ለሰው ልጆች ጌጥ ናት፡፡

የሰው ልጅ የፀጋ ልጅነትን ተጎናጽፎ እንዲኖር እመቤታችን ቃል ወልደ እግዚአብሔርን ስለወለደችልን ነው፡፡ ሊቁ አባ ፅጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌው ድርሰቱ ምሳሌ መስሎ ሲናገርላት የምድራውያን ጌጥ ይላታል፡፡ ‹‹ሀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ተሰገወ ምድር በሥነ ጽጌያት፤ ክረምቱ አለፈ፤ የበረከት ዘመን መጣ፤ ምድርም በአበቦች አጌጠች፤ አባ ጽጌ ድንግልም ለጊዜው ስለ ክረምቱ አልፎ በጋው ስለመተካቱ የተናገረው ቢሆንም  ምሥጢሩና ፍፃሜው ግን ለእመቤታችን ነው፤ ክረምት የተባለው የብሉይ ኪዳን ዘመን ነው፡፡ በክረምት መከራ ውጣ ውረድ የበዛበት ወቅት ነው፤ ብሉይ ኪዳንም ኃጢአት ሞት የሰለጠነበት ዘመን ነበር፡፡

ክረምቱ ሲያልፍ በጋው ለገበሬው በረከት ተስፋም ለምድር ውበትን ይዞ ይመጣል፤ ምድርም በጽጌያት ትዋባለች፤ በክረምት ገበሬው ዝናቡን ጭቃውን ታግሦ በጋው ሲመጣ የመከራው ዘመን አልፎ በረከትን የሚያገኝበት ወቅት ነው፡፡ ነቢያትም በብሉይ ኪዳን ሞት መከራን ታግሠው በሐዲስ ኪዳን አበባዋ እመቤታችን ፍሬ ሕይወት ክርስቶስን ይዛ ተገኝታልናለች፡፡ እኛ ምድራውያንም በእመቤታችን አጊጠናል፡፡ ከፍሬ በፊት አበባ እንደሚገኝ ከክርስቶስ በፊት አበባዋ እመቤታችንን አገኘን፡፡ አበባዋ ድንግል ማርያምም ክርስቶስን ሰጠችን የምንለው ለዚህም ነው፡፡ የሕይወታችን ጌጥ የምንላት በበጋ ገበሬው ክረምት የደከመበትን የሚያገኝበት ስለሆነች ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳንም ነቢያት በብሉይ ኪዳን በተስፋ መነጽር አሻግረው ሲያዩት የነበረውን ከአበባዋ እመቤታችን መድኅን ክርስቶስን አግኝተው የተደሰቱበት ያጌጡበት ናት፡፡ የመከራው የሞት ዘመን አልፎ የሕይወትና የሰላም ዘመን በክርስቶስ መጥቷልና ምድራውያንም አጊጠናል፡፡ ስለዚህም ይህች ዓለም በሥነ ፍጥረት እንደተዋበችና እንደተጌጠች የሰው ልጅም በድንግል ማርያም ሰማያዊ ጌጥ ሽልማትን አግኝቷል፡፡ አማናዊት በገራህተ ሠሉስ የተመሰለች እመቤታችንን የሕይወታችን ጌጥ እንላታለን፡፡

ይቆየን!